“ኢትዮጵያ ቡና ካጣቸው ወርቅ ልጆቹ መካከል አሰግድ ተስፋዬ አንዱ ነው” ክፍሌ ወልዴ (የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር)

በዛሬዋ ዕለት የዛሬ ሦስት ዓመት በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬን ለተከታታይ ቀናት እንዘክረዋለን ባልነው መሠረት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበርን በመወከል ክፍሌ ወልዴ ይህንን መልዕክት አጋርቶናል።

” አሰግድ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እጅግ ከሚወደዱ እና ታሪክ ሰርተው ካለፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ቡና እንዲወደድ እና ገናና እንዲሆን ካደረጋቸው ወቅቶች አንዱ እነ አሰግድ የመጡበት ከ1988 በኋላ ያለው ትውልድ ነው። ብዙ ጊዜ ሚዲያው ኢትዮጵያ ቡና በአንድ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ቀረ ከሚለው በቀር ትልቅ ገድል ቢኖር በምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ የክለቦች ዋንጫ ላይ ከሀገር ውጭ የመጀመርያውን የነሐስ ሜዳልያ ያስገኘው ኢትዮጵያ ቡና ነው። ይህ ታሪክ ሲደበቅ ያበሳጫል፤ ለምን እነ አሰግድን የመርሳት ያህል ስለ ሚቆጠር። በዚህ ታሪክ ውስጥ የአሰግድ ሚና ከፍተኛ ነበር። በዚህ ውድድር አሰግድ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀበት ነው። አስታውሳለው ይሄንን ቡድን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመሄድ አቀባበል አድርገናል። የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የመጨረሻ ውድድር (ከዛ በኋላ ፕሪምየር ሊግ ተጀምሯል) የነበረውን የ1989 ዋንጫን ኢትዮጵያ ቡና ያነሳው በአሰግድ እየተመራ ነበር። ይህ ለኢትዮጵያ ቡና ቅርስ (ማስታወሻ) የሆነን ዋንጫ በአሰግድ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያገኘነው ነው።

“የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አሰግድን ከምናስታውሰበት መንገድ አንዱ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀው ነው። በኢትዮጵያ ቡና ካየናቸው ተጫዋቾች መካከል በቅጣት ምት አሰግድን የሚስተካከለው የለም። ከድሮው ሙልጌታ ወልደየስ፣ ሚልዮን በጋሻው፣ ዮናስ ተፈራ፣ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) እና በዚህ ዘመን ዳዊት እስጢፋኖስን የቅጣት ምት ኳስ አጠቃቀማቸው ምርጥ ነው ብለን እንናገራለን። ግን ከእነዚህን ሁሉ ተጫዋቾች በላይ ቅጣት ምት ሊመታ ሲል ጎል እንደሚያስቆጥር እርግጠኛ የምትሆነው አሰግድ ተስፋዬ ሲመታ ብቻ ነው። ለዚህም ነው አሰግድ ቅጣት ምት ሊመታ ሲል የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች “አሴ.. ጎል.. ጎል..” የሚሉት።

” ከዚህ ውጭ አሰግድ አንበል በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ጫጫታ አትሰማም ነበር። ቡድን የመምራት፣ አንድ የማድረግ፣ በቡድኑ ውስጥ የገባን አላስፈላጊ መንፈስ በአሰልጣኝ እና በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን የማስተካከል እና ለበጎ አላማ ቡድን የማስተባበር ልዩ አቅም የነበረው ተጫዋች ነው። አመለ ሸጋነቱ እና ሰው አክባሪነቱ ጨዋነቱ የአሰግድ መልካም ገፅታዎቹ ናቸው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቡና አስር ቁጥር መለያ ለብሶ በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ሐ ሀትሪክ መስራት የቻለ ከስንት አንዴ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ቀልጣፋ ተጫዋች ነው።

” እግርኳስን ካቆመ በኃላ በተለያዩ ኃላፊነቶች ኢትዮጵያ ቡናን ማገልገል የቻለ ሲሆን ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት እርሱ ያገኘውን እድል ታዳጊዎች እንዲያገኙ ለማድረግ ፕሮጀክት ከፍቶ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችን በመላው ዓለም ይዞ በመሄድ ለማብቃት የነበረውን ፍላጎት ስታይ ምን ያህል ለሀገሩ እግርኳስ እድገት አሳቢ እንደሆነ ታያለህ።

” አሟሟቱ እጅግ ያልተጠበቀ ድንገተኛ የሆነ አሳዛኝ ነው። አሰግድ በድንገት እንዲህ እናጣዋለን ብለን አልጠበቅንም ያው መቼም ሞት አይቀርም ነፍስ ይማር እንላለን ። አሰግድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ነው። አሰግድን ባስታወስን ቁጥር ሁሌም እናዝናለን። ኢትዮጵያ ቡና ካጣቸው ወርቅ ልጆች አንዱ ነው። በምንም መንገድ የማትረሳው በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ልብ ሁሌም የሚታወስ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ