በሁሉም የሀገሪቷ የሊግ ውድድሮች የደሞዝ አልተከፈለንም ጥያቄ በበረታበት በዚህ ሰዓት የወላይታ ድቻ ተጫዋቾችም ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ክለቡ ላይ ቅሬታ እያሰሙ ይገኛል።
በኮሮና ወረርሺኝ ሊጉ መቋረጡ ተከትሎ በኢትዮጵያ እግርኳስ አሳሳቢ ችግር እየሆነ የመጣው የተጫዋቾች የወራት ደሞዝ አልተከፈለንም ጥያቄ በተደደጋጋሚ እየተነሳ ይገኛል። ያለፉትን ዓመታት አንድም ቀን ለተጫዋቾች ደሞዝ በመክፈል አስተጓግሎ የማያቀው ወላይታ ድቻ ስሙ ከተጫዋቾች ደሞዝ ክፍያ ጋር መነሳቱ አስገራሚ ሆኗል። ተጫዋቾቹ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳደረሱት መረጃ ከሆነ “ይህው ደሞዝ መከፈል ካቆመ ሦስት ወር ሆኖናል። ለምን እንደዘገየብን በስልክ ብንደውል ምላሽ የሚሰጠን አካል አጥተናል። ወላይታ ድቻ በተጫዋች ደሞዝ አለመክፈል ስሙ ተነስቶ አያውቅም ነበር። በትዕግስት ይከፈለናል ብለን ብንጠይቅም ይህው ሦስት ወር ሆነን። ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሲሆን ወደ ሚዲያ ለመውጣት ተገደናል።” ብለዋል።
የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ኃይሌ በበኩላቸው ” ያልከፈልነው ደሞዝ የሚያዚያ እና የዚህን ወር የግንቦትን የሁለት ወር ብቻ ነው። ክፍያውም የዘገየበት ምክንያት የቦርድ አመራሮቻችን ከወቅቱ ሁኔታ አንፃር ትኩረታቸውን እዛ ላይ ያደረጉ በመሆናቸው ነው። የተጫዋቾቹ ደሞዝ እንዲቀርባቸው አንፈልግም። በዚህ አስራ አምስት ቀን ውስጥ የክለቡ የቦርድ አመራር ተነጋግሮ ክፍያውን ይፈፅማል ” ብለውናል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ