በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ውስጥ ጎልተው ከወጡ ተጫዋቾች መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አጥቂ ረሂማ ዘርጋ አንዷ ነች። እኛም ስኬታማዋን ግብ አዳኝ በዛሬው የሴቶች አምዳችን ቃኝተናታል፡፡
ትውልድ እና ዕድገቷ በመዲናችን አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው፡፡ ኳስንም የጀመረችው እዛው ሽሮ ሜዳ ቀበሌ 03 ከሠፈር ጓደኞቿ ጋር ነበር። ከቆይታ በኋላም በወቅቱ ተክለኃይማኖት ፔፕሲ የሚሰሩ የሰፈር ጓደኞቿ እጇን ይዘው በአሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ በሚሰለጥነው ተክለሀይማኖት ፔፕሲ ቡድን ቀላቀሏት። በተክለኃይማኖት ፔፕሲም የአምስት ዓመታት ቆይታን ካደረገች በኋላ 2000 ላይ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚያሰለጥነው የሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ቡድን አስፈረማት። በክለቡ ቆይታዋ መልካም ጊዜን አሳልፋ 2003 ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሸጡ ተጫዋቿም ከሌሎች የቡድን ጓደኞቿ ጋር በመሆን ወደ ንግድ ባንክ ተዘዋውራ እስከ አሁኗ ጊዜ ድረስ በዚሁ ክለብ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሜዳ ላይ የመምራት አቅሟ እና በግንባር የምታስቆጥራቸው ግቦች መገለጫዎቿ እንደሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚመሰከርላት ረሂማ በሦስቱ ቡድኖች ቆይታዋ አስር ዋንጫዎችን ማሳካት ችላለች፡፡
“በተክለኃይማኖት በነበረኝ ቆይታ ከአሰልጣኝ ቴዲ ጋር እንደ አባት እና ልጅ ነበር ቀረቤታችን። ከሱ ተለይቶ ወደ አዲስ ክለብ ፣ አዲስ አሰልጣኝ እና አዲስ ተጫዋቾች መሄድ ትንሽ ይከብድ ነበር። ነገር ግን አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ደግሞ ብዙም የሚከብድ ባህሪ አልነበረውም። ወደ ሴንትራል ስገባም ደስ በሚል ነገር ተቀበለኝ። በሴንትራል ስንቆይ እንደሀብታም ቡድን ነበር ስንኖር የነበረው ፤ ትልቁ ክፍያ የሚከፈለንም እኛ ነበርን (ስምንት መቶ ብር)። እናም አንድ ቦታ አስቀምጦን ከእግር ኳሱ ባለፈ በኮሌጁ እያስተማረን ነበር። የክለቡ መስራች አቶ አብነት የፈለግነውን የትምህርት ዓይነት ራሳችን መርጠን እንድንማር አድርገው ነበር። ለኔ የሴንትራል ቆይታዬ በጣም ደስ የሚል ነበር።” በማለት በሴንትራል የነበራትን የሦስት ዓመታት ጊዜ ታስታውሳለች።
ከሴንትራል ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ተቀላቅላ እስከ አሁን ድረስ ቡድኑን ከፊት በአጥቂነት ከዛም ባሻገር በአምበልነት እየመራች ያለችው ረሂማ ዘርጋው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ውስጥ ያለፉትን አስራ ሁለት ዓመታት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
” ንግድ ባንክ ከሌላው ቡድን የሚለየው በአንድነቱ ነው ፤ ደስ ይላል። ቤስት ወይም ቤንች የሚባል ነገር የለም ማናችንም እንደሰውነታችን ነው የምንከባበረው። አሰልጣኛችንም የሚለየው ነገር የለም። ረሂማ ሁሌም ተሰላፊ ናት ብሎ ሌላውን የሚጎዳበት መንገድ የለም። ሁሉም እስታፎች ጋር ተመሳሳይ ነገር አለ። በንግድ ባንክ ይሄን ያህል እንድጫወትንም እነኚህ ነገሮች ምክንያት ሆነውኛል። በዚህ አጋጣሚ እኔም ለሰው ልጅ ትልቅ ቦታ አለኝ ፤ ትልቅ ነው ትንሽ ነው ብዬ አይደለም ሁሉንም እያከበርኩኝ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩት። ከአሰልጣኝ ብርሀኑ ጋር የምንስማማበት ነገርም ታዝዤ ስለምሰራ ነው። አምበልም ነኝ ቢሆንም ከሱ ጋር ስለቤተሰቤም ስለ ራሴም እየተመካከርኩኝ ነው ለዚህ ደረጃ የደረስኩት። ምንም ያህል የተለየ ተጫዋቾች መሆን ቢቻል እንኳን እሱ ጋር ዲሲፕሊን ወሳኝ ነው። ለቡድኔም በጣም ትልቅ ክብር አለኝ። ” ስትል የረጅሙን የንግድ ባንክ ቆይታዋን ምክንያት ትናገራለች።
በንግድ ባንክ በቆይችባቸው ጊዚያት በርካታ ስኬቶችን ያጣጣመችው ረሂማ የቡድኑ የስኬት ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲህ ስትል ታብራራለች። ” ከሴንትራል ጀምሮ አብዛኛዎቻችን ተያይዘን ነው የመጣነው። በተለይ ከሽታዬ ጋር በደንብ እንግባባለን። ከብዙ ቆይታችንም እኔ ምን እንደምፈልግ ሽታዬ ታውቃለች እኔም ደግሞ እሷ ምን እንደምትፈልግ አውቃለሁ። ከቆይታ አንፃር በባህሪም ሆነ በምንም ነገር ስለምንግባባ ውጤታማ ሆነናል። እናም ረጅም ዓመታትን አብረን ስለነበርን ለንግድ ባንክ ውጤታማነት አስተዋጽኦን አድርጓል። በመሀል ብንበታተን ይሄ ውጤት ሊመጣ አይችልም ነበር። ሁሉም እርስ በእርስ ስለሚተዋወቅ አንድ ላይ መሆናችን ጠቅሞናል ብዬ አስባለሁ”
በ1990ዎቹ ማብቂያ ላይ በተክለኃይማኖት ፔፕሲ ስትጫወት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጥሪ ደርሷት የመመረጥ ዕድልን ግን ያላገኘች ቢሆንም ረሂማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በብሔራዊ ቡድኑ የተሳካ ዓመታትን ስታሳልፍ ቆይታለች። በአሁኑ ሰዓትም የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ጭምርም ሆናለች። “ያኔ ስቀነስ ምንም አልመሰለኝም። ምክንያቱም እነአዲስ ፈለቀ ፣ ሽታዬ ሲሳይ እና ብርቱካን ገብረክርስቶስን በጣም አደንቃቸው ነበር። እነሱ ጋር ደርሼ በመመለሴ ራሱ ደስተኛ ነበርኩ። ስቀነስ ራሱ እኔም ከዛ በኃላ እነሱ የደረሱበት ለመድረስ ነበረ ስሰራ የነበረው። አላህም አላሳፈረኝም ከእነሱ ጋር አብሬ ተጫውቻለሁ። እስከ አሁንም አጠገቤ ሆነው የሚጎለኝን እንነጋገራለን። ያኔ እነሱ ለኔ የሰጡኝን ለሌላው እየሰጠው ያን እያስቀጠልኩ መምጣቴ በብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጊዜ እንዲኖረኝ አስችሎኛል።” ትላለች።
በሀገራችን እምብዛም ባልተለመደ መልኩ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች የመመዝገብ ልምድ ያላት ረሂማ በእግር ኳስ ህይወቷ 574 ግቦችን እንዳስቆጠረች እና 168 ያህሉን በግንባሯ በመግጨት ከመረብ እንዳሳረፈቻቸው ትናገራለች። በተክለኃይማኖት የአምስት ዓመት ቆይታዋ 182 ፣ በሴንትራል በነበራት የሦስት ዓመት ጊዜ 122 ፣ በንግድ ባንኩ ያሉፉት የዘጠኝ ዓመታት ቆይታዋ 252 እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ላለፉት 12 ዓመታት 18 ጎሎችን ማስቆጠሯን መዝግባለች።
በብዙሀኑ የእግር ኳስ ቤተሰብ ዘንድ በሥነ ምግባሯ ተምሳሌት ተደርጋ የምትገለፀው ረሂማን ከአስራ ሁለት ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት አብሯት የዘለቀው ብርሀኑ ግዛው እንዲህ ሲል ገልጿታል፡፡ ” 1996 ላይ የአዲስ አበባ ምርጥ አሰልጣኝነት ቦታን አግኝቼ ነበር ፤ እሷ ፔፕሲ እየተጫወተች ማለት ነው። የዛን ሰዓት በደንብ አየሁዋት። በተጨማሪ 1998 ላይ አዲስ አበባ ምርጥን ይዤ በባህርዳር በነበረው ውድድር ላይ በድጋሜ ሳያት ‘ይህችን ልጅ ለወደፊቱ ማሰልጠን ከምፈልጋቸው አንዷ ናት’ ብዬ አሰብኩ። ሴንትራልን ስይዝም አመጣኋት። ከዚህ ባለፈ ማኔጅመንቷን አይቼ ነው በንግድ ባንክም በብሔራዊ ቡድንም አምበል ያደረኳት። ብዙ ተጫዋቾች አሰልጥኛለሁ። የሷ ከሌላው ሁሉ የሚገርመኝ ባህሪዋ ገራገርነቷ ነው። በአጠቃላይ የተሰጣትን የምትወጣ ናት ፤ ከእግር ኳሱም ውጪ ከሷ ተለይቶ መኖር የምትከብድ ሙሉ ሰው ነች። ”
ከሀገር ወጥቶ የመጫወት ትልቅ ፍላጎት ያላት ረሂማ ‘ሎዛ አበራ እንዳደረገችሁ ሁሉ እኔም ዝግጁ ሆኛለሁ’ ትላለች። ” ከሀገሬ ጋር ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍን እፈልጋለሁ። ከዚያ ቀጥሎ ግን በውጪ ሊግ መጫወት እፈልጋለሁ። ውስጤ የሚሰማኝ ያ ነው ፤ መድፈር አለብኝ ከሎዛ የተማርኩት ነገር አለ። ደፍሬ ወጥቼ ትልቅ ተጫዋች መሆኔን ስለማውቀው ባለኝ ነገር በውጪ ሊግ መጫወትን አስባለው።”
እግር ኳስ ተጫዋች መሆንን ከልጅነቷ አልማ የተነሳችው እና በቤተሰቧ ዘንድ ከዕምነቷ አንፃር በተለይ ከወንድሞቿ ዘንድ ‘ አትጫወቺ’ የሚል ሀሳብን ታስተናግድ የነበረችው ረሂማ በአባቷ ጥረት እዚህ መድረሷን ትናገራለች። “አባዬ እኔ ስጫወት ደጋፊዎችም ያውቁታል። ለኔ ያለውን ነገር ሳይሰስት ያደርግልኛል ያኔ ኳስን መጫወት ስጀምር መሳፈሪያ እንኳን አልነበረኝም ፤ እሱ ነበር የሚደጉመኝ። ጫማዎችን ይገዛልኝ ነበር ፤ እንዳይከፋኝ ብዙ ነገር ያደርግልኝ ነበር። በእኛ ኃይማኖት በእስልምና ዘንድ ተፅዕኖ ስለነበረው በዚያ ሰዓት ከአጠገቤ ሆኖ ሲደግፈኝ የነበረው አባቴ ነው። ትንሽ ታላቅ ወንድሜ ይቆጣኝ ነበር ‘ እንዴት ቀሚስ ፣ ሻሽ አውልቃ ? ‘ በሚል ትንሽ ከአባቴ ጋር ይጋጩ ነበር። ግን አሸንፌ እንድወጣ ያደረገኝ አባቴ ነው። ኳስ በጣም ይወዳል አሁንም መጥቶ ቢያየኝ ደስ ይለኛል። አሁን ላይ ዕድሜው ቢገፋም ከአላህ ቀጥሎ እዚህ እንድደርስ የረዳኝ አባቴ ነው። ”
በመጨረሻም ረሂማ እዚህ ለመድረሷ ለአባቷ ምስጋና የቸረች ሲሆን ለቀድሞው አሰልጣኟ ቴዎድሮስ ደስታ እና በእሱዋ አገላለፅ ‘ከጎኔ ሆኖ ዛሬም ድረስ በህይወቴ ላይ ትልቅ ድርሻ ላለው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ለሰፈር ሰዎች በተጨማሪም ደግሞ ለሚደግፉኝ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” በማለት ገልፃለች፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ