የቀድሞው ታላቅ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሦስተኛ ዓመቱን አስመልክቶ በተለያዩ ፅሁፎች ስናስበው መቆየታችን ይታወሳል። በዚህ መሰናዶም ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር በሕልፈቱ ወቅት ያዘጋጀውና የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበትን ፅሁፍ እነሆ!
እውነተኛ የኳስ ጀግና የደጃቱ ፍሬ የአሸዋው ሜዳ አብዶኛ፣ አጭሩ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ባለሟል፣ ቀንደኛው የጎል ሰው፣ ለድሬዳዋ “ፔሌ” ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና መድን “አለን ዥሬስ”፣ ለኢትዮጵያ ቡና “ሮማርዮ” የነበረው የጎል ማሽን አሰግድ ተስፋዬ በሚወደው እግር ኳስ ሕወቱን ባሳለፈበት ሜዳ ጀምሮ እዛው እስትንፋሱ ጨረሰ።
የጊዜው ወደር የለሽ አጥቂ የዘመኑ ድንቅ ባለ ክህሎት በሁለቱ ትልልቅ ክለቦች ደጋፊ እኩል ከበሬታ ያገኘው ሰው ህይወቱ ግንቦት 26 ቀን 2009 አርፎ በሁለተኛው ቀን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል። ይህ ሰው በተጫወተባቸው አስራ ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁነኛ መለያ ነበር። የእግር ኳሱ ኃይሌ ገብረሥላሴነት ክብርን በዘመኑ ማግኘት ይችላል። በሦስቱ ታላላቅ ቡድኖች በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ግቦችን አምርቷል። በእርሱ ዘመን ከተፈጠሩ አጥቂዎች በፍጥነት ዝግ ያለ ቢሆንም ነገር ግን በአዕምሮ እሳቤ ፈጣን ሆኖ ኮከብነትን ደጋግሟል። በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ትልቁ ውጤት ምንድነው ካላችሁ የደጋን እግሩ ባለቤት ያለበት ኢትዮጵያ መድን የአራቱ የአፍሪካ ምርጥ ቡድንነት ታሪክ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ሆኖ ታገኙታላቹ። በዚ ቡድን ውስጥ የአሰግድ ግቦች በዚህ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ነበሩ።
የሃያ ሦስተኛው የዩጋንዳ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ማነው ብላቹየችሁ ጠይቁ። በሴካፋ ክለቦች ታሪክ ኢትዮጵያዊው ቀዳሚ ኮከብ ግብ አስቆጣሪም ነው። የአርባ አንድ ዓመቱ ኢትዮጵያ ቡና የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤትነት ዋነኛ መንስዔ እሱ ነበር። የስልሳ ስምንተኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ስቴድየም ድንቅ ግብ ክለቡን በአፍሪካ ደረጃ ለመጀመርያ ግዜ ለቻምፕየንስ ሊግ ክብር አብቅቶታል። መች ይሄ ብቻ የ1988 የኢትዮጵያ ቻምፒዮንስ ሊግ ጥምር ግብ አስቆጣሪ እና የአዲስ አበባ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ጭምር ነበር። በኢትዮጵያ ቻምፒዮና ታሪክ በአንድ ውድድር የሦስት ሦስታዎች(ሐት-ትሪክ) ባለቤት ፤ በአንድ የውድድር ዓመት አምስት ሦስታዎች በመስራት የመጀመርያው ሰው ነው። እነዚ ሁሉ በአንድነት የድንቁ አጥቂ የአሰግድ ተስፋዬ የስኬት መዝገብ የሚያቀኑ ናቸው።
የሲሸልሱ ሴይንት ሚሼል ኢትዮጵያዊው ሮማርዮን በሚገባ ያስታውሳል፤ በአንድ ጨዋታ አምስት ግቦች ሸምቶባቸዋልና። የሆሳም ሐሰኑ አልአህሊ ላይ ያስቆጠረው የመቀስ ምት ግብ፣ የዛማሌኩ የአንድ ሁለት ቅብብል ድንቅ ግብ፣ የቴሌኮም ወንድረርስ ጥምዝ ቅጣት ምት ሁሌም ከኢትዮጲያውያን የእግርኳስ ቤተሰብ የማይጠፉ ትዝታዎች ናቸው። ቀዳሚ የሴካፋን ነሐስ በክለብ ደረጃ ሲገኝ ይህ ሰው ኮከብ ግብ አግቢም ነበር።
ከሀምሳ ጨዋታዎች በላይ ሀገሩን ወክሎ ግቦችን አምርቷል። የድሬዳዋው ግኝት በእርሱ ዘመን በነበሩ ተጫዋቾች ምርጥ አስራ አንድ ሁሉም ተቀዳሚ የአጥቂ ምርጫ ነበር። ከሀረርጌ ኮከብነት አንስቶ እስከ ምስራቅ አፍሪካ ኮከብነት አንፀባራቂ የእግር ኳስ ሕይወት አሳልፏል። በደቡብ አፍሪካ የመጫወት ዕድል ቢያገኝም ልቡ ግን ከሀገሩ መውጣት አልፈቀደችም። አሰግድ ተስፋዬ ከሜዳ ውጭም በድንቅ ባህሪው አብረው የተጫወቱት ይመሰክሩለታል፤ ለተጫዋቾች ወዳጅ ለጭንቅ ቦታ የሌለው መልካሙን የሚያስቀድም ሰው ነበር።
አስር ቁጥሩ በ1993 በቡና ማልያ ጫማውን ሰቀለ። ከዛ በኃላ በግሉ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለመደገፍ ያልተሞከሩ መንገዶች እያሳካ ለአስራ ስድስት ዓመታት ታትሯል። ፓሽን የእግር ኳስ አካዳሚ እና አሴጋ አካዳሚን መስርቶ ታዳጊዎች በእርሱ መንገድ መቅረፁን ቀጠለ በሀገር ደረጃ ያልተሳካውን የጎትያ የአለማቀፍ ዋንጫ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች በታዳጊዎች ተሳታፊነትም አግኝቷል።
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ችሎታ በመላው ዓለም እንዲታይ መንገዶችን አመቻችቷል። ለአሰልጣኞች ከፈረንሳይ ሆላንድ እና ሌሎች ሀገራት ስልጠና እያስመጣም ይሰጥ ነበር። በእግርኳሱ ሩቅ ህልም ነበረው፤ ነገር ግን ሞት ቀደመው። የጎሉ አድባር፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ዘመን አይሽሬ አስር ቁጥር፣ የድሬዳዋው መለያ ሕይወቱን ሁለት ሦስተኛ ባሳለፈበት የእግር ኳስ ሜዳ ህልፈት ሆነ።
ግንቦት 26 ቀን 2009 ቅዳሜ ረፋዱን እንደ ሁልጊዜው እየቀለደ እና እየተላፋ ከጓደኞቹ ጋር በፈገግታ ኳስ ተጫወተ። ቦሌ መድሐኔዓለም አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ከሌላው ቀን በተለየ ከጨዋታው በኃላ ግዜ ፈጅቶ ሰውነቱን አላቀቀ፤ እናም ወደ መታጠብያ ቤት አመራ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ግን ባለ ግርማ ሞገሱ አጥቂ ተዝለፍልፎ ተገኘ። እናም ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። ነገር ግን ሞት ከሆስፒታል ዶክተሮች በፊት ሕይወቱን ነጠቀው። አሰግድ ተስፋዬ ሁሌም የሚኖር ሰው እየመሰለ በሀያት ሆስፒታል አልጋ አሸለበ።
የአንዲት ሴት ልጅ አባት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እውነተኛ ጀግና፣ ባለ ሩቅ አላሚው ሰው ወዳጀ ብዙ የህዝብ ተወዳጅ ልጅ አሰግድ ተስፋዬ። ሀዘኑ የሁሉም ልብ ሰብሯል። ከቦሌ መድሐኒዓለም ሜዳ እስከ መላው ኢትዮጵያ ድረስ ድንጋጤው ከባድ ነበር። በሰሜን አሜሪካ በአውሮፓ እና በአጥቂነት የብሔራዊ ቡድን አጣማሪው ኤልያስ ጁሐር ባለበት አውስትራሊያ ድረስ የአሴ ጎል ሞት እምባ አራጭቷል። ኢትዮጵያ ያጣችው የእግር ኳስ የአንድ ትውልድ የሀገር ጀግናዋን ነው። የእግር ኳስ ዘመኑ ድንቅነት ግን ሁሌም በኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አብሮ ይኖራል፤ እሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዘመኑ ልዩ ምልክት እውነተኛ የእግርኳስ ጀግና ነበር።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ