ቶክ ጀምስ በኢራቅ ቆይታው ምንድነው የገጠመው?
በአንድ ወቅት በሊጉ ውስጥ ከነበሩት ተስፈኛ ተከላካዮች ግንባር ቀደም ነበር። ረጅም ተክለ ሰውነት እና የተረጋጋ አጨዋወት ያለው ቶክ ጀምስ የእግርኳስ ሕይወቱ የመጀመርያ ዓመታት ከተጠበቀው በላይ የተሳካ እና እስከ ብሔራዊ ቡድን መጠራት ድረስ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ ግን በርካታ መሰናክሎች አጋጥመውት ብዙ ተስፋ የተደረገለት ብቃትም ለረጅም ጊዜ መታየት አልቻለም።
በ2003 በባቱ በተደረገው የክልሎች ሻምፒዮና ባሳየው ብቃት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ተዘዋውሮ ከአንድ ዓመት የታዳጊ ቡድን ቆይታ በኃላ በ2004 ወደ ዋናው ቡድን በማደግ በፍጥነት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆን የቻለ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ቦታ ለማግኘትም አልተቸገረም ነበር። በኋላም ከቡና ጋር ተለያይቶ ወደ ወልዲያ ከዚያም ወደ ንግድ ባንክ የመመራው ይህ ተከላካይ በ2009 መጨረሻ ከአንድ የኢራቅ ቡድን ጋር በተያያዘ ጉዳይ አነጋጋሪ እንደነበር አይዘነጋም።
ተጫዋቹ ወደ በኢራቅ የገጠመው አይረሴ ገጠመኝ እንዲህ ያስታውሳል። ” ኢራቅ የነበረኝ ትውስታ ጥሩ አይደለም። ጉዳዩ በጣም ውስብስብ ነው፤ የጠበቅኩት እና ያገኘሁት ነገር የተለያየ ነበር። እዚህ ኢትዮጵያ ሆኜ የጨረስኩት ዝውውር ነበር። ክለቡ በቱርክ እና ኢራቅ መሀከል በሚገኘው ኩርድ የሚባል ግዛት ውስጥ የሚገኝ ክለብ ነበር፤ ቅድመ ኮንትራት ልኮልኝ ሁሉን ነገር ጨርሼ ነበር ወደዛ የሄድኩት። ከመፈረሜ በፊት በኖርዌይ በሚገኝ የባለቤቴ ወንድም አማካኝነት ብዙ ነገሮች አረጋግጠን ነው ለክለቡ የፈረምኩት። እዛ የገጠመኝ ግን ሌላ ነው ፤ የተቀበለኝ ክለብ እዚ ኢትዮጵያ እያለሁ የተፈራረምኩት ሳይሆን ሌላ ክለብ ነበር። በኤርፖት የተቀበሉኝ ሰዎች ወደማላውቀው አንድ ክለብ ነው የወሰዱኝ። ደንግጬ ለወኪሌ ስጠይቀውም አጥጋቢ መልስ አልሰጠኝም። ከዛ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነው የወሰንኩት። እዛ ሁለት ቀን ብቻ ነው የቆየሁት። የተቀበለኝ ክለብ እንድቆይ ፈልጎ ነበር ፤ እኔ ግን ፍቃደኛ አልነበርኩም። ” ብሏል።
በኢራቅ አስደሳች ያልሆነ ቆይታ እንደነበረው የሚናገረው ቶክ ጀምስ ችግሩ እንዴት እንደተፈጠረ ቆይቶ እንዳወቀ ቢናገርም አሁን ስለጉዳዩ ዝርዝር ነገር ለማውራት ጊዜው እንዳልሆነ ይናገራል። “በኢራቅ የቀናት ቆይታዬ በጣም ብዙ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ስለ ችግሩ መናገር አልፈልግም፤ አሁን አልፏአል። ችግሩ እንዴት ተፈጠረ ላልከው በዚህ ሰዓት ስለ ዝርዝር ጉዳዩ ማውራት አልፈልግም። በዛን ሰዓት ስጠይቅ ግን አጥጋቢ ምላሽ አልተሰጠኝም። ከኢትዮጵያ ውጭ ወጥተው ለመጫወት የሚያስቡ ተጫዋቾች ከዚህ ብዙ ልምድ መውሰድ አለባቸው። ከጥሩ ወኪል ጋር መስራት አለባቸው። ከዛ በተረፈ በውል አፈራረም ላይ ብዙ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። የኳስ ሕይወቴ ምስቅልቅሉ የወጣው በወኪሎች ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ቡና እያለሁ ጀምረው ብዙ ወኪሎች ያነጋግሩኝ ነበር። በዛ ሰዓትም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ነበርኩ። እና ሌሎች ተጫዋቾችም ከማን ጋር እየሰራን ነው ብለው መጠየቅ አለባቸው።”
በዚህ ሰዓት በጥሩ ዝግጅት እንዳለ የገለፀው ቶክ ጀምስ በቀጣይ ዓመት በፕሪምየር ሊግ የመጫወት አቅም እንዳለው በልበ ሙሉነት ይናገራል። “አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ የማሰላስልበት ጊዜ አደለም ድጋሜ በትልቅ ደረጃ ለመጫወት በጥሩ ዝግጅት ነው ያለሁት፤ አቅሙም አለኝ። ያለፈው ዓመት ከከፋ ቡና ጋር በጣም ጥሩ ዓመት ነው ያሳለፍኩት። ከፍተኛ ሊጉ ብዙ ትኩረት አይሰጠውም እንጂ በጣም ፈታኝ ነው። በግሌም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ” ብሏል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ