በአጭሩ የተቀጨው የእስራኤል ቆይታ – ትውስታ በአሥራት መገርሳ አንደበት

በአንድ ወቅት አነጋጋሪ ከነበሩት ዝውውሮች አንዱ የነበረው የአሥራት መገርሳ ወደ እስራኤል ማምራት ነበር። የብሔራዊ ቡድን ስኬታማ ቆይታውን ተከትሎ ወደ ሀፖይል ኒርራማት ሀሻሮን ዝውውር ያደረገው አሥራት ብዙም ሳይቆይ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰበትን ጉዳይ በዛሬው የትውስታ አምዳችን ይዘን ቀርበናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ እና በማጣርያ ውድድሮች ላይ የተሳካ ጊዜያት ካሳለፈ በኋላ በርካታ ተጫዋቾች ስማቸው ከአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት ክለቦች ጋር መያያዙ እና ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾችም ዝውውሩ ተሳክቶላቸው ከሀገር ውጭ ወጥተው መጫወታቸው ይታወሳል። ከተጫዋቾቹ መካከልም የወቅቱ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ አማካይ የነበረው ግዙፉ አሥራት መገርሳ ይገኝበታል። አማካዩ ለወራት ብቻ የዘለቀው የእስራኤል ቆይታው እና በመጀመርያው ጨዋታ ያጋጠመው ነገር እንዲህ ያስታውሳል።

“በመጀመርያ ዝውውሩ እንደሌላው ዝውውር በህጋዊ መንገድ ነው ያለቀው፤ ክለቤ መብራት ኃይልን ጠይቀው ነው ያስፈረሙኝ። እንደሚታወቀው በዛ ክለብ ብዙም አልቆየሁም። የቅድመ ውድድር ዝግጅት ብቻ አሳልፌ በጥቂት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች እና አንድ የነጥብ ጨዋታ ተጫውቼ ነው የተመለስኩት። የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ቃላቸውን መጠበቅ ስላልቻሉ ነው። በጥቅማ ጥቅም ደረጃ ቃል የገቡልኝን ነገር መፈፀም አልቻሉም፤ ባለቤቴንም ከእኔ ጋር እንደሚወስዷት ነበር የተነጋገርነው። ይሄን ሁሉ አላሟሉም።ገከመፈረሜ በፊት ብዙ ነገር እንደሚያሟሉ ነበር የተነጋገርነው። ከሄድኩ በኃላ ግን የተሟላልኝ ቤት ብቻ ነው። እና በክለቡ ያልቆየሁበት ምክንያት ይሄ ነው።”

በወቅቱ ስሙ ከበርካታ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጋር ተያይዞ የነበረው አስራት ወደ እስራኤል ለመሄድ የወሰነበት ምክንያት እና በመጀመርያው እና ብቸኛው የሀፖይል ኒል ራማት የነጥብ ጨዋታ የገጠመው እንዲህ ያስታውሳል።

“ወደ እስራኤል ለመሄድ የወሰንኩበት ምክንያት የሊጉ ደረጃ ከደቡብ አፍሪካ የተሻለ ስለነበር እና ለተሻለ ዕድል የቀረበ ስለሆነ ነው እንጂ ሁለት ሦስት የሚሆኑ የደቡብ አፍሪካ ቡድኖች ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር። ከነሱ ውስጥ ኦርላንዶ ፓይሬትስ እና ጅሞ ኮስሞስ የሚባሉ ቡድኖች ይገኙበታል።

” በእስራኤል የገጠመኝ ነገር በመጀርያው ጨዋታዬ ቀይ ካርድ ያየሁበት አጋጣሚ ነው። ሊጉ ላይ ያሉ ብዙ ተጫዋቾች አስመስሎ በመውደቅ የተካኑ ናቸው። እኔም ለሊጉ አዲስ እንደመሆኔ በመጀመርያ ጨዋታዬ የነሱ ሰለባ ነበርኩ። በሁለት ቢጫ (ቀይ ካርድ) ነበር የወጣሁት። ሁለቱም ቢጫዎች አስመስለው በመውደቅ ነው ቢጫ ያሰጡኝ፤ ይሄን አጋጣሚ አልረሳውም”

ከእስራኤል መልስ ብዙም ሳይቆይ ለዳሽን ቢራ በመፈረም ቡድኑ እስከፈረሰበት 2008 መጨረሻ ድረስ በዳሽን ቆይታ የነበረው ይህ አማካይ ከዛ በኃላ ለደደቢት እና ወልዋሎ ተጫውቷል። ከጥቂት ወራት በፊት (ሊጉ ከመሰረዙ በፊት) ለስሑል ሽረ ፊርማውን ማኖሩም ይታወሳል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ