ስለ ዮናስ ገብረሚካኤል ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ብዙዎች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከታዩ ምርጥ የመስመር ተከላካዮች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚመሰክሩለት የዘጠናዎቹ ኮከብ ዮናስ ገብረሚካኤል ማነው ?

ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ድንቅ ብቃቱን በማውጣት በቀያዮቹ ቤት መድመቅ የቻለው የዛሬው እንግዳችን ዮናስ ገብረሚካኤል ብዙ ታሪክ በሰራባቸው የመብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን መላው የእግር ኳሱ ተከታታይ የሚስማማበት ምርጥ የቀኝ መስመር ተከላካይ ነው። በአዲስ አበባ ተክለኃይማኖት አከባቢ ተወልዶ የእግር ኳስ ህይወቱን በመብራት ኃይል ታዳጊ ቡድን የጀመረው ዮናስ በእግር ኳስ በቆየባቸው ከአስር የማይበልጡ ዓመታት ውስጥ ምርጥ የመስመር ተከላካይ መሆኑን አስመስክሯል። በተለይም በውጤታማው የመብራት ኃይል ቡድን ውስጥ የነበረው አስተዋፅኦ ለዚህ ምስክር ነው። የመስመር ተከላካዮች ወደ ፊት ሄደው የማጥቃት አጨዋወቱን ለማገዝ በማይደፍሩበት ወቅት በማጥቃቱ ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው ይህ ተከላካይ በተለይም በተሳኩ ሸርተቴዎቹ እና ወደፊት ሄዶ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ይታወቃል።

በእግርኳስ ህይወቱ በልዩ ለሚታወሰው በአርጅንቲናው የዓለም ዋንጫ ለተሳተፈው ወጣት ብሔራዊ ቡድን እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በአንድ የውድድር ዓመት የሦስትዮሽ ዋንጫ ባሳካው ውጤታማው መብራት ኃይል ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ የየመኖቹ ሀሊ ሁዳያዳ እና አል ረሽድ ቀጥሎም ትራንስ ኢትዮጵያ እና ደደቢት የተጫወተው ዮናስ ለአሳዳጊ ክለቡ መብራት ኃይል እና ለኢትዮጵያ ቡና ልዩ ፍቅር እንዳለው ይገልፃል።

መብራት ኃይል በ1993 የሦስትዮሽ ዋንጫ ክብርን እንዲያሳካ ከረዱት ቁልፍ ተሰላፊዎች አንዱ የነበረው ዮናስ በ1996 ከልጅነቱ ጀምሮ ሲደግፈው ለኖረው እና በልቡ ውስጥ ልዩ ቦታ ላለው ኢትዮጵያ ቡና መጫወቱ እጅግ እንደሚያስደስተው ይገልፃል። በኢትዮጵያ ቡና እስከ1998 ድረስ ተጫውቶ ወደ የመን በማምራት ሁለት የውድድር ዓመታት ያሳለፈው ይህ ተከላካይ በድጋሜ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለሚወደው ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ትራንስ ኢትዮጵያ እና ደደቢት ተጫውቷል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ሲያነሳ በ1996 ደግሞ ለዓመቱ ኮከብነት ያሳጨውን ድንቅ የውድድር ዓመት አሳልፎ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቦ ነበር።

የስፖርት ጋዜጠኛው ዮናስ አዘዘ ስለመስመር ተከላካዩ ብቃት ምስክርነት ከሚሰጡ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ውስጥ አንዱ ነው፤ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተመለከታቸው ተጫዋቾች ውስጥ የግሉን ምርጥ 11 ለሶከር ኢትዮጵያ ባጋራበት ወቅትም በቀኝ መስመር ተከላካይነት ስላካታታው ዮናስ ገብረሚካኤል ይህንን ብሎ ነበር። ” የአልሸነፍ ባይነት እልሁ እጅግ ያስገርመኛል። የመስመር ተከላካይ ሊያሟላቸው የሚገቡ የግል ብቃቶችን አሟልቶ የያዘ ነው። አንድ ለአንድ ዮናስን ማለፍ በጣም ከባድ ነው ፤ ጊዜያቸውን የጠበቁ ሸርተቴዎቹ እጅግ ያስገርማሉ ፤ የቡድን ጓደኞቹ የመከላከል ክፍተት በሚፈጥሩበት ጊዜ ያንን ክፍተት ለመሸፈን የሚያሳየው ትጋትም በጣም አስገራሚ ነው። በማጥቃት ወቅት ተደርቦ ወደ ውስጥ ገፍቶ በመግባት ማጥቃቱን በማገዝ በኩልም የተዋጣለት ነበር።”

በወጣት ብሔራዊ ቡድን እና መብራት ኃይል እጅግ የተሳኩ ጊዜያት የነበሩት ዮናስ የክለብ እና የብሔራዊ ቡድን ቆይታውን እንዲህ ይገልፀዋል።

” መጀመርያ ከመብራት ኃይል ሦስተኛ ቡድን ነው ያደኩት። በኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድንም ተጫውቻለው። የታዳጊ ቡድን ቆይታዬ በጣም አሪፍ ነበር። በልዩ ተነሳሽነት ነበር የምንሰራው ፤ የኳስ ምዕራፍ መጀመርያዬ ስለነበር በልዩ ሁኔታ ነው የማስታውሰው። መጀመርያ በ1991 ከሁለተኛ ቡድን ነው ለብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩት ፤ በሰውነት ቢሻው አማካይነት። ከአንድ ዓመት በኃላ ደግሞ በዲያጎ ጋርዝያቶ በሰለጠነው ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን አባል መሆን ችያለው። ያን ጊዜ ይልበጥ ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ጋር የተዋወቅኩበት ጊዜ ነበር።”

” ከመብራት ኃይል ጋር የነበረኝ ቆይታ ደግሞ በጣም ምርጡ እና በህይወት ዘመኔ ከማልረሳቸው ጊዜያት አንዱ ነው። በጣም ስኬታማ ጊዜ ነበር ፤ በመብራት ኃይል ታሪክ እስካሁን ድረስ ትልቅ ቦታ አለው። በ1993 በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ክብሮች ያሳካንበት ጊዜ ነበር። በግሌም በወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ እና ዓለም ዋንጫ የተሳተፍኩበት ወቅትም ስለነበር ልዩ የስኬት ጊዜ ነበር። አብዛኞቻችን ታዳጊዎች ነበርን ፤ ከሁለተኛ ቡድን ነው ያደግነው። ፍቅራችን እና መግባባታችንም ልዩ ነበር ፤ ጊዜው በጣም ደስ የሚል ነበር። በፍቅር ነው ያሳለፍነው ፤ አሁን ይሄን ጥያቄ ስታነሳልኝ ራሱ ወደ ኃላ ተመልሼ ብዙ እንዳስብ አድርጎኛል። ለአሳዳጊ ክለቤ መብራት ኃይል በዋናው ቡድን ብዙ አገልግያለው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ካገለገልኩት በላይ ዕውቅናን አግኝቼበታለው። ከ1992-95 ነበር በመብራት ኃይል የቆየሁት፤ በመጨረሻዎቹ ጊዜያት አከባቢ ግን በጉዳት ብዙ አልተጫወትኩም።

” ቀጥሎ ከልጅነቴ ጀምሮ ልቤ ውስጥ ለነበረው ኢትዮጵያ ቡና ነው የፈረምኩት። እግዚአብሔር ፈቅዶ ለምወደው እና ለምደግፈው ኢትዮጵያ ቡና በመጫውቴም ደስተኛ ነኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ስመኘው የነበረውን ህልም በማሳካቴም ደስተኛ ነኝ። በሜዳ ላይ ቆይታዬም ደስ የሚል ጊዜ አሳልፍያለው ፤ ቡና ውስጥ ብዙ የልብ ደጋፊዎች አሉ። በተመሳሳይ ደግሞ ብዙ ፈተናዎችም አሉ። በ1996 ለክለቡ በፈረምኩበት ጊዜ በጣም ጥሩ ቡድን ነበር። ስብስቡ አንድነት ነበረው ፤ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችም ነበሩ። በግሌ በጣም የተሳካ ጊዜ ነበር ማለት እችላለው። በዚያ ዓመት በመጨረሻው ሰዓት ዋንጫውን በማጣታችን ባዝንም በብቃት ደረጃ ግን ጥሩ ብቃት ላይ ነበርን። በኢትዮጵያ ቡና በሁለት ጊዜያቶች በድምሩ ለአምስት ዓመታት ተጫውቻለው። በቡና አሪፍ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። በተለይም ደጋፊዎቹ እስካሁን ድረስ ከአዕምሮዬ አይጠፉም። በእግር ኳስ ህይወቴ በኢትዮጵያ ቡና ተጫውቼ በማለፌ ሁሌም ደስተኛ ነኝ። የቡድኑን ሁኔታ አሁንም እከታተላለው። በቡና በአምበልነት ለሦስት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ አገልግያለው ፤ የቤቴ ያህል ነው የሚሰማኝ። ቡና እና መብራት ኃይል በልቤ ልዩ ቦታ አላቸው ፤ ቡና ከልጅነቴ የምደግፈው ቡድን ነው ፤ መብራት ኃይል ደግሞ አሳዳጊ ክለቤ ነው።

“የእግር ኳስ ቤተሰቡ ሳይጠግብህ ነው ከኳስ የተለየኸው ላልከው እኔም እስከምፈልገው ድረስ ተጫውቻለው ብዬ አላስብም። በኢትዮጵያ ለአስር ዓመታት ተጫውቻለው በየመንም ለሁለት ዓመታት ተጫውቻለው። ደጋፊው ሳይጠግበኝ ከኳሱ የተለየሁት በጉዳት ነው፤ በተለይም በመጨረሻዎቹ ዓመታት ከነጉዳቴ ነው የተጫወትኩት። እኔም አቅሜን ሳላሳይ በደንብ ተጫውቼ ሳልጠግብ እንደተለየው ነው የሚሰማኝ። ነገር ግን ባሳለፍኩት ጊዜ ብዙ ስኬታማ ስለነበርኩ በጣም ደስተኛ ነኝ።

” በማደርጋቸው የተሳኩ ሸርተቴዎች ነበር የምታወቀው፤ ይህን ያዳበርኩትም በልምምድ ነው። ተከላካይ ስትሆን ብዙ ነገር ማሟላት ይጠበቅብሀል። ከነዚህ ውስጥ ሸርተቴ አንዱ ነው። ከልምምድ ሌላ የውጪ ሀገር በተለይም የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በብዛት እከታተል ነበር። የመስመር ተከላካዮችን እንቅስቃሴ በትኩረት እመለከት ነበር። ከዛም ብዙ ትምህርት ወስጃለው ፤ የግሌ ጥረትም ብዙ ነበር። በተጨማሪም በጋርዝያቶ ስር በሰለጠንኩበት ወቅት ስለ ሸርተቴዎች እና መሰረታዊ የመከላከል ብቃቶች ብዙ ነገር አስተምሮናል ፤ የሱ ሚናም ቀላል አልነበረም። እኔ ለደረስኩበት ደረጃ ሁሉም ያሰለጠኑኝ አ ሰልጣኞች የበኩላቸው ሚና አላቸው በዚህ አጋጠሚም ላመሰግናቸው እፈልጋለው።

“በህይወቴ ብዙ የማልረሳቸው አጋጣሚዎች አሉ ፤ በስኬት ደረጃ በብሔራዊ ቡድን እና በመብራት ኃይል የነበረኝን ስኬት አልረሳውም። በሌላ በኩል በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በተለይም ደግሞ በ1996 ቡና እያለው ያጣነው ዋንጫ የሚያስቆጭ ነበር። ሦስት አራት ጨዋታ እየቀረን በሰባት ነጥብ እየመራን ነበር። ያ ጊዜ መቼም ከአዕምሮዬ አይወጣም ምክንያቱም ከቡና ጋር ዋንጫ መሳም እፈልግ ነበር።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ