ለሃያ ሦስት ዓመታት በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት ስኬታማ የእግርኳስ ህይወት እያሳለፈ የሚገኘው የዘጠናዎቹ ኮከብ አጥቂ የወቅቱ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ማነው?
ላመነበት ነገር ታማኝ እንደሆነ የሚነገረው መሳይ ተፈሪ በአርባምንጭ ከተማ ልዩ ስሙ ጨንቻ በተባለ አካባቢ እድገቱን አድርጓል። በታዳጊነቱ ለትምህርት ቤት እና ለቀበሌ ቡድን በመጫወት ጀምሮ በ1989 በክለብ ደረጃ ለአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ለሁለት ዓመታት ከተጫወተ በኃላ ወደ ወንጂ ስኳር በማምራት ጥሩ ቆይታ አድርጓል። በተለይ ወንጂ ስኳር ከታችኛው ዲቪዝዮን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲያድግ የነበረው ግልጋሎት የተሳካ ነበር። በወንጂ አጭር ቆይታ አድርጎ ዳግመኛ ከ1994–95 ወደ አሳዳጊው ክለብ አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ በመመለስ ለመጫወት ችሏል።
በብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የማይዘነጋው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ አሸናፊውን ለማወቅ የመጨረሻውን ጨዋታ ፊሽካ መሰማት ለመጠበቅ ከተገደዱ አይረሴ ድራማዊ ትንቅንቆች መካከል በ1995 ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨማሪ ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ዋንጫውን ከአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ በነጠቀበት ገዜ በአርባምንጭ በስብስብ ውስጥ ከነበሩ ድንቅ አጥቂዎች መካከል መሳይ ተፈሪ አንዱ ነበር። በቀጣዩ ዓመት 13 ጎሎች ለአርባምንጭ ያስቆጠረው መሳይ የጥምር ኮከብ ጎል አግቢነት ክብርን ከታፈሰ ተስፋዬ እና ቢንያም አሰፋ ጋር መጋራት ችሏል።
“መሳይን ብዙ ጊዜ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፍ ላታየው ትችላለህ። ሆኖም ሳጥን ውስጥ በትዕግስት በመጠበቅ ክፍት ቦታዎችን በመፈለግ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት በመጠቀም እጅግ የተዋጣለት ጨራሽ አጥቂ ነው።” በማለት አብረውት የተጫወቱ ይመሰክሩለታል። ከኢትዮጵያ ቡና በመቀጠል ለአየር ኃይል፣ ጥቁር ዐባይ በመጨረሻም ዳሽን ቢራ ስፖንሰር ባደረገው በአርባምንጭ ዳሽን (አርባምንጭ ከተማ) ውስጥ ተጫዋች እና ም/አሰልጣኝ በመሆን እግርኳስን እስካቆመበት 2001 ድረስ መጫወት ችሏል። አሰልጣኝ ሥዩም አባተ በያዘው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ታዳጊ እና ወጣት ቡድን በመጫወትም ሀገሩን ማገልገል ችሏል።
በኢትዮጵያ ቡና አብሮት የተጫወተው ኤልመዲን መሐመድ መሳይ በተጫዋችነቱ ይታይበት የነበረው ዝንባሌ አሰልጣኝ እንደሚሆን ፍንጭ የሚሰጥ ነበር ይላል። “መሳይ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የባላጋራ ቡድንን ድክመት እና ጥንካሬ ተመልክቶ አብረውት ለሚጫወቱት ከመምከሩ ባሻገር ተቀይሮ በመግባት ያየውን ድክመት ተጠቅሞ ጎል ሲያስቆጥር አይቸዋለው። የዛን ግዜ ከሚያደርገው ነገር ተነስተን ወደፊት አሰልጣኝ እንደሚሆን ቀድመን እናውቅ ነበር። ምክንያቱም በጣም የተደራጀ፣ በጥብቅ መከላከል ውስጥ በመልሶ ማጥቃት ጎል የሚያስቆጥር ቡድን ይወድ ነበር። ለዚህም ነው ያኔ እኔ፣ አወቀ እና ቻይና “ሞሪንሆ” እያል አንጠራው የነበረው። አሁን ላይ አሰልጣኝ ሆኖም በፊት ያመነበትን ፍልስፍና ለመተግበር በወላይታ ድቻ የሚገነባቸውን ቡድኖች ሳይ ብዙም አልገረምም። ምክንያቱም በጣም የተደራጀ፣ በመልሶ ማጥቃት የተዋጣለት፣ ታክቲካል ዲሲፒሊንድ የሆነ ቡድን አድናቂ ነው። ይህ ቀድሞ ይወድ ስለነበረ ነው እኛም ሞሪንሆ ያልነው።” ብሏል።
በአሰልጣኝነት ዘመኑ ወላይታ ድቻን ከምስረታው አንስቶ ከታችኛው ዲቪዚዮን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ በማድረግ ሁሌም በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች እና ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስም ተክሎ ያለፈ አሰልጣኝ መሆን ችሏል። በተለይ የመጫወት አቅም ኖሯቸው ብዙም የመታየት እድል ያላገኙ፣ ከታችኛው የውድድር እርከን ቦታው ድረስ በመሄድ በመመልመል ትልቅ ተጫዋቾች ያደረጋቸው በርካታ ናቸው። ለአብነት ያህል ወንድማማቾቹ በዛብህ እና እንዳለ መለዮ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ አላዛር ፋሲካ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሌሎችን መጥራት ይቻላል።
በወላይታ ድቻ ከስምንት ዓመት በላይ ቆይታው በአነስተኛ ወጪ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ከመገንባቱ ባለፈ የ2009 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ድቻ በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ችሏል። ከወላይታ ከተለያየ በኃላ በፋሲል ከነማ ለጥቂት ወራት የሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ለሚገኘው አርባምንጭ ከተማ እያሰለጠነ ይገኛል።
ለአስራ ሁለት ዓመታት በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት እስካሁን ለአስር ዓመታት የሰራው የዘጠናዎቹ ከከብ መሳይ ተፈሪ የዛሬው እንግዳችን ነው።
” አንድ ስኬት የሚለካው በዋንጫ ብዛት እና በኮከብ ሽልማት ብቻ አይደለም። በተጫዋችነት ዘመኔ ለዋንጫ አልታደል እንጂ እጅግ ስኬታማ የሆነ የእግርኳስ ህይወት አሳልፌያለው። ከአርባምንጭ ጋር የዘጠና አምስቱ የመጨረሻው የዋንጫ ጉዞ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በዘጠና ስምንት የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እስከ መጨረሻው ምዕራፍ የደረስንበት ትልቅ ስኬቴ ነው። ከታፈሰ ተስፋዬ እና ቢንያም አሰፋ ጋር በ1996 ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የተሸለምኩበት፣ እንዲሁም ወንጂ ስኳርን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደኩበት አጋጣሚ እነዚህ ለእኔ በእግርኳስ ዘመኔ መቼም የማልዘነጋቸው ጥሩ ጊዜዎቼ ናቸው።
” በአሰልጣኝነት ቆይታዬ ወላይታ ድቻን ከምንም አንስቼ ትልቅ እና አስፈሪ ቡድን እንዲሆን በመስራቴ ኩራት ይሰማኛል። በነበረኝ የስምንት ዓመት ቆይታ በርካት እውቅና ስም አግኝቻለው። ባመንኩበት የቡድን ግንባታ እና አጨዋወት በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ቡድን ሰርቼ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳት ችያለው። ፋሲል ከነማም በጥሎ ማለፍ ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ማድረስ ችዬ ነበር። ዘንድሮም አርባምንጭ ከተማን በከፍተኛው ሊግ በማሰልጠን ዳግመኛ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ከምድቡ በአንድም ጨዋታ ሳንሸነፍ ምድቡን እየመራን ለማጠናቀቅ በምናደርገው ብርቱ ትግል የኮሮና በሽታ መጥቶ ሊጉ እንዲቋረጥ አድርጎታል። በአጠቃላይ የአሰልጣኝነት ቆይታዬ መሳይ ምን እንደሚፈልግ ምን ዓላማ እንዳለው በሚገባ ማሳየት ችያለው።
” 1995 ከአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ ጋር ያንን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አለማንሳቴ በተጫዋችነት ዘመኔ በጣም የሚቆጨኝ ነገር ነው። በአንድ ወቅት ሁሉም ወደ ክልሉ ሄዶ በሀገር አቀፍ ይጫወት ተብሎ በተወሰነበት ጊዜ በደቡብ ክልል ዋንጫ አንስቼ ይሆናል። ሆኖም የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሁለቱን ጫፍ ደርሼ ዋንጫ ባለማንሳቴ በጣም ነው የምቆጨኝ። በቀጣይ የአሰልጣኝነት ዘመኔ አሳካዋለው ብዬ የማቅደው በተጫዋችነት ዘመኔ ያጣሁትን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን እና በአፍሪካ መድረክ ትልልቅ ስኬቶችን በቀጣይ በአሰልጣኝነት ቆይታዬ አሳካዋለው ብዬ ውስጤ ያምናል።
“መሳይን ይረዱት ብዬ የማስበው የእግርኳስ ፍልስፍናዬን ባለው ነገር ሰራሁት ብዬ አስባለው። ትክክለኛ የእኔ እምነት ተገልጧል ብዬ ግን አላስብም። የተወሰነ የገለጥኳቸው ነገሮች አሉ በቀጣይ ግን ባላንስ የሆነ ቡድን አጥቅቶም ተከላክሎም መጫወት የሚፈልግ ቡድን መስራት እፈልጋለው። ኳሱንም የሚጫወት ኳስ ነጥቆ በፍጥነት ጎል የሚያስቆጥር በአጠቃላይ ለማሸነፍ የሚያስችል ነገር ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባ ቡድን እንጂ ሜዳውን ክፍት አድርጎ የሚጫወት ቡድን አልፈቅድም። ኳስን እንደ አስፈላጊነቱ የሚጫወት ቡድን መስራት የእኔ ፍልስፍና እና ዕምነት ነው። ብዙ ጊዜ እሰማለው የመሳይ ቡድን ይከላከላል ይሉኛል። ይህ ግን ትክክል አይደለም። እኔ የምፈልገው የሚከላከል፣ የሚያጠቃ በተለይ ጎል የሚያስቆጥር ቡድን ነው። ይህ ደግሞ በትክክል ተገልጿል ብዬ አላስብም። ወደ ፊትም በዚህ ባመንኩበት ፍልስፍና እየቀጠልኩ በአነስተኛ ወጪ ዝቅ ብዬ አቅም እያላቸው ሆኖም የመታየት ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን ኃላፊነት ወስጄ ጠንካራ ቡድን የመስራትን መንገዴን ወደፊትም የምቀጥልበት ነው።
“በቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና የሁለት፣ የሦስት ዓመት እና የአምስት አመት ወንድ ልጆች አባት ነኝ። ሁለቱም የኳስ ፍቅር አላቸው ።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ