እግርኳስን ማሰልጠን የጀመረው በወንዶች ነው። ነገር ግን በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው በሴቶች እግርኳስ ውጤታማ ጉዞው ነው፡፡ ወንዶችን ከታዳጊ እስከ ብሔራዊ ሊግ ሲያሰለጥን በሴቶች ያለፉትን ስምንት ዓመታት ሀዋሳ ከተማን በፕሪምየር ሊጉ መምራት ችሏል። በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን እንዲህ ተመልክተነዋል፡፡
ውልደት እና ዕድገቱ በርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ካፈራው የሀዋሳ ኮረም ሠፈር ነው። ምንም እንኳን በክለብ ደረጃ እግር ኳስን መጫወት ባይችልም በትምህርት ቤት ውድድሮች እና ከተማዋንም በመወከል መጫወት ችሏል። ክለብ ገብቶ የመጫወት ህልም ቢኖረውም ለትምህርት ቤት ውድድር ተመርጦ በልምምድ ላይ ሳለ በአንድ ገደላማ የሜዳ ክፍል ውስጥ እግሩ በመግባቱ እና በጉልበቱ ላይ ጉዳት በማስከተሉ በተጫዋችነት ካሰበበት መድረስ ሳይችል ጉልበቱን እያስታመመ ከዘለቀ በኃላ ዛሬ ላይ ወደሚታወቅበት የአሰልጣኝነት ሙያ ገብቷል።
ከተጫዋችነት በጊዜ ከተለየ በኃላ ሳያመነታ በወሰደው የአሰልጣኝነት ስልጠና በዛው ኮረም ሜዳ በአካባቢው እና በሀዋሳ ውስጥ የሚገኙ ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾችን በመሰብሰብ ማሰልጠንን ጀመረ። “ኳስን መጫወት ከተውኩኝ በኃላ የአካባቢውን እና የተለያዩ ቦታ ልጆችን ሰብስቤ ወደ ማሰልጠኑ ገባው። ከተወሰኑ ዓመታት በኃላም በ1998 ከ17 ዓመት በታች የሀዋሳ ከተማን ፕሮጀክት ቡድን ይዤ አንድ ዓመት ካሰለጠንኩኝ በኃላ ውድድር ተዘጋጀ። ውድድሩ ደግሞ ቡታጅራ ከተማ ላይ ነበር። በውድድሩ ቡድኑን ቻምፒዮን አደረኩኝ። ይህን ቡድን ለውጤት ካበቃሁኝ በኃላ የክልሉን ምርጥ ይሰጠኛል ብዬ ባስብም በወቅቱ የነበረው አሰራር ጥሩ ስላልነበር ለሌላ ሰው ዕድሉ ተሰጠ። እኔ ግን ማሰልጠኔን አላቆምኩም ፤ በተለያዩ የስለጠና ደረጃዎች አሰልጥን ነበር። በአጋጣሚ በዛው ዓመት ፕሮጀክቱ ተበተነ። ከዛ በኃላ ፕሮጀክቱ በአዲስ መልክ ሲቀየር አሁንም ከተማ አስተዳደሩ የሴቶች ፕሮጀክት ቡድንን እንዳሰለጥን ዕድሉን ሰጠኝ። በሰዓቱ የሴቶች ስልጠና የመጀመሪያዬ ስለነበር ፍላጎት አልነበረኝም። ሆኖም ፕሮጀክት የሚለው ነገር ስለነበር እንድ አራት ዓመት እሱ ላይ ሰራሁኝ። ” ሲል አሰልጣኝ ዮሴፍ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ወደ ሙያው እንዴት እንደገባ ይናገራል።
ዛሬ ላይ በሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኝነት ስሙ ይጠራ እንጂ ስልጠናን በወንዶች እግር ኳስ የጀመረው ዮሴፍ በወንዶች እግር ኳስ ከፕሮጀክት ስልጠና ጀምሮ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ወጣቶችንም በማሰልጠን በክለቦች ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ነበረው። በዚህም ሂደት ውስጥ በግብፅ ለምስር ኤል ማቃሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለን ፣ ማናዬ ፋንቱን፣ የሽረው ዮናታን ከበደን ፣ የሲዳማ ቡናው አበባየው ዮሃንስን ፣ የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰን ጨምሮ በርካታ ወንድ ተጫዋቾችን ለእግር ኳሱ አበርክቷል፡፡ በወንዶች እግር ኳስ ራሱን በሚገባ ያደረጀው አሰልጣኝ ዮሴፍ ፎር ኤች የሚባል ክለብን ከአሁኑ የወሎ ኮምቦልቻ አሰልጣኝ ሻምበል መላኩ ጋር በጣምራ በማሰልጠን ከሀገር አቀፍ ሻምፒዮና ወደ ብሔራዊ ሊግ እንዲገባ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሆኖም ከሚሊኒየሙ ማግስት በኃላ ፊቱን ወደ ሴቶች እግር ኳስ በማዞር ከፕሮጀክት ስለጠና ተነስቶ አሁን ላይ በሀገሪቱ ካሉ ትልልቅ የሊጉ አሰልጣኞች ተርታ ሊሰለፍ ችሏል፡፡
2003 ላይ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የደቡብ ክልል የሴቶች ቡድንን አዳማ ላይ በነበረው የመላው ኢትዮጵያ ውድድር ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ማድረግ በመቻሉ በሴቶች እግር ኳስ በአጭር ጊዜ ላይ ያስመዘገበውን ውጤት መነሻ በማድረግ ሀዋሳ ከተማ ካለምንም ማስታወቂያ 2005 ላይ በይፋ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጠረው። በወቅቱ በምድብ ተከፍሎ ይካሄድ በነበረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በደቡብ ምስራቅ ዞን ሲዳማ ቡናን እና አርባምንጭ ከተማን በደርሶ መልስ በመርታት እና የምድቡ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን አንስቶ አዳማ ላይ ለተዘጋጀው የማጠቃለያ ውድድር ማብቃት ችሏል፡፡ በእሱ ስር በፕሮጀክት ይሰለጥኑ የነበሩ ተጫዋቾችን በመያዙ በውድድሩ ብዙ ያልተቸገረው አሰልጣኙ ለዋንጫ ለማለፍ ደርሶ በንግድ ባንክ ቢሸነፍም በመጀመሪያ ዓመቱ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሀስ ተሸላሚ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነበር። አሰልጣኙ በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዳ “ሀዋሳ ከተማን ስይዝ የመጀመሪያውን ዓመት ለተሳትፎ ብቻ ነበር የተወዳደርነው። ክፍያውም የወረደ ነበር ፤ የአሰልጣኝ አንድ ሺህ የስፖርተኛ ደግሞ ሠባት መቶ ብቻ። ነገር ግን ልክ እኔ ይሄንን ቡድን ያዝ ስባል ከማሰለጥነው ታዳጊ የሴቶች ቡድን አስራ አንድ ልጆችን ነው በድፍረት ይዤ የመጣውት። ከዚህ ውጪ ከእኔ በፊት በሌላ አሰልጣኝ ይሰለጥኑ የነበሩትን ልጆችንም አካትቼ ነው ወደ ውድድር ገባው ። በዚህ ረገድ ሀዋሳ ከተማን ማመስገን እፈልጋለሁ። ስምንት ዓመት ስሰራ ስለተጫዋች ምልመላ ስለምንም ነገር ማንም ሰው ጣልቃ ገብቶብኝ አያውቅም። ያን ዓመት ለተሳትፎ ብለን ተጨማሪ ከሌላ ቦታም ጨማምረን ወደ ውድድር ገባን። እንደ አሰልጣኝ ፕሪምየር ሊግ ከባድ ነው። ምክንያቱም ስናሰለጥን የነበረው ፕሮጀክት ነው። ወደ ውድድር ገብቼ ግን ሳየው ‘ፕሪምየር ሊግ ማለት ይሄ ነው ? ‘ ነበር ያልኩት። ልጆቹም ራሳቸውን ለማሳየት እና ነገ የተሻለ ቦታ ለመገኘትም አብረን በመስራታችን 2005ን ማንም ሳይጠብቀን ተፎካካሪ በመሆን ሦስተኛ ሆነን ጨረስን” ይላል።
ያለፉትን ስምንት ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ሀዋሳ ከተማን እያሰለጠነ የቆየው አሰልጣኝ ዮሴፍ እንደ ቢርኪርካራዋ አጥቂ ሎዛ አበራ ፣ ዓይናለም አሳምነው ፣ አባይነሽ ኤርቄሎ ፣ ቅድስት ዘለቀ ፣ ምርቃት ፈለቀ ፣ ዝናሽ ብርሀኑ ፣ መቅደስ ማሞ እና ዘንድሮ ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆና ስትመራ የነበረችው መሳይ ተመስገንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሴት ተጫዋቾችን እየመለመለ ዛሬ ለደረሱበት ትልቅ ደረጃ እንዲበቁ ከፍተኛ አሻራውን አሳርፏል። ታዳጊ ተጫዋቾችን እየመለመለ ለክለቡ ከማበርከት በዘለለ ወደ ሌሎች ክለቦችም አምርተው ተፅኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማድረግ የአሰልጣኙ አበርክቶት ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል። “ዛሬ ከሎዛ ጀምሮ አብዛኞቹ ትልቅ ቦታ የደረሱት ከወረዳ እና ከዞን መጥተው ነው። ፕሮጀክት ሳሰለጥን ጀምሮ በወጣቶች አምናለሁ። ሀዋሳን ማሰልጠን ስንጀምር ክፍያውም ትንሽ ስለነበር ወጣቶች ላይ በደንብ ትኩረት አድርጌያለሁ። ያም ቢሆን ትልቅቅ ቡድኖችን እናሸንፍ ነበር ፤ ወጣቶች በመሆናቸው ይሰሙኝ ስለነበር አልቸገርኩም። ዛሬ ላይ በክልል አስፈሪ የሚለውን ስም የያዘው ከዚህ መነሻነት ይመስለኛል” በማለት ወጣቶች ላይ ስላለው ዕምነት ያስረዳል።
ወጣት ተጫዋቾችን በየዓመቱ እየመለመለ በትንሽ ክፍያ ጥሩ ቡድን ሲገነባ በተደጋጋሚ የሚታየው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ስለዚህ ዕምነቱ እንዲህ በማለት ያስረዳል። “እግር ኳስ በአንተ አጀማመር ይወስናል። እኔ የመጣሁበት መንገድ ሳሰለጥን ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። ሀዋሳ ቤት ይሄን አምጡ ተብለን የምንገደድበት ቤት አይደለም። ሲጀመርም ለተሳትፎ ተጀመረ ከዛ በኃላ ተፎካካሪ እየሆንን ስንመጣ ደግሞ ጥንካሬያችን እየጎለበተ መጣ። ተጫዋቾቼም እኔን ስለሚሰሙኝ ረጅም ጊዜን ላሳልፍ ችያለሁ። ትንንሽ የወረዳ እና የክልል ውድድሮችን ተመልክቼ ተጫዋቾችን ሳመጣ ትንሽ ጊዜ ልቸገር እችላለሁ። ከዚያ በኃላ ግን ነጥረው ሲወጡ ይታያል። አብዛኛዎቹ አሁን ላይ ስማቸው የሚጠራው ከወረዳ የተገኙ ናቸው። ለምሳሌ አባይነሽ ኤርቄሎ እና ቅድስት ዘለቀን ማንሳት ይቻላል ። ወጣቶች ላይ በደንብ በመስራቴ ትልቅ ክፍያ ወይም ውጤት አምጣ የሚል ስለሌለ ትኩረት ላደርግ ችያለሁ።”
አሰልጣኝ ዮሴፍ በሀዋሳ የስምንት ዓመታት ቆይታው በሊጉ 2005 እና 2009 ላይ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ሲችል ከ2005 እስከ 2007 ሊጉ በምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ በነበረ ጊዜ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የምድቡ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ 2009 እና 2011 ላይ ሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሲያነሳ የአሰልጣኙ ድርሻ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡
በተጫዋቾቹ ዘንድ እጅጉን የሚፈራው እና በሥነምግባር የታነፀ ቡድን ሲገነባ የሚታየው ዮሴፍ ገብረወልድ ስለኃይለኛ እና ቁጡ ባህሪው ይህንን ይላል። “እኔ ፈልጌው የመጣ ነገር አይደለም። አንድ ሰው የሚሰጠው ባህሪ አለው። ይሄ መሰጠት ነው እንጂ ሴቶቹ ላይ ብቻ የማሳየው ባህሪ አይደለም። ወንዶችንም ሳሰለጥን ይሄ ባህሪዬ ነበር። ደግሞም ለእግር ኳስ ብቻ አይደለም ለማንኛውም ነገር ሥነምግባር አስፈላጊ ነው። ሥነምግባር የሌለው ሰው ህይወቱ ይበላሻል። እኔም ተጫዋቾቼ ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ህይወታቸው እንዳይበላሽ ለማድረግ እንጂ የመቆጣት ወይ ሰው የማመናጨቅ ወይ የመሳደብ አመል ኖሮኝ አይደለም። እኔ ከምን አይነት ቤተሰብ እንደመጣሁ አውቀዋለሁ። ስፖርተኞች ደግሞ በብዛት ከችግረኛ ቤተሰብ የሚመጡ ናቸው። ሴቶች ደግሞ ትንሽ ነገር ከገጠማቸው ከወጡ መመለስም ይከባዳቸዋል። ከዛ አንፃር እንጂ ሴቶች ስለማሰለጥን ብዬ ያመጣሁትም አይደለም። መቆጣትን ሰዎች የሚገልፁበት መንገድ ሊኖር ይችላል። የሰውን ልጅ አልሰድብም ሜዳ ስገባም ስራዬ ነው ፤ ማድረግ ያለብኝን አደርጋለሁ። ስፖርተኛ መንከባከብ ግድ ይላል። ያን ሳላደርግ ቀርቼ አይደለም። መንከባከብ ባለብኝ ነገር እንከባከባለሁ። ነገር ግን አልተጎዳሁበትም ፤ የኔ ጥቅም የገባቸው አመስግነውኛል። በባህሪዬም ብዙዎቹ ተጠቅመዋል ፤ እኔን ግን በሽተኛ አድርጎኛል።”
አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ያላሳካውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማንሳት በእጅጉ የሚያልም ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለማሰልጠንም ከፍ ያለ ፍላጎት አለው። እስካሁንም ይህን ዕድል አለማግኘቱ እንደሚያስቆጨው ይህ አስተያየቱ ይናገራል። ” በእኔ ስር ያለፉ ተጫዋቾች ዛሬ ተጠቃሚ ሆነው ማየቴ ለኔ ከበቂ በላይ ነው ፤ ሳያቸውም ደስተኛ እሆናለሁ። ከዛ ሲቀጥል ግን እንደ አሰልጣኝ ሀገሬን ባሰለጥን ደስ ይለኛል። ስኬታማ ከሆንክ እና ሁሉም የአንተን ጠንካራነት ከመሰከሩ ብሔራዊ ቡድን ማታሰለጥንበት ምንም ምክንያት አይኖርም ፤ ይሄ የኔ ችግር አይደለም። ፌድሬሽኑ የራሱን ችግር መገምገም አለበት። እኛ በክልል ደረጃ ሆነን ማሰልጠናችን ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ከሚዲያ በመራቃችን እና በአካባቢያችን ያሉ ሚዲያዎችም ትኩረታቸው እምብዛም በመሆኑ ተበድለናል። በእርግጠኝነት አዲስ አበባ ብሆን በአንድ ክለብም እንዲህ ስኬታማ ብሆን እመረጥ ነበር። ሚዲያዎች ደግሞ ለዚህ አስተዋጽኦ አላቸው። እንደሰው በነበረኝ ስኬታማ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ባለማሰልጠኔ ውስጤ ተጎድቷል። ይሄ ማለት ደግሞ ተስፋ ቆርጬ አቆማለሁ ማለት አይደለም። ለምሳሌ እኔ ያፈራሁዋቸው ተጫዋቾች ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እየተጫወቱ ነው። እነሱን ያየ ዓይን እኔን የማያይበት ምክንያት ይገርመኛል። ነገር ግን ብዙ አይጨንቀኝም። መዘጋጀት እና ዕድሉን ሳገኝ መስራት እንጂ እሰጣ ገባ ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ አይደለም። በተለይ ባለፈው ዓመት ጠብቄ ነበር ፤ ከ17 ወይም ከ20 ዓመት በታች። ያ አልሆነም ፤ እግዚአብሔር እስኪፈቅድ መጠበቅ ነው።”
ተወልዶ ባደገበት ኮረም ሠፈር በሚገኘው ሜዳ ኳስን ከመጫወት አንስቶ እስከ አሰልጣኝነት ሙያ የደረሰው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተናግሮለት ስለማይጠግበው ሜዳ እንዲህ ይላል። “ኮረም ሜዳ ሰፈሬ ነው ፤ የተወለድኩትም ጭምር። እኔ ከዝቅተኛ ቤተሰብ ነው የተገኘውት። በዚያን ሰዓት በግል ማቴሪያል ማግኘት ይከብድ ነበር። ሆኖም በራሴ ጥረት የማደርገውን እያደረኩ ልጆችንም እየሰበሰብኩ እያሰለጠንኩ ብዙ ተጫዋቾች አፍርቻለው። አሁን እከሌ እከሌ ማለት ይከብደኛል። ኮረም ሜዳ በተለይ ለኔ ለዛሬው ህይወቴ መነሻ የሆነኝ ሜዳ ነው። ከዚያ አካባቢ የወጣን ሁሉ የሜዳው ውለታ አለብን። ስለሜዳው አውርተን አንጠግብም ፤ ህይወታችንን እንድንመራ አድርጓናል። የገለፅኩት በጥቂቱ እንጂ ያንስበታል።”
በራሱ ጥረት ታትሮ እዚህ ደረጃ የደረሰው አሰልጣኙ በብሔራዊ ሊግ ደረጃ አብሯቸው ለሰራው አሰልጣኝ ሻምበል መላኩ ትልቅ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ” ከእሳቸው ጋር አብሬ መስራቴ ጠቅሞኛል” ይላል። በሌላ በኩል ለቤተሰቦቹ ፣ ለባለቤቱ ፀዳለ ብዙነህ እና የሀዋሳ ህዝብም ምስጋናውን አቅርቧል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ