አሳዛኙ የዕዳጋ ሐሙስ አደጋ – ትውስታ በሲሳይ አብርሀም አንደበት

በአሳዛኝ አጋጣሚ የተደመደመው የአዳማ ከተማ የደስታ ቀን

በ 2003 ካጋጠሙት እና የማይረሱ አጋጣሚዎች አንዱ የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በትግራይ ዕዳጋ ሐሙስ በምትባል ከተማ ያጋጠመው አስደንጋጭ የመኪና አደጋ አንዱ ነው። ታኅሣሥ 24 ቀን 2003 በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ትራንስ ኢትዮጵያን ለመግጠም ወደ ዓዲግራት አምርቶ ጨዋታውንም 2-0 አሸንፎ በመመለስ ላይ እያለ ያጋጠመው ይህ አደጋ ሁለት የቡድኑ አባላት ላይ የሞት አደጋ ሲያስከትል ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾች እና ዋና አሰልጣኙ ሲሳይ አብርሀምም ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግደዋል። የዛሬው ትውስታ ዓምዳችን እንግዳ የሆነው አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀምም በወቅቱ የደረሰው አደጋን እንዲህ ያስታውሳል።

” በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፤ ጨዋታውን አሸንፈን በልዩ የደስታ ስሜት ላይ ነበርን። ሙሉ ቡድኑ ደስታ ላይ ነበር። አሁን ሆኜ ሳስበው ማደር ነበረብን፤ ግን ነብሱን ይማረው እና መሐመድ ዴሌሞ መሄድ አለብን አለ። ከወቅቱ ፕሬዝዳንታችን ጋር ተነጋገሩና ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለመሄድ ተወሰነ። መንገድ ስንጀምር ትንሽ ለዓይን ያዝ አድርጎ ነበር። ሹፌሩ ደግሞ በጣም ይፈጥናል። ተጫዋቾች ደጋግመው ቀስ በል ይሉት ነበር። እኔም ቀስ ብሎ እንዲነዳ ደጋግሜ ጠይቄው ነበር። በዚ መሀል እኔ ፊት ስለነበርኩ ወደ ኃላ ቦታ ቀየርኩ። መንገዱ አስቸጋሪ ነበር፤ ጨለምለም ብሏል። በዛላይ ሹፌሩ ቀስ ብለህ ንዳ ብንለው አልሰማ አለን። እኛ ብቻ ሳንሆን ፕሬዝዳንታችንም ከኃላችን በመኪና እየተከታተለን ስለነበር ካንዴም ሁለቴ ቀስ ብለህ ንዳ ብሎ አስጠንቅቆት ነበር። በዛ ላይ ከብዙ ሽንፈት በኃላ ያገኘነው ድል ስለነበር ደስታችን ልዩ ነበር ጥሩ ቀን ነበር ያሳለፍነው፤ መጨረሻው ግን አላማረም።

“ከዛ በኃላ ወደ ዕዳጋ ሐሙስ አካባቢ ስንደርስ አደጋው አጋጠመ። እኔ ራሴን አላውቅም ነበር፤ መስተዋት ሰብረው ነው ያወጡኝ። ከአስር በላይ አባላት ጉዳት ደረሰብን። ደረጄ የሚባል ታዳጊ እና ቡድን መሪያችን መሐመድ ዴሌሞን ደግሞ በሞት አጣናቸው። ከባድ ሌሊት ነበር። ህዝቡ በጣም ነበር የተባበረን፤ በዛን ሰዓት ህፃን ብትል ባለስልጣን ብትል ሁሉም ሆስፒታል ድረስ መጥቶ አበረታቶናል።

” ጉዳቴ ትንሽ ከበድ ይል ነበር፤ ከዛ ወደ አዳማ ሄድን። ሰመረዲን ከሚባል ሌላ የቡድኑ አባል ጋር ኃ/ማርያም ማሞ ሆስፒታል ገባን። እዛም ብዙም አልቆየንም ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሪፈር አሉን። ጥቁር አምበሳ ከሁለት ወር በላይ አልጋ ይዤ ቆየሁ። ”

ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ህክምና ያላገኘው ሲሳይ የግድ ወደ ውጭ ወጥቶ መታከም እንዳለበት ይነገረዋል። ጉዳቱ ከባድ እንደነበር እና ብዙ ጊዜ እንደፈጀ ገልጾ ወደ ውጭ ሄዶ እንዲታከም የተባበሩት አካላትን በማመስገን በታይላንድ የነበረው ቆይታ እንዲህ ያስታውሰዋል።

” ጥሩ ህክምና ለማግኘት የግድ ውጭ ሄጄ መታከም እንዳለብኝ ተነገረኝ። ገዛኸኝ ለማ የሚባል የክለባችን ፅሐፊ ጋሽ አብነት ገ/መስቀል ድጋፍ እንዲያደርጉልን ይጠይቅና ጋሽ አብነትም ድጋፍ እንደሚያደርግልን ቃል ገቡ። በዛ ሰዓት አሜሪካ ነበሩ፤ ከተመለሱ በኃላ ቃል በገቡት መሰረት ለህክምና ወደ ታይላንድ ላኩኝ። ይሄ የሆነው በሦስተኛው ወራችን ነበር፤ በጣም ከባድ ግዜ ነበር። ታይላንድ ሄጄ ወደ አምስት ሰዓት የሚጠጋ ቀዶ ጥገና አደረጉልኝ ጥሩ ህክምና አገኘሁ። ትልቅ ቀዶ ጥገና ስለተደረገልኝም ብዙ ማረፍ ነበረብኝ። ቶሎ ጥሩ ህክምና ባላገኝ ፓራላይዝድ እሆን እንደነበር ነው ዶክተሮቹ የነገሩኝ። እዛ ሄጄም አንድ ወር ሆስፒታል ነበርኩ። የተቀረው ሦስት ወራት ደግሞ ተጨማሪ ህክምና እየወሰድኩ ሆቴል ነበርኩ ከአራት ወራት በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ ትንሽ ጊዜም ቤቴ ቆየሁ። እንዲ እያለ ዓመቱ ተጠናቀቀ።”

በቂ ህክምና ካገኘ በኃላ ቶሎ ወደ ስራ ለመግባት ጉጉት እንደነበረው የሚናገረው ሲሳይ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ወደ እግር ኳስ ተመልሶ አዳማ ከተማን ተረከበ። ሆኖም የመጀመርያው ዙር ተጠናቆ በመጀመርያው ሳምንታት አከባቢ ቡድኑ በጥሩ ሁኔታ እያለ ሳይጠበቅ ክለቡን እንደለቀቀ እንዲህ ያስረዳል።

” ከሼር ኢትዮጵያ የተሻለ ጥሩ ክፍያ ቀረበልኝ። በዛ ምክንያት ነው አዳማን የለቀቅኩት፤ በዚህም የአዳማ ከተማ አመራሮች ይጠቀም በሚል ብዙ ትብብር አድርገውልኛል። የሁለት ዓመት ቀሪ ውል እያለኝ ነው በስምምነት የለቀቁኝ። ከአዳማ የተለያየሁበት ምክንያት ይሄ ነው፤ በሼር ኢትዮጵያ ጥሩ ቆይታ ካደረግኩ በኃላም በሰበታ ለጥቂት ግዜ ሰርቻለው። በሀያ ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንም የግርማ ሀ/ዮሐንስ ምክትል ሆኜ ሰርቻለው። ከዛ በኃላም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ከአክሱም ከተማ ጋር ቆይቻለው። ባለፈው ዓመት ደግሞ በድጋሜ አዳማ ከተማን አሰልጥኛለው። በዚ አጋጣሚ በ2004 መጨረሻ ለጥቂት ግዜ አዳማን አሰልጥኛለው። ቡድኑ ላለመውረድ እየተጫወተ ሁለት ጨዋታ ቀርተውት ከመከላከያ እና መብራት ኃይል መጫወት ነበረበት። ከዛ መብራት ኃይልን አሸንፈን በሊጉ መቆየት ችለናል።

በመጨረሻም አሰልጣኙ ባለውለተኞቹን አመስግኗል። ” ጋሽ አብነት ገብረመስቀልን በጣም አመሰግናለሁ፤ ብዙ ድጋፍ አድርገውልናል። ጊዮርጊስ ለአዳማ ከተማ ቤተሰብ ነው። ጋሽ ገዛኸኝ ለማም በጣም አመሰግነዋለው፤ ብዙ ነገር አግዞኛል። እሱ ባይኖር የድጋፍ መንገዶቹ ከባድ ይሆኑ ነበር። ጊዮርጊሶች ነብሱን ይማረው ሞገስ ታደሰ፣ አማኑኤል ግደይ እና መሐመድ ናስርን ሰጥተውን ነበር። በተጨማሪም ደሞዛቸውን ጭምር ነበር የሸፈኑልን። ኢትዮጵያ ቡናም ኢብራሂም ሑሴንን ሰጥቶን ነበር፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ቡናን አመሰግናለው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ትልቅ እገዛ ነው ያደረገልን። በወቅቱ ሊጉን አራዘሞልናል። እና በዛን ሰዓት ለተባበሩኝ በጣም አመሰግናለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ