አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ከአሰልጣኞች ጋር የፈጠሩት መልካም ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እያደገ እና እያስመሰገነ ይገኛል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ በሀገራችን ያሉ የእግር ኳስ ውድድሮቸ በመሰረዛቸው በተለይ ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኞች ልክ እንደማህበረሰቡ ሁሉ ወደየቤቱ ለመሰብሰብ ተገዷል፡፡ ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በግል ተነሳሽነት የጀመሩት ከአሰልጣኞች ጋር ለመማማር ይረዳ ዘንድ በቪዲዮ ምስል ግንኙነት እያደገ የመጣ ይመስላል፡፡
አሰልጣኙ ባሳለፍነው ዕሁድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ስለ ዘመናዊ የቪዲዮ ቴክኖሎጂ እና አሰልጣኞች በምን መልኩ ይህን በሽታ ተቋቁመው ወደ ስራ ለመግባት ምን ማድረግ አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይትን ያደረጉ ሲሆን ከትላንት በስቲያ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በርካታ የእግርኳሱ ቤተሰብ ከመጀመሪያው ዕለት ስብሰባ በተለየ መልኩ ቁጥራቸው አድጎ ውይይት ያደረጉበት ነበር፡፡
ረቡዕ አመሻሽ በነበረው የቪዲዮ ኮንፈረንስ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና በአሜሪካ የሳክሬም ዩናይትድ አካዳሚ የሴቶች ዳይሬክተር አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን ውይይቱን በዋናነት የመሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ጂራ የፅህፈት ቤት ጊዜያዊ ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን የስራ አስፈፃሚ አባሉ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና በመጀመሪያው ስብሰባም ተሳትፎ ያደረጉት ቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን ኩሩ ተገኝተውበታል፡፡ ከፌዴሬሽኑ አካላት በተጨማሪ በአሰልጣኝ አብረሀም ግብዣ የቀረበላቸው የካፍ ቴክኒክ ዳይሬክተር ራውል ቺፔንዳ እና ከሀገራችን ኢትዮጵያ ተገኝታ በካፍ የሴቶች ልማት ኮሚቴ ውስጥ በሀላፊነት እየሰራች የምትገኘው መስከረም ታደሰም የዚህ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሎች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ ቀን ስብሰባ ከነበሩ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ባለፈ በሴቶች እግር ኳስ ላይ እየሰሩ ያሉት አሰልጣኝ መሠረት ማኒ፣ ብርሀኑ ግዛው እና ኢንስተራክተር ሰላም ዘርዓይም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
ውይይት ከመጀመሪያው ቀን ጠንከር ያለ እና ብዙ ሀሳቦች የተነሱበት እንደነበረ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡ “የኮሮና ቫይረስን ክለቦች አሰልጣኞች አመራሮች እና የሚመለከተው ሁሉ እንዴት በጋራ ሆኖ መከላከል ይችላል፤ ይህን በሽታ ቢኖርም እንዴት ህይወት ዘርተን ወደ እግር ኳሱ እና ወደ ውድድር መመለስ እንችላለን” የሚሉ በዋናነት ለውይይት የቀረቡ አንኳር ጉዳዮች ሲሆኑ ስለ ቪዲዮ ቴክኖሎጂም በዚህኛው ቀን በስፋት የተቃኘ ርዕስ ነበር፡፡ ሦስት ሰዓታትን የፈጀው እና በቀጣይም እያደገ እንደሚመጣ የተነገረው ይህ ውይይት ከአሰልጣኞቹ እና ከፌዴሬሽን ሰዎች በተጨማሪ የካፍ ተወካዮች መገኘታቸው ይበልጥ በርካታ ሀሳቦች እንዲነሱበትም ሆኗል፡፡ ካፍን በመወከል የተገኙት ቴክኒክ ዳይሬክተሩ ራውል ቺፔንዳ “በዚህ የኮሮና ወቅት ሌሎች ሀገራት ተግባራዊ እያደረጉ ስላለው የእግር ኳስ በጎ ፅንሰ ሀሳብ ተነስተው ለሀገራችን አሰልጣኞች እና ለውይይቱ ተሳታፊዎች የገለፁ ሲሆን አሁን እየተደረገ ያለው የቪዲዮ ኮንፈረንስ ደስ ይላል ቀጣይነት ካለው እኔም በተፈለኩ ጊዜ ሀሳብ ለማካፈል ዝግጁ ነኝ።” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የካፍ የሴቶች ልማት ኮሚቴን በመወከል የተገኘችው መስከረም ታደሰ በበኩሏ በአፍሪካ የሴቶች እግርኳስ ትኩረት እያገኘ አለመሆኑን ገልፃ ለወንዶች ብቻ ሳይሆን ሀገራት ለሴቶች እግር ኳስ እድገት መስራት አለባቸው ያለች ሲሆን ከሰሜን ሀገራት ውጪ ሌሎች ሀገራትም በሰፊው እዚህ ላይ ሊሰሩ ይገባል ብላለች መስከረም በንግግሯ በኮሮና የተነሳ ቤት ውስጥ የገቡት ሴት የእግርኳሱ ቤተሰቦች ከወንዶች ይልቅ ሊጠቁ ወይንም ሊጎዱ ስለሚችሉ በተለየ መልኩ ትኩረት ራሳቸውን የቻለ መዋቅር ሊበጅላቸው እንደሚችልም የፌዴሬሽኑን አካላትን ገልፃ ኢትዮጵያም ሰፊ ድርሻ ሊኖራት ይችላል በማለት አብራርታለች፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ በውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑ አሰልጣኞች ጋር በነበራት ቆይታ አሰልጣኞች ይህ ውይይት እያደገ መምጣቱን የገለፁ ሲሆን “በዚህ ጊዜ ስለ ኮሮና ብቻ እያሰብን ሙያችንን ዘንግተን የነበረ ቢሆንም ይህ ውይይት ከመጣ በኃላ ራሳችንን ማንቃት ጀምረናል።” ብለዋል። በተለይ በፕሪምየር ሊጉ እያሰለጠኑ ያሉ አሰልጣኞች አብርሀም መብራቱን አመስግነዋል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ