“የዘመኑ ከዋክብት ገፅ” ከአሌክስ ተሰማ ጋር…

ላለፉት ዓመታት በቋሚነት የመቐለን ተከላካይ ክፍል የመራው አሌክስ ተሰማ የዛሬው የዘመኑ ኮከቦች እንግዳችን ነው።

ላለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት በወጥነት የቡድናቸው ተከላካይ መስመርን ከመሩ ተጫዋቾች መካከል የመቐለው ወሳኝ ተጫዋች አሌክስ ተሰማ አንዱ ነው። አዲስ አባባ ጨርቆስ ሰፈር ተወልዶ የእግር ኳስ ሕይወቱን በኒያላ ሁለተኛ ቡድን የጀመረው አሌክስ ለኒያላ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ዳሽን ቢራ መጫወት የቻለ ሲሆን በ2008 ክረምት ዳሽን ቢራ መፍረሱን ተከትሎ በወቅቱ በከፍተኛ ሊጉ ሲወዳደር ወደነበረው መቐለ 70 እንደርታ አምርቷል። በመጀመርያ የክለቡ ቆይታው ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና የተወጣ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ቡድኑ በሊጉ እንዲላደልና በ2011 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

የወጥነት እና በአንድ ክለብ ተረጋግቶ የመጫወት ችግር በሚታይበት ሊግ ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት መቐለን በቋሚነት ያገለገለው ይህ ተከላካይ በዘመናችን ኮከቦች የዛሬ እንግዳችን ነው። ከተጫዋቹ ያደረግነው ቆይታም እነሆ።

ጊዜውን የሚያሳልፍበት…

አብዛኛው ጊዜዬን በቤቴ ውስጥ ነው የማሳልፈው። ከቤተሰቦቼ እና ልጆቼ ጋር ጥሩ ግዜ እያሳለፍኩ ነው። ማክሰኞ ፣ ሐሙስ እና ቅዳሜ ደግሞ በግል ስፖርት እየሰራሁ ነው።

እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን..

ከልጅነቴ ጀምሮ ከእግርኳስ ውጭ በሌላ ሙያ ላይ እሰማራለው ብዬ አስቤ አላውቅም። በጣም የሚገርመው እኔ ራሴን ከእግርኳስ ተጫዋችነት ውጭ አስቤው አላውቅም። ገንዘብ ለማግኘት ምናምን ሳይሆን በቃ የእግር ኳስ ፍቅር ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር። አሁን ሆኜ ሳስበው ግን ተጫዋች ባልሆን ኖሮ ከሰፈራችን ሁኔታ አንፃር ወደ ንግድ ነገር የምገባ ይመስለኛል።

ቡድናቸው ላይ ከገቡት ጎሎች የሚያስቆጨው ..

የማልረሳው እና የሚያስቆጨኝ ጎል በአሸናፊዎች አሸናፊ የፋሲሉ ሙጂብ ቃሲም ያገባብን ጎል ነው። ጨዋታው ወሳኝ ነበር፤ ኳሳንም ብቀላሉ ማዳን እንችል ነበር። ይመልሰዋል ብዬ ስጠብቅ ሙጂብ ከፊት መጥቶ አገባት። እና እሷ ጎል ሁሌም ትቆጨኛለች።

በተቃራኒ ሲገጥመው የሚያስቸግረው…

ሰልሃዲን ሰዒድ ነው። ሰልሃዲን ቦታ አያያዙ በጣም ከባድ ነው። ለአቀባዮች ራሱን የሚያመቻችበት መንገድ እና ውሳኔ አሰጣጡ ስታይ በተቃራኒ ለመግጠም ይከብዳል። እያንዳንዱ ነገር ላይ ጥንቃቄ አድርገህ እንድትጫወት ያደርግሀል።

ቢጣመር ደስ የሚለው..

ከያሬድ ባየህ ጋር ብጣመር ደስ ይለኛል። ከዚህ በፊትም በዳሽን ቢራ አብረን ተጫውተናል። በጣም አሪፍ ተከላካይ ነው። ከሱ ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል።

ከእግር ኳስ ውጪ የምሚዝናናው

ከልጆቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ደስታ ይሰጠኛል። ከነሱ ጋር የማሳልፋቸው ጊዜያት ሁሌም ደስተኛ እንድሆን ያደርገኛል።


በእግር ኳስ ውስጥ የቅርብ ጓደኛው
የቅርብ ጓደኛዬ ዮናስ ገረመው ነው። የቅርብ አማካርዬ ነው። ግንኙነታችን ከጓደኝነት ይልቅ እንደ ወንድምነት ነው።

በእግር ኳስ ውስጥ የማይረሳቸው አጋጣሚዎች

ብዙ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ከሚያስደስቱኝ መቐለ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገበት ቀን ነው። ከሚያሳዝኑኝ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ እያለሁ ከአርባምንጭ ጋር ስንጫወት ያጋጠመኝ ጉዳት መቼም አልረሳውም፤ ከባድ ነበር።

በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ያጋጠመው የማይረሳው አጋጣሚ

ሀዋሳ ከተማ እያለው ያጋጠመኝ አንድ ገጠመኝ አለ። ጨዋታው እንዳልኩህ ሀዋሳ ነበር፤ በጨዋታ መሀል አንድ የቡድናችን ተጫዋች ጥፋት ይሰራና ዳኛው ይነፋል። ከዛ አምበል የነበረው ገረሱ ስሜታዊ ሆኔ ዳኛውን ለማስረዳት ሲጠጋ ዳኛው ገረሱን ለማናገር ፍቃደኛ አልነበረም። ከዛ ዳኛው ምንም ላላደረገው ከአንዱ ጥግ ቆሞ የነበረው አሸናፊ ቀኜ ለሚባል ተጫዋች ቀዩን ሰጠው። ቀይ የተሰጠው ተጫዋቹ ምንም አላመነም። ጨዋታ ለመጀመር በሜዳው ይዟዟራል። ሜዳው ላይ የነበረው ሁኔታ ፣ ቀይ የተሰጠው ተጫዋች እና እዛ አከባቢ የነበረው ሁኔታ በጣም ያስቅ ነበር። ካጋጠሙኝ የሚያስቁ አጋጣሚዎች አንዱ ይሄ ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ