ስለ እስማኤል አቡበከር (ዊሀ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

በተለያዩ ምክንያቶች እንደነበረው አቅም እና ችሎታ በአንድ ክለብ ውስጥ የተረጋጋ ቆይታ ማድረግ ሳይችል የእግርኳስ ህይወቱን የመራው የዘጠናዎቹ ኮከብ ፈጣኑ አጥቂ የአሁኑ አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር (ዊሀ) ማነው?

ግልፅ መናገሩ በእግርኳስ ህይወቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳደረሰበት የሚገልፀው እስማኤል አቡበከር ትውልድ እና ዕድገቱ ልደታ ሠፈር “ቤሪሞ” ሜዳ አካባቢ ነው። በአባቱ ናይጄርያዊ፣ በእናቱ ኢትዮጵያዊ ነው። እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ ተወልዶ ባደገበት ሜዳ እግርኳስን መጫወት የጀመረው እስማኤል በ1988 ሙገር ቢ በመግባት የክለብ ህይወቱን ጀምሯል። ወደ ዋና ቡድን በማደግ ለሁለት ዓመት ቆይታውን አጠናቆ በ1990 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢያመራም በጉዳት ምክንያት የተፈለገውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጥ ብዙም ሳይቆይ ከወራት ቆይታ በኃላ ከፈረሰኞቹ ጋር ተለያይቷል። ቀልጣፋና፣ ፈጣን፣ በጉልበቱ እንደሚጫወት እና የአጨራረስ ብቃቱ ጥሩ እንደሆነ የሚነገርለት እስማኤል ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ተገዶ በታችኛው ዲቪዚዮን ለሚጫወተው ኪራይ ቤት ወርዶ ለአንድ ዓመት በመጫወት የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ፉክክር ውስጥ በመግባት ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ወጣት ቡድን መመረጡ ወደ ተሻለ ክለብ እንዲሄድ እድሉን ከፍቶለት በ1992 በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፈው የአሰልጣኝ መንግስቱ ወርቁ መድንን ሊቀላቀል ችሏል።

አንዳንዴ በግልፅ የተሰማውን ስሜት ፊት ለፊት መናገሩ የማይወደድለት በመሆኑ ያልተረጋጋ የእግርኳስ ህይወት እንዲያሳልፍ ያገደው እስማኤል ከመድን በኃላ ወደ ውጪ ሄዶ የመጫወት እድል አግኝቶ ወደ ሞቃታማዋ የሩቅ ምሥራቅ ሀገር ኦማን ቢሄድም ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት የቀዶ ጥገና ህክምና በማድረግ ወደ ሀገሩ በመመለስ በድጋሚ በ1993 ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሏል። በአመዛኙ ጊዜ ማለት ይቻላል ለፈረሰኞቹ ሳይጫወት ለወጣት ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ወደ አርጀንቲና ሊያመራ ቢችልም ወደ አሜሪካ ለመግባት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ እርሱን ጨምሮ ሰለሞን እና ሁሴን ሰማን በመሆን ለአንድ ዓመት ለአንድ ወር በአርጀንቲና በመጥፋታቸው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ሊርቅ ችሏል።

አርጀንቲና የስደደት ህይወት የከበደው እስማኤል በቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ ሰብሳቢ በአቶ አብነት ገብረ መስቀል መልካም ትብብር የአውሮፕላን ትኬት ተልኮለት ወደ ሀገሩ ተመልሶ በ1995–96 ድረስ ለቅዱስ ጊዮርጊስን በድጋሚ መጫወት ቢችልም ቡድኑ ውስጥ በነበሩት ጠንካራ ተጫዋቾች እና በወቅቱ የነበረው አሰልጣኝ ቡድን በሚመራበት መንገድ ደስተኛ ባለመሆን በቂ የመሠለፍ እድል ሳያገኝ በመቅረቱ የ1995 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ብቻ አሳክቶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በመለያየት 1997–99 ድረስ በተከታታይ ዓመታት ለወንጂ ስኳር፣ መከላከያ፣ ጥቁር አባይ በመቀጠል ወደ የመን በመሄድ ከተጫወተ በኃላ በትዳር ህይወቱ ላይ ባጋጠመው ፍቺ ምክንያት አይምሮው ሊረጋጋ ባለመቻሉ ለተወሰኑ ወራት እግርኳስን ካቆመ በኃላ በአስራ አራት ዓመት የእግርኳስ ህይወቱ ውስጥ ሊጠቀስ በሚችል ሁኔታ በተወሰነ መልኩ የተረጋጋ ጊዜ አሳልፏል ወደሚባልበት ሀዋሳ ከተማ አምርቶ ከ2000 እስከ 2002 ለሦስት ዓመት በተለየ ሚና በአማካይነት በመጫወት መልካም የውድድር ዘመናትን አሳልፏል። በመጨረሻም የእግርኳስ ህይወቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ወደ መጠናቀቂያው ደርሶ ለሁለት ዓመት ለኢትዮ ኤሌትሪክን በመቀላቀል ከተጫወተ በኃላ በ2004 ራሱን ከእግርኳስ አርቋል።

በብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው እስማኤል ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት በሠፈር ውስጥ የፕሮጀክት ቡድን በማሰልጠን ጀምሮ አድርጎ በሐረር ሲቲ ታዳጊ ቡድን ሠርቷል። ይልቁንም አበቡበከር ናስር፣ ሚኪያስ መኮንን እና ሌሎችም ተጫዋቾች በእርሱ ሥር የመሰልጠን ዕድል ያገኙ የዘመኑ ኮከቦች ናቸው። በመቀጠል ያለፉትን ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ም/አሰልጣኝ በመሆን እየሰራ ይገኛል። በተለያዩ ምክንያቶች እንደነበረው አቅም እና ችሎታ በአንድ ክለብ ውስጥ የተረጋጋ ቆይታ ማድረግ ሳይችል የተመሰቃቀለ የእግርኳስ ህይወት ያሳለፈው የቀድሞ የዘጠናዎቹ ኮከብ ፈጣኑ አጥቂ የአሁኑ አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጋር ያደረግነው ቆይታ ይሄን ይመስላል።

“ያልተረጋጋው የእግርኳስ ህይወቴ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም ግልፅ በመሆኔ የደረሰብኝ ተፅዕኖ አለ። እሱም ብቻ ሳይሄን እኔ በባህሪዬ ብቻዬን መቆም አለብኝ ብዬ የማስብ ሰው ነኝ ፤ ደጋፊ የሌለኝ ሰው ነኝ። ሁልጊዜም በራሴ የምተማመን ሰው መሆን እፈልግ ነበር። ስለ እኔ መናገር ያለብኝ ራሴ ብቻ ነኝ ብዬ የማምነው እንዲሁም በእኔ በኩል የሚመጡ ማንኛውንም ነገሮች ራሴን ችዬ ኃላፊነትም እወስዳለው። ነገር ግን በእግር ኳስ ዘመኔ በአሰልጣኝ ህይወት ውስጥ አንዴም ገብቼ አላውቅም። ክለቡ እስከቀጠረው ድረስ የዛን ሰው ስልጣን እና ኃላፊነት የማከብር ሰው ነኝ። ነገር ግን በወቅቱ አንዳንድ በራስ መተማመን ያልነበራቸው አሰልጣኞች ነበሩ፤ ዝም በማለቴ ብቻ የሚረበሹ። እና በዛ በዛ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ተረጋግቼ መጫወት አቅሜን አውጥቼ መጠቀም አልቻልኩም።

” አርጀንቲና ለመጥፋት የፈለግነው ዋና ዓላማችን በብራዚል አድርገን አሜሪካ ለመግባት ነበር። ከኢትዮጵያ ውጭ የመጫወት ወይም ፕሮፌሽናል የተጫዋቾች ኤጀንት በመሆን ኢትዮጵያውን ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው እንዲጫወቱ እድል ለማመቻቸት በጣም እናስብ ነበር፤ ምንም እንኳ ሀሳባችን ባይሳካም። ወደ ቦነስ አይረስ በመምጣት ጥሩ የሚባል ጊዜ አሳልፈናል። እዛ በነበረኝ አንድ ዓመት ከአንድ ወር ቆይታ የማይፀፅተኝ በእግርኳሱ ብዙ እውቀት ያገኘሁበት ጊዜ አሳልፌያለው። እንዲያውም ሳልታ ላይ ከሦስት ቡድኖች ጋር ብሔራዊ ቡድናችን የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ ነበር። እነዚህ ክለቦች ሊወስዱን ፈልገው የነበረ ቢሆንም የመኖርያ ፍቃድ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል። የሚገርምህ በአርጀቲና እግርኳስ ማኅበር ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ያደገ አንድ አርጀንቲናዊ ሰው ነበር። እና በፌዴሬሽኑ የሚመራ ጂምናዚየም ውስጥ ካሉ ዶክተሮች ጋር አገናኝቶን የአካል ብቃታችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን እየሰራን ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን ነበር። እየቆየን ስንሄድ የበለጠ በዚሁ ሀገር ፍቃድ እናገኛለን እንጫወታለን ብንልም ሳይሳካ ወደ ሀገራችን ተመልሰናል። ወደ ሀገሬም እንድመለስ ከፍተኛውን ውለታ የዋሉልኝ አቶ አብነት ገብረመስቀልን በዚሁ አጋጣሚ አመሰግናለው።

” በእግር ኳስ ህይወቴ አላሳካውትም የምለው እና የሚቆጨኝ ብዙ ነገሮች አሉ። ሌሎች ሀገሮች በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ ላይ ሲካፈሉ ሳይ፤ እንደገና አሁን እግር ኳሱ በጣም ያደገበት ጊዜ በመሆኑ ወጣት ሆኜ ይሄን አለማድረጌ ይቆጨኛል። በጊዜው ምንም አይመስልም ነበር፤ ካለፈ በኋላ ግን ይቆጭሀል። አሀን ላሉ ተጫዋቾች የምመክረው ነገር ቢኖር የመስራት ባህላቸውን ካዳበሩ እና ከእነዚህ አርቴፊሻል ከሆኑ ነገሮች ከራቁ ለምሳሌ አሉባልታ እና ጥርጣሬን ካስወገዱ መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ ላይ ይደርሳሉ ብዬ አምናለው ። እነዚህ ነገሮች ናቸው ተጫዋችን ወደኋላ የሚያስቀሩት። ከአጉል መካሪ፣ ደጋፊ እና ጭብጨባ መታቀብ አለባቸው። እግር ኳሱን ወደው እና አፍቅረው ለእግር ኳሱ ሲሉ ሌሎች ነገሮችን ትተው ከቀጠሉ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ።

“በቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረኝ ቆይታ በአርጀንቲና ያገኘሁትን ከፍተኛ ልምድ ተጠቅሜ አቅሜን በማሳየት በድጋሚ በሀገሬ ሊግ እነሳለው ብዬ ጠብቄ ነበር። ምንም እንኳን የዛን ጊዜ የነበሩ ተጫዋቾች በጣም ጠንካሮች የነበሩ ቢሆኑም ነገር ግን አሰልጣኙ ተጫዋቾችን የሚቆጣጠርበት፣ የሚያስተዳድርበት መንገድ የሚያስደስት አልነበረም። ለምሳሌ አንዳንድ ተጫዋቾች ብቃቱ ቢኖራቸውም ወቅታዊ ብቃታቸው ጥሩ ባልሆነበት ሰዓት ያስገባቸዋል። በአጠቃላይ ሰብዓዊነቱ ወይም የግል ስብእናው የወረደ በመሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ብዙ የማገልገል የመጫወት ፍላጎት እየነበረኝ ብዙ ሳልቆይ ልለቅ ችያለው።

“ያልተረጋጋ የእግርኳስ ህይወት እንዳሳለፍኩ አምናለው። ቶሎም እግርኳስን አቁሜ ሊሆን ይችላል። ቅድም እንዳልኩሁ ከእኔ ስብዕና ጋር የማይሄዱ አሰልጣኞች የተጨዋች ህይወት ላይ ያላቸው ያልተስተካከለ ዕቅድ የተጫዋችነት ዘመኔን እንዳይረጋጋ ስላደረገው እግር ኳሱን እንድጠላው ሆንኩኝ። እንደ አጋጣሚም ወንድሜ ህይወቱ በማለፉ በዛም ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እግርኳሰን አቆምኩ። ለዓመታት ከእግርኳሱ ብርቅም ወደ ስልጠናው እንድገባ ያሬድ የማነ የሚባል ሰው ምክንያት ሆነኝ። በጣም ምጡቅ የሆነ አዕምሮ ያለው ልጅ ነው። መድን እኔ ዋናው ቡድን ሆኜ እሱ ታዳጊ ነበር። እንዳጋጣሚ ወንጂ ላይ ተገናኘን። ወንጂ ደግሞ ትንሽ ስለነበረች ብዙም መሄጃ ስለሌለ ቁጭ ብለን ስለእግር ኳስ እናወራ ነበር። ነጋ ጠባ ስለ እግር ኳስ ነበር የምናወራው። ያኔ እነ ዣቪ፣ ኢኒዬስታ እና ሜሲ መግነን የጀመሩበት ጊዜ ነበር። ባርሴሎናን በጣም እናደንቅ ነበር። ጨዋታቸውን እያየን ‘እንዴት እንደዚህ ሊጫወቱ ይችላሉ ? ‘ ብለን እናወራ ነበር። ያሬድ ስለ እግር ኳስ ያለው ዕውቀት በጣም ጥልቅ ነበር። እናም ያ ነገር ነው ወደ ስልጠናው እንድገባ አስተዋፅዖ ያደረገው። በእርግጥ በውጪም አሰልጣኞች በሀገር ውስጥም ትላልቅ በሚባሉ አሰልጣኞች ሰልጥኛለው። ነገር ግን ከሱ (ያሬድ) ጋር መዋል ከጀመርኩ በኋላ ነው አዕምሮዬ ውስጥ የሰረፀው። የ IT ተማሪም ስለነበር በዛ ተጠቅሞ ቴክኒኩ ላይ ብዙ ነገሮችን ይመረምር ነበር። እና ‘ ታዳጊዎች ላይ በመስራት ለውጥ ማምጣት አለብህ’ የሚለውን ነገር እስርፆብኝ ነበር። በኋላ ላይም እንግሊዝ ሀገር ሄዶ ብዙ መፅሀፎች ይልክልኝ ነበር። በዛ መነሻም ነው ወደ አሰልጣኝነቱ ልገባ ችያለው።

“በመጨረሻም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መስተካከል ያለበት ነገር የምለው። እኛ ሀገር በብሔራዊ ቡድን ብዙ የምናሳካው ነገር አለ ብዬ አስባለው። ነገር ግን ተጫዋቾች ሲመረጡ አሰልጣኞች የየራሳቸው ምርጫ ቢኖራቸውም ብዙ ጊዜ ‘ሩጫ’ ላይ ያተኩራሉ። ለምሳሌ እኔ ፈጣን ተጫዋች ነበርኩ፤ ኳሱንም በደንም እችለው ነበር። በዛን ጊዜ በቅፅል ስም ‘ዊሀ’ እየተባልኩ እጠራ ነበር። የማገባቸው ጎሎች የጭንቅላት ጎሎች ነበሩ። በጣም ጥሩ ችሎታ እና አቅም ነበረኝ። እና ብሔራዊ ቡድን ላይ ይሄንን ከሌሌች ጋር አንድ ላይ ቀላቅሎ የማጫወት ሳይሆን እንዳይገናኝ የማድረግ ነገር አለ። በእግር ኳስ ችሎታ ሳይሆን ቦታው ከሚፈልገው ነገር አንፃር ተመሳሳይ ተጫዋቾችን የማገናኘት ስራ አይሰራም። ያ ነገር የተገናኘ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሓራዊ ቡድን ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለው። የተጨዋቾች የግል ችሎታ ቦታው ከሚፈልገው አንፃር ቢሆን ፍልስፍናችንን ለማራመድ የተመቸ ይሆናል። ተጫዋቾችም የመስራት ባህላቸውን ካዳበሩ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ