በአንድ ወቅት በድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ቆይታ የነበረው ታዲዮስ ወልዴ የት ይገኛል?
በፕሪምየር ሊጉ ለበርካታ ክለቦች ተጫውቷል። የእግርኳስ ሕይወቱን በድሬዳዋው ጨርቃ ጨርቅ የታዳጊዎች ፕሮጀክት ጀምሮ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በማምራት ቡድኑ በ2001 ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ጥሩ አስተዋጽኦ የነበረው አማካዩ ከብርቱካናማዎቹ ጋር ቆይታ ካደረገ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ ወዳደረገበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምርቶ ከክለቡ ጋር የአምስት ዓመታት ቆይታ አድርጓል።
ከንግድ ባንክ በኃላ ከአርባምንጭ እና ወላይታ ድቻ ጋር አጫጭር ቆይታዎች ያደረገው ታዲዮስ ባለፈው የውድድር ዓመት መጀመርያ ወደ ባህርዳር ከተማ አምርቶ ከክለቡ ጋር ያልተሳካ ጊዜ ካሳለፈ በኃላ ላለፉት ስምንት ወራት ከእግርኳሱ ርቆ ቆይቷል። አማካዩ ከእግር ኳስ የራቀበት ምክንያት እንዲህ ይገልፃል። “ዋነኛ ምክንያቴ በቤተሰብ ችግር ነው፤ ከአንዳንድ ክለቦች ጥያቄ ቀርበውልኝ ነበር። ሆኖም በጊዜው ከቤተሰብ ርቄ መኖር የማልችልበት ምክንያት ነበር። ያም ሆኖ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ከመድን ጋር ልምምድ ጀምሬ ነበር ” ይላል።
አማካዩ በአንድ ወቅት ከወልዋሎ ጋር ልምምድ ጀምሮ ዝውውሩ ያተጠናቀቀበት ምክንያት እና ስለባህርዳር ቆይታው እንዲህ ይላል። ” እሱ አንዳንድ መጥቀስ የማልፈልጋቸው ችግሮች ነበሩ። ሌላው ደግሞ የማልጫወት ከሆነ ለምን እቆያለው ብዬ ነው በራሴ ፍላጎት ክለቡን የለቀቅኩት። እንደኔ ሳትጫወት ቁጭ ብለህ ደሞዝ መቀበል አልደግፈውም፤ በዛ ሰዓት ደግሞ ከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝ ነው ክለቡ የለቀቅኩት። አሁን ሆኜ ሳስበው ብዙ አማራጭ እያሉኝ ወደዛ ሄጄ መፈረሜ ትክክለኛ ውሳኔ አልነበረም። የወልዋሎ ዝውውር ያልተጠናቀቀበት ምክንያት ደግሞ ከሜዳው ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነበር። ከክለቡ ጋር ለአንድ ሳምንት ልምምድ ጀምሬ ነበር። ከዛ በኃላ ግን እግሬ ላይ የሆነ የህመም ስሜት ስለነበረኝ በዛ ሜዳ መጫወት ይከብደኛል ብዬ ነው ያንን ውሳኔ የወሰንኩት። በዛ ሰዓት ሜዳው ሳር አልነበረም። እሱም ለጉዳት ያጋልጣል ከነበረኝ የህመም ስሜትም ትክክለኛ ውሳኔ ነው የወሰንኩት” ብሏል።
ታዲዮስ አሁን ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታም እንደዚ ይገልፀዋል። “ጠዋት በግል ስፖርት እሰራለሁ። ከዛ ውጭ አብዛኛው ጊዜዬን ከቤተሰቦቼ እና ከልጄ ጋር ነው የማሳልፈው። በቀጣይ ራሴን አሻሽዬ ወደ እግር ኳስ ለመመለስ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው። ፈጣሪ ፈቅዶ በሽታው ይጥፋ እንጂ ወደ የምወደው እግር ኳስ እመለሳለሁ።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ