የኮምቦልቻ የዳኞች እና ታዛቢዎች ሙያ ማኅበር ድጋፍ አደረገ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ሀገራችንም እያስከተለ የሚገኘውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በስፖርቱ ዘርፉ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ድጋፋቸውን እያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ የኮምቦልቻ ዳኞች እና ታዛቢዎች ሙያ ማህበርም በቀደሙት ጊዜያት በወሎ እና አካባቢዋ በዳኝነቱ ሆነ በስፖርቱ ጉልህ አስተዋፅኦ ላደረጉት ባለውለተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን አስመልክቶ የማኅበሩ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ታምሩ አዳም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ይህን ብለዋል።

” ማኅበሩ ከተቋቋመበት ከ2007 ዓ.ም አንስቶ እስካሁን ድረስ የተለያዩ ስራዎችን ማለትም በከተማ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ዳኝነት ስልጠናን በማዘጋጀት አዳዲስ ሙያተኞችን በማፍራትም ሆነ በክልላችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስብል መልኩ በሀገሪቱ ከሚገኙ ስመጥር ከሆኑ ኢንተርናሽናል እስከ ፌደራል ዳኞች ጋር አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ የልምድ ልውውጥ አካሄደናል። በከተማችን ካሉት ዳኛች ውስጥ በዚህ አመት ሁለት ዳኞችን የፌደራል ዳኝነት ስልጠና እንዲሰጡ እና የፌደራል ዳኞች ቁጥርን ደግሞ ወደ 5 ያሳደግን ሲሆን አሁን ላይ ጊዜው ያመጣውን በሽታ መቋቋም ደሞ የግድ የሚል እንደመሆኑ እንደ ማኅበር ወስነን ምንም እንኳን በሀገርዓቀፍ ደረጃ ውድድሮች ቢቆሙም ህብረተሰባችንን ከማገልገል አያቆመንም በሚል መሪ ቃል የቀድሞ የስፓርት ቤተሰቦችን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ችለናል። 

“በዚህም ጥረት ውስጥ በከተማችን ካሉ የልማት ድርጅቶች ግለሰቦች ማለትም ከቤዛ ፖስፐሪቲ ፣ የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች ከሁሉም ቅርጫፍች ያሰባሰብን መሆኑ እና በቀጣይ ቀናቶች ተጨማሪ ድጋፍ የማሰባሰብ እና የደም ልገሳ ስራ ለመስራት አቅደን እየሰራን እንገኛለን። በተለይም ቤዛ ፖስፐሪቲ የልማት ድርጅት እያደረግነው በሚገኘው ጥረት ላይ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ይገኛል። አላማችንን ለማሳካት በርካታ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እየረዱን ነው። አሁንም እገዛ ቢያደርጉልን ይህን ጊዜ ተረዳድተን ማለፍ እንችላለን። ይህ ድርጊታችን በራሱ ለቀድሞ ስራቸው እውቅና መስጠትም ነው። ከጉናችን ለነበሩ እንዲሁም ወደፊትም አብረውን ለሚኖሩ ምስጋናዬን አቀርባለው።” ብለዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ