ንጉሤ ደስታ በተለያዩ ግለሰቦች አንደበት ..

የቀድሞው ተጫዋች እና አሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ በድንገት ህይወታቸው ካለፈ ሁለት ዓመታት ማስቆጠራቸውን ተከትሎ ቀደም ብለን የእግርኳስ ሐይወታቸውን በአጭሩ ማስቀኘታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ ከአሰልጣኙ ጋር ቅርበት የነበራቸው ግለሰቦች የሰጡት አስተያየት ይዘንላቹ ቀርበናል።

ሚካኤል ዓምደመስቀል (የደደቢት ሥራ አስከያጅ )

በደደቢት ከአሰልጣኝ ንጉሤ ጋር የሰራው ሚካኤል ዓምደመስቀል የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥቷል።

” ንጉሤ ሥራውን የሚያከብር ጥሩ አሰልጣኝ ነበር። ብዙ ዓመታት አብረን ሰርተናል። በነዛ ዓመታት በመጥፎም በጥሩም ጊዜ ንጉሤ ያው ነበር። ሥራውን የሚያስቀድም እና የሚያከብር ቅን ሰው ነበር። እኔ ሥራ አስኪያጅ በነበርኩበት ግዜ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሳልፈናል ፤ ከራሱ ስራ አልፎ የሌሎች ስራዎችም ደርቦ የሚሰራ እና ከተጫዋቾች ጋር ያለው ግንኙነት ደግሞ በጣም የሚገርም ነበር። ብዙ ትላልቅ አሰልጣኞች አውቃለው እንደ ንጉሤ የቡድን መንፈስ ጠብቆ የሚሄድ ቡድኑ እንደ አንድ ሰው እንዲያስብ የሚያደርግ ግን አይቼ አላውቅም። ዋንጫ ባነሳንበት ዓመት የነበረን ነገር በጣም አሪፍ ነበር። ንጉሤ በአጠቃላይ የዋህ፣ ቅን፣ ከማንም ሰው ጋር ተስማምቶ መስራት የሚችልና ሀገሩን የሚወድ አሰልጣኝ ነበር።

“ከሁለት ዓመት በፊት መሞቱን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። መጀመርያ አላመንኩም ነበር። ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ስለ ቀጣይ የቡድናችን ሁኔታ ብዙ ነገር ተወያይተን ነበር። እንደ አጋጣሚ አፋር ከነበረው ስብሰባ እንደመጣሁ ከአርባምንጭ ጋር ላለን ጨዋታ ብዙ ውይይት አድርገን ነበር። ለሊት ደውለው ሲነግሩኝ ማመን አልቻልኩም። ጎተራ ሄጄ እስካየው ምንም አላመንኩም፤ መሞቱን ከሰማሁ በኃላም በጣም ነው ያዘንኩት።

” ሕይወቱ ስላለፈ ሳይሆን በቃ ንጉሤ በጣም ጥሩ ሰው ነበር፤ ሌላው ይቅር ስለ ሳር እንክብካቤ የሚጨነቅ የዋህ ሰው ነበር። የሥራ ከባቢውን በጣም ምቹ ለማድረግ የሚጥር የተጫዋቾች ችግር ከማንም በላይ የሚረዳ ነበር። ከኳስ ውጭም ስለ አጠቃላይ ነገር ጥሩ እውቀት የነበረው ሰው ነበር። ከዛ ውጭ ንጉሤ አረንጓዴ ለም ቦታ ደስ ይለው ነበር። ደብረዘይት ምናምን ስንሄድ ቦታውን ያየውና ሌሎች ቦታዎች በተለይም የትውልድ ቦታው ትግራይ ለምን እንደዚ ለም እንዳልሆነ ሁሌ ይናገር ነበር። በዛ ዙርያም ለመስራት ያስብ ነበር።”

ሥዩም ተስፋዬ (የቀድሞ የደደቢት ተጫዋች)

በአሰልጣኝ ንጉሤ ደስታ ስር በርካታ ዓመታት የሰለጠነው የመስመር ተከላካዩ ሥዩም ተስፋዬም ስለ አሰልጣኙ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል።

” ንጉሤ በጣም መልካም አሰልጣኝ ነበር። ከተጫዋቾች ጋር የነበረው አሪፍ ግንኙነት ማንም ያውቀዋል። ልክ እንደ ቤተሰብ ነበር የሚያቀርበን። ይሄ ደግሞ ያለንን ነገር አውጥተን እንድንጫወት ያደርገን ነበር። አወንታዊ አመለካከት የነበረው ለሁሉም መልካም አሳቢ እና ተግባቢ ነበር። በዚህም ሁሉም ነው የሚወደው። ከጥሩ አሰልጣኝነቱ ባሻገር እንደገለፅኩት ተግባቢ እና የቡድን ሰው ነበር። በግሌ እንደ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ሳይሆን ልክ እንደ ቅርብ ቤተሰብ ጓደኛ ነበር የማወራው፤ ከምልህ በላይ የቅርብ አማካርዬ ነበር። የሆነው ነገር በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ ልብ ይሰብራል። በሜዳ ውስጥም ጥሩ አሰልጣኝ ነበር ከሜዳ ውጭ ከሚያሳየን ነገር የተለየ ነገር አልነበረውም። በዛ ምክንያት ሜዳ ውስጥ ያለው ሁሉም ይታገልለታል። ያለህን ነገር አውጥተህ በወኔ እንድትጫወት ያደርግሀል። በሜዳም ከሜዳ ውጭም ከራሱ ይልቅ ለተጫዋች ይቆማል።

“መሞቱን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። አሞኛል ብሎ አንድ ልምምድ ቀረ ፤ ህመም እንደተሰማው አላወቅንም እኛ በግል ጉዳይ የቀረ ነበር የመሰለን። ለሊት ደውለው ሲነግሩኝ ምንም አላመንኩም። ምክንያቱ መታመሙን ራሱ አልሰማሁም። ልክ እንደተደወለልን ከብርሀኑ ቦጋለ (ፋዲጋ) ጋር ወደ ቦታው ሄድን ቦታው እስክደርስ ውስጤ አላመነም ነበር። ሁላችንም ልባችን ነበር የተሰበረው አሰልጣኛችን ብቻ አልነበረም አባታችንም ጭምር ነበር። ያሁሉ የቤተሰብ ስሜት ያሁሉ መቀራረባችን በዚ መንገድ ሲቋጭ ልብ ይሰብራል። ”

ዳንኤል አስመላሽ (ስፖርት ጋዜጠኛ)

ከአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የረጅም ጊዜ ቀረቤታ የነበረው አንጋፋው የትግርኛ የስፖርት ጋዜጠኛ ዳንኤል አስመላሽም ስለ ንጉሤ ይህን ብሏል።

” ንጉሤ በጣም ቅን ሰው ነበር። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አሰልጣኞች ከሚታሙበት ስርዓት የሌለው የደላሎች ግንኙነት ውስጥ እጁ የሌለበት ሞያውን የሚያከብር አሰልጣኝ ነበር። ለእግርኳስ የሚለፋ ትጉህ ሠራተኛ ነበር። ይህ እኔ ብቻ ሳልሆን በሱ ስር የሰለጠኑ ተጫዋቾችም የሚመሰክሩት ነገር ነው። ሌላው ንጉሤ የሚገባውን ክብር ያላገኘ (Under rated)፣ ለእግርኳሱ ያለውን ነገር ሁሉ የሚሰጥ አሰልጣኝ ነበር። የሊጉ ጥሩ አሰልጣኞች ስም ሲጠቀስ የሱ ስም አይጠቀስም፤ ከሰራው ስራ አንፃር ስንሄድ ግን ከማንም የማይተናነስ ነገር አበርክቷል። ከደደቢት ጋር የሀገሪቱ ሁለት ታላላቅ ዋንጫዎች አሳክቷል። በወልዲያ የሁለት ዓመት ቆይታው ያሳካው ነገር አስደናቂ ነው፤ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድጎ በመጀመርያ ዓመት የሊጉ ቆይታም በትንሽ በጀት የሰራው ቡድን በጣም ጥሩ ነበር።

” በተጫዋችነት ጊዜውም ጥሩ ተጫዋች ነበር። ተጫዋች እያለ በቅርበት ባላውቀውም በስራ አጋጣሚ ከሱ ጋር የሰሩ ስጠይቅ ሁሉም በጎ መልስ ነው የሚሰጡኝ። በአስራ ስድስተኛ ክፍለጦር እና በመቻል ጥሩ ጊዜ ነበረው። በአሰልጣኝነት ጊዜውም በወጣቶች የሚያምን ነበር። እውነተኛ ሙያውን የሚያከብር እና እዚም እዛም የማይገኝ ለሞያው ስነ-ምግባር ታማኝ የነበረ ሰው ነው። ለዛም ነው በስሩ የሰለጠኑ ተጫዋች ከሱ ጋር የሰሩ ባለሞያዎች ስሙን በጥሩ የሚያነሱት።

” ከእግር ኳስ ውጭ ባለው ሕይወቱም ቅንና ጨዋታ አዋቂ ነበር። መቐለ ሲመጣ በቅርብ ለምናውቀው ሰዎች ሰብስቦ ያገኘን ነበር ፤ ከሰው ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም ሰላማዊ ነበር። ነገሮች ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚወድ ሰው ነበር። እንደውም እሱ ነገር ብዙ ጊዜ አስቀጥቶታል። ይህም ፊት ለፊት መጋፈጡ ያመጣው ነገር ነው። ”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ