የሴቶች ገፅ | ከእግርኳስ ተጫዋችነት እስከ ህክምና ባለሙያነት…

የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጎል ያስቆጠረችውና እና በአሁኑ ሰዓት የህክምና ባለሙያ በመሆን እያገለገለች ያለችው የዶ/ር እንደገናዓለም አዋሶ አስገራሚ የህይወት ጉዞ።

ውልደት እና እድገቷ አዳማ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበሌ 09 በሚባል ስፍራ ላይ ነው። ከልጅነቷ ጀምሮ እግርኳስ ለመጫወት ብዙ ፈተናዎችን አልፋ እንደነበረ የምትናገረው እንደገናዓለም በተለይ እንደማንኛውም ታዳጊ ልጅ በሰፈር ውስጥ ኳስ ለመጫወት ስትፈልግ በፆታዋ ምክንያት ትከለከል እንደነበረ ታስታውሳለች። በተለይ ባደገችበት አካባቢ እንደእርሷ ኳስን የምትወድ እንስት ስላልነበረች ብቻዋን ከወንዶች ጋር ተጋፍጣ የምትወደውን ኳስ ለመጫወት ትሞክር ነበር። እየለመነች ኳስ ከወንዶች ጋር በሰፈር በምትጫወትበት ጊዜ ግን አንድ የህይወቷን መስመር ያስተካከለ መልዕክት ዋሲሁን ከተባለ የሰፈሯ ልጅ ይደርሳታል። “ዋሲሁን ለእኔ ትልቅ ነገር አድርጎልኛል። ሰፈሬ ውስጥ ከወንዶች ጋር በመከራ እየተጫወትኩ ባለሁበት ጊዜ መጥቶ ‘ስታዲየም አካባቢ አሰልጣኝ አለማየሁ ለማ የሚያሰለጥነው የሴቶች ቡድን አለ። እዛ ልውሰድሽ’ ብሎ መልካም ብስራት አበሰረኝ። እኔም ሳላንገራግር በደስታ ወደዛ ሄድኩኝ። በጊዜው በጣም ከፍተኛ ደስታ ነበር የተሰማኝ። ምክንያቱም ከእኔ አምሳያዎች ጋር ለመጫወት እና ለመስራት እድሉን ስላገኘሁ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ወንዶቹንም ሳልለማመጥ ዓለማየሁ ጋር እየመጣሁ መሰልጠን ጀመርኩ።”

ለበርካታ ዓመታት በሴቶች እግርኳስ ላይ ባሳለፈው አሰልጣኝ ዓለማየሁ መሰልጠን የጀመረችው እንደገናዓለም አሁንም ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላትም። በተለይ ወላጅ አባቷ ልምምድ ሰርታ እና ጨዋታ አድርጋ ወደቤት በምትመጣበት ጊዜ ከፍተኛ ተግሳፅ እንደሚያደርስባት ታወሳለች። ይህ ያልበገራት እንደገና ግን እንደምንም ከቤተሰብ እና ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡትን ጫናዎች ተቋቁማ ጉዞዋን ቀጥላለች። በዚሁ ቡድን ብቃቷን እያጎለበተች የመጣችው ተጨዋቿ ቀስ በቀስ የወረዳ፣ የዞን እና የክልል ውድድሮች ላይ የመሳተፉን እድል ማግኘት ጀመረች። በውድድሮቹም ላይ ተጨዋቿ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ስኬታማ ጊዜያትን አሳለፈች። “በሦስቱም ውድድሮች (በዞን፣ በወረዳ እና በክልል ደረጃ) በጣም ስኬታማ ጊዜያት ነበረኝ። እኔ በግሌ ብቻ ሳልሆን ቡድናችንም በጣም ጥሩ ነበረ። በግሌ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ነበር ውድድሮቹን ያጠናቀኩት። በክልል ደረጃ በምጫወትበት ጊዜ ባሳየሁትም አቋም ደግሞ ለብሔራዊ ቡድን ተመረጥኩ።”

ክልሏን ወክላ ድንቅ እንቅስቃሴን በማድረጓ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እንድትካተት የሆነችው ተጫዋቿ ከውድድሩ በፊት ግን እድገቷን የሚከታተል ሰው እንደነበረ ትናገራለች። ” ስታዲየም አካባቢ ልምምድ ስንሰራ የጊዜው የሙገር አሰልጣኝ የነበሩት አቶ አዳነ ይከታተሉኝ ነበር። እንደውም አንድ ጊዜ ‘ሴቶችን ከወንዶች ጋር አደባልቆ መጫወት ቢቻል እወስድሽ ነበር’ ብለውኝ ነበር። በወቅቱ ሙገርም እኛው አካባቢ ስለነበረ በየጊዜው ልምምድ ቦታ እየመጡ ያበረታቱኝ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሲመሰረት አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት እሳቸው ነበሩ (ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በጋራ)።”

በአሰልጣኝ አዳነ የረጅም ጊዜ እይታ ውስጥ የነበረችው እንደገና በክልል ውድድር ባሳየችው ምርጥ ብቃት አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተመርጣ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀመረች። ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ለሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች የተዋቀረው ብሄራዊ ቡድኑም ከዩጋንዳ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ጨዋታውን በደርሶ መልስ አደረገ። እንደገናም በጨዋታው ጎል አስቆጥራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጎብ አስቆጣሪ በመባል የታሪክ መዝገብ ላይ ስሟን አሰፈረች።

“እርግጥ ከዩጋንዳው ጨዋታ በፊት በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደረጃ አንድ ጨዋታ ከሶማሊያ ጋር ወንጂ ላይ አከናውነናል። ነገርግን ጨዋታው ይፋዊ ወዳጅነት ስላልነበረ የሚመዘገብ አይደለም። በይፋ ግን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ግጥሚያ ያደረገው ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረግ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ነው። ግጥሚያው ወንጂ ላይ ነበር የተደረገው። ጨዋታው በጣም ስሜታዊ አድርጎኝ ነበር። ምክንያቱም የመጀመሪያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ስለነበር። እውነት ለመናገር ግን እኔ ብቻ አይደለም ስሜታዊ የሆንኩት። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ውጥረት ተሰምቷቸው ነበር። ነገር ግን እንደምንም ተረጋግተን ጨዋታውን አደረግን። በጨዋታው ቡድኔም ሆነ እኔ ጥሩ ብቃት አሳየን። እኔም የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጎል አስቆጥሬ ጨዋታውን አሸንፍን። በሰዓቱ ጎል ሳስቆጥር ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር።”

አሰልጣኝ አዳነ ትልቅ ባለውለታዋ እንደነበሩ የምትናገረው ተጨዋቿ እስከ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ስትጫወት ግን የቀለም ትምህርቷን አልዘነጋችም ነበር። እንደውም የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ እያደረገች የ12ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና ወስዳ ነበር። በማትሪኩም አምርቂ ውጤት በማምጣት ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድሉ አጋጥሟት ፊቷን እና ትኩረቷን ወደ ትምህርት ዓለም ለማዞር ተገደደች። በጅማ ዩኒቨርስቲም በኢንቫሮመንታል ሄልዝ ትምህርት ጥሩ ውጤት በማምጣት ከተመረቀች በኋላ ዳግም ወደ እግርኳሱ ተመለሰች። እንደገናዓለም ከጅማ ዩኒቨርስቲ ተመርቃ ከወጣች በኋላ ግን ወደ አዲስ አበባ ነበር የመጣችው። በወቅቱ አለቤ-ሾው በተባለው ክለብ ተጨዋቾችን እያስጠናች እንድትጫወት ድርብ ኃላፊነት ተሰጥቷት ስራ ጀመረች። የቡድን አጋሮቿን ትምህርት እያስጠናች እግርኳስን በአለቤ ክለብ ውስጥ የቀጠለችው ተጫዋቿ ከአንድ ዓመት ከግማሽ በኋላ ደግሞ የስኮላርሺፕ እድል አግኝታ ትምህርቷን ለመቀጠል ወደ ኩባ ሃገር አመራች። በኩባም ለ6 ዓመታት የጥርስ ህክምናን (ዴንታል ሰርጅን) በዶክትሬት ደረጃ በማጥናት የቀለም እውቀቷን አጎልብታ ዳግም ወደ ሃገሯ ተመለሰች።

ከ6 ዓመታት በኋላም የእግርኳስ ፍቅሯ ያልቀዘቀዘባት እንደገና በድጋሚ ወደ እግርኳስ ህይወት ተመለሰች። ” ከኩባ ከተመለስኩ በኋላም የመጫወት ፍቅሬ አልቀዘቀዘም ነበር። ውስጤ እግርኳስን እንዳልጠገብኩ ይነግረኝ ነበር። በተለይ የመጫወት ፍላጎት እና አቅም በነበረኝ ሰዓት በደንብ ስላልተጫወትኩ ከኩባም ከተመለስኩ በኋላ መጫወት እንድፈልግ አደረገኝ። በመጀመሪያም ቢሆን እግርኳስን ጠልቼ እና ገፍቼ አይደለም ወደ ትምህርቴ ያዘነበልኩት። ለረጅም ጊዜ የምቆይበትን የሥራ ህይወት ከማስቀደም ጋር በተያያዘ እንጂ። አንዳንዴ የምትወደውን ነገር ሳትፈልግ ተሰዋለክ። እኔ ጋርም የሆነው ይህ ነው። በተለይ ደግሞ የኩባው የትምህርት እድል ካመለጠኝ መልሼ እንደማላገኘው ስለተረዳሁ ስሜቴን ገድቤ ወደእዛ አቀናሁ። ከኩባ ከተመለስኩ በኋላ ግን ወደ እግርኳስ የመለሰኝ ስሜቴ ብቻ አልነበረም። ለሴቶች እህቶቼ ትምህርት መሆን ስለፈለኩም ነው። በትምህርት ትልቅ ደረጃ ተደርሶም እግርኳስ መጫወት እንደሚቻል ለማሳየት ነው የምጫወትበት ክለብ የፈለግኩት። እንደመጣሁም ከአሰልጣኝ ሠላም ጋር ተነጋግሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ልምምድ ጀምሬ ነበር። ነገር ግን ወደ ትውልድ ሃገሬ አዳማ የምጫወትበትን እድል ሳገኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረኝን ነገር አቁሜ ወደ አዳማ መጣሁ። ለአዳማም ከ2006 ጀምሮ እስከ 2010 ድረስ ዶክትሬቴን ይዤ መጫወት ቻልኩ።”

በአዳማ ከተማ እየተጫወተች ህክምና መሰጠቷን ስትቀጥል የነበረችው ይህች አጥቂ ከሁለት ዓመታት በፊት ግን ጫማዋን ሰቅላ የህክምና ጋውን ሙሉ ለሙሉ ማጥለቅን በመምረጥ እግርኳስን ተሰናበተች። ምንም እንኳን እንደገና እግርኳስን በተጫዋችነት ብትሰናበትም በአሰልጣኝነት ወደፊት ብቅ ለማለት ሃሳብ እንዳላት ትናገራለች። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የሲ ላይሰንስ (C licence) የአሰልጣኝነት ስልጠናም ወስዳለች። በአሁኑ ሰዓት ግን በዋናነት በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ስራዋን እየሰራች ትገኛለች። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የህክምና ማህበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የውድድር ኮሚቴ ውስጥ አባል በመሆን ለእግርኳሱ ግልጋሎት እየሰጠች ትገኛለች።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ