ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል ሁለት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


በቦሪስ አርካዲዬቭ አማካኝነት የተፈለሰፈውን እና ይሁነኝ ተብሎ የታቀደበት ትርምስ (Organised Disorder) በመፍጠር የሚካሄደውን የመከላከል አጨዋወት ታክቲክ በድጋሚ ስለማሻሻል ማሰብ ምናልባት የሚገርም ላይሆን ይችላል፡፡ እንዲያውም ያን ጊዜ (በ1950ዎቹ) ከዚህኛው ዘዴ እየተለመደ መሄድና መስፋፋት ጥቂት ዓመታት በኋላ በሩሲያ ሌላ የመከላከል አደረጃጀት መምጣቱ አይቀሬ መሆኑ ግልጽ ነበር፡፡

በሶቭየት አየር ኃይል የሚደገፍ ክሪልያ ሶቬቶቭ ኩይቢሼቭ (አሁን-ሳማራ-ተብሎ የሚጠራ) ክለብ በ1943 ተመሰረተ፡፡ ይህ ቡድን በ1945 ወደ ከፍተኛው ሊግ አደገ፡፡ እጅጉን በመከላከል ላይ ያመዘነው የቡድኑ አጨዋወት የአየር ኃይሉን ክለብ ወዲያውኑ ታዋቂ ለመሆን አበቃው፡፡ በተለይም <ቮልሸካያ ዣሽቼፕካ (Volzhskaya Zashchepka)> የተባለው ጥብቅ የመከላከል ታክቲክ የተለየ ቦታ ተሰጠው፡፡ መጠሪያው ከሩሲያ በሚነሳውና ካስፒያን ባህር ላይ መዳረሻውን ባደረገው ከአውሮፓ ትልቁ ቮልጋ ወንዝ ጋር ተያይዟል-Volga Clip-፡፡ የቨሩውን ያህል ተለዋዋጭ ወይም ዋላይ (Flexible) ባህርይ አልነበረውም፤ የተገኘውም እንደ ሌሎቹ ታክቲካዊ ግኝቶች ከ2-3-5 (Pyramid) ሳይሆን ከ3-2-2-3 (WM) ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መሰረታዊ መርሆዎቹ ተመሳሳይና የተለመዱቱ ነበሩ፡፡ ከመሃል ተከላካዮቹ (Half-Backs) መካከል አንደኛው ወደኋላ ይሳብና የመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Defensive Centre-Half) ከመስመር ተከላካዮቹ (Full-Backs) ጀርባ ሆኖ የመጥረግ ሥራውን (Sweeping-Role) ይከውናል፡፡ የክሪልያው አሰልጣኝ አሌክሳንደር ኩዝሚች አብራሞቭ የዚህ ንድፈ-ሐሳብ አመንጪ ነበር፡፡

” እርሱ ሙሉ ጊዜውን ለእግርኳስ አሰልጣኝነት ያዋለ እና በትልቅ ደረጃ ያሰለጠነ ባለሙያ ባለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች በጣም ተገርመዋል፡፡ነባር ታክቲካዊ ጉዳዮችን የቀኖና ያህል ያልወሰዳቸው ከጂምናስቲኩ ዓለም ስለመጣ ሳይሆን አይቀርም፤ በእግርኳስ አጨዋወት ሐሳቦች ዙሪያ ግትር አቋም አልነበረውም፡፡ ስለዚህ እርሱ የሚመስለውን ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ ቀድሞ በነበረው የአሰልጣኝነት ሥራው ለጂምናስቲክ ልምምድ ልዩ ትኩረት ይቸር ነበር፡፡ የተለያዩ የሥልጠና መርኃግብሮችን በመተግበር ቅንጅታችንን ለማሻሻል ጥሯል፡፡ ልምምድ ስንሰራ ኳስ ሳንነካ አንድ ሰዓት ሊያልፍ ይችላል፡፡ ሆኖም እኛ የበለጠ ብቁ እየሆንን ሄድን፤ ኩዝሚች ሜዳ ላይ ሁኔታዎችን በተለያዩ አቅጣጫዎች እንድናይ፥ በሰፊው እንድናሰላስም አደረገን፡፡ ከእያንዳንዱ ጨዋታ በፊት የቡድኑን አባላት አንድ ላይ ይሰበስብና ለግጥሚያው ምን እንዳቀደ ይነግረናል፤ እኛ እንድንወያይባቸውም ሐሳቡን በዝርዝር ያስረዳናል፡፡ እንግዲህ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሌሎች አሰልጣኞቼ ይህን ሲያደርጉ አልገጠመኝም፡፡” ይላል የቀድሞው የክሪልያ አምበል ቪክተር ካፕሮቭ፡፡ ካፕሮቭ ይቀጥላል- ” የአጨዋወታችን እቅዶች እንደ ተጋጣሚዎቻችን ይለያያሉ፡፡ አስብ እስኪ! ከዳይናሞ ጋር ስንጫወት፥ የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው -ትሮፊሞቭ፣ ካርቴሴቭ፣ ቦስኮቭ፣ ሶሎቪዮቭ እና ላይን ናቸው፡፡ እነዚህን መሳይ በዘመኑ በአንድ ቡድን ውስጥ የሚሰለፉ ከዋክብት አጥቂዎች ለማቆም የተለየ ዝግጅት ማድረግ አለብህ፡፡ በወቅቱ አብዛኛዎቹ ቡድኖች በሶስት ተከላካዮች ይጫወቱ ነበር፡፡ የቡድናችን ተከላካዮች ግን ከፊታቸው በሚሰለፉት የኋላ አማካዮች (Half-Backs) ይታገዛሉ፡፡  ይህ ማለት እኔ በቀኝ (Right-Half) እና ኒኮላይ ፖዥያናኮቭ በግራ (Left-Half) ሆነን የመከላከያ ወረዳችንን እናጠናክራለን፡፡ እኛ ብዙም ተጫዋችን-በ-ተጫዋች በመያዝ የመከላከል ዘዴ (Man-Marking) አንጠቀምም፤ በተቻለን አቅም እንደሁኔታው በሚለዋወጥና በሚዋልል አቀራረብ እንጫወታለን፡፡ በዚህ ሥልት የእያንዳንዱ ተጫዋች ኃላፊነት ሰፋ ያለ ይሆናል፡፡ አልፎአልፎ ከተጠባባቂ ቡድናችን አንድ ተጫዋች ወደ ሜዳ ይገባና ሙሉ ጊዜውን የተጋጣሚን ተጫዋች ለመከታተል ሲታትር ይታያል፡፡ ግትር ተልዕኮ የተሰጠው የመሰለው ምስኪኑ ተጫዋቻችን ሲከታተለው የነበረው የተጋጣሚ ተጫዋች ውሃ ሊጎነጭ ወደ መስመሩ ጠርዝ ሲጠጋም አብሮት ይሄዳል፡፡ ይሄኔ ሌሎቻችን ይህን ቀኖናዊ ትዕዛዝ ለመተግበር የሚጥሩ ጀማሪ ተጫዋቾች ስናይ ሳቃችንን መቆጣጠር ያቅተናል፡፡ ምክንያቱም እኛ አንጋፎቹ ስንሰለጥን እንቅስቃሴያችን እንደ ሁኔታዎች እንደሚወሰን እንማራለን፡፡”

ኒኮላይ ስታሮስቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድሙን በሦስተኛ ተከላካይነት (Third-Back) ሲያሰልፈው እንደተከሰተው ከባድ ተቃውሞ ሁሉ የአብራሞቭ ታክቲካዊ ግኝትም የትግበራ ጅማሬው ላይ እንዲሁ ትልቅ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የአሰልጣኙ ውሳኔ ለሩሲያውያኑ አመቺ የነበረውን አጨዋወት እንደ መክዳትም ተቆጥሮበታል፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ የጨዋታ ዘይቤው ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ፡፡ ሌቭ ፊላቶቭ <About Everything in an Orderly Manner> ላይ ሥልቱን በሚመለከት ” የደካሞች መብት” ሲል አስፍሯል፡፡ በአብራሞቭ ሥር ክለቡን በአምበልነት የመራው አጥቂው ቪክቶር ቮሎሺሎቭ የአጨዋወት ሥልቱን የሚተቹ ሰዎችን ይነቅፍ ነበር፡፡ ” እስቲ ከCDKA ጋር እንጫወታለን ብለን እናስብ- በማጥቃት መስመራቸው ላይ ግሪኒን፣ ኒኮላቪቭ፣ ፌዶቶቭ፣ ቦብሮቭና ዶይሚንን የመሳሰሉ ስል አጥቂዎች አሏቸው፡፡ እና ታዲያ ያለ አቅማችን ወደፊት ሄደን መጋፈጥ አለብን? ለዚህ’ኮ ነው ወደ ራሳችን የግብ ክልል ቀርበን የምንጫወተው፡፡ አንዴ ከዳይናሞ ሞስኮው ጋር ስንጋጠም የተከላካይ ክፍላችን ክፍተቶችን ፈጠረ፤ የእነርሱ አሰልጣኝ ሚክኼይ ያኩሺን አስወረረንና 5-0 ረመረሙን፡፡”

የተቃራኒ ቡድንን የማጥቃት አጨዋወት ለመመከት የ<Volga Clip>ን እንደ ውጤታማ ዘዴ እና ጥሩ የታክቲክ አማራጭ (Spoiling Tactic) መጠቀም አዋጭ አልነበረም ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ በ1946 ክሪልያ ከሃያ ሁለት ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ አሸንፎ አስራ ሁለት ክለቦች በሚሳተፉበት ሊግ አስረኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፡፡ በ1947 ግን ክሪልያ ሰባተኛ በመውጣት ደረጃውን አሻሻለ፡፡ እንዲያውም በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ዳይናሞ ሞስኮን በማሸነፍ ኗሪ የታሪክ አሻራ አሳረፈ፡፡ በ1948ም ክሪልያዎች ጠንካራ ሆነው ቀረቡ፤ ዳይናሞ ሞስኮንም በድጋሚ ረቱ፡፡ በ1949 ደግሞ ለትልልቆቹ ቡድኖች ይበልጥ ፈታኝ ሆነው ተገኙ፤ በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ CDKAን 1-0 ድል አደረጉ፡፡ ” የክሪልያ ትልልቆቹ ተጋጣሚዎች ፍልሚያውን ቀለል ያለ ጨዋታ እንዲሆን ይሞክራሉ፤ በቅብብሎች የታጀበ ፈጣን እንቅስቃሴ ይከውናሉ፤ የቅጣት ምቶችና የማዕዘን ምቶችን በተደጋጋሚ ያገኛሉ፤ ነገርግን ሁሉም ኳሶቻቸው ይበላሹባቸዋል፤ አብዛኞቹ የተሻሙ ኳሶች ወደ ሰማይ ይጎናሉ አልያም ወደ መሮጫ መሙ ይሄዳሉ፡፡ ጭንቅላታቸውን ከግድግዳ ጋር እያላተሙ መሆኑ ሲገባቸው ቀስ በቀስ የማሸነፍ ወኔያቸው ይወርዳል፡፡ ይህም ክሪልያዎች እያንዳንዱን ጨዋታ የሞትና ሽረት ጉዳይ ስለሚያደርጉት የሚፈጠር ነው፡፡” ሲል ፊላቶቭ ጽፏል፡፡

በመሰረቱ የ<Volga Clip> ታክቲክ የጨዋታ የበላይነትን በራስ ቡድን ዝግጅት መሠረት ማስገኘት የሚያስችል ዕቅድ (Pro-Active Strategy) ሳይሆን ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ቡድኖች ትልልቆቹን ክለቦች የሚቋቋሙበት የአጨዋወት ስልት ነበር፡፡ ክሪልያ በ1951 ይህንኑ አጨዋወት የሙጥኝ ብሎ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ሆኖ አጠናቀቀ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ለሶቭየት ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍጻሜ ቀረበ፡፡ ካፕሮቭ እንደሚያስታውሰው ሩሲያ (USSR) ሃንጋሪን ስትገጥም ለአንጋፋው የዚያ ዘመን ሃንጋሪያዊ አጥቂ ጉይላ ስዝላዪን ጥብቁን ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመቆጣጠር ዘዴ ተጠቅማ <Volga Clip> ታክቲክን በመተግበር በ1954 በቡዳፔስት የተካሄደውን የዓለም አቀፍ ውድድር ጨዋታ 3-0 መርታት ችላለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የእግርኳስ አጨዋወት ታክቲክ አብዛኛውን ጊዜ ስሙ ተያይዞ ሲነሳ የኖረው ከክሪልያ ክለብ ጋር ነው፡፡ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኘትም <Bolt> ቀደም ብሎ ጣልያኖች ጋር መድረስ ተጠብቆበታል፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡