” አበባው ቡታቆ በረጅሙ ሲልካት የተከላካዩ እና የግብ ጠባቂውን አቋቋም አይቼ በግንባሬ አስቆጠርኳት…”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ ጥሩ አስተዋፅኦ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት በመቐለ 70 እንደርታ እየተጫወተ የሚገኘውና በእግር ኳስ ህይወቱ ለኒያላ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ደደቢት የተጫወተው ይህ የመስመር ተከላካይ በቦታው ለረጅም ዓመታት ወጥነት ባለው ጥሩ ብቃት ከመጫወቱ በዘለለ ከሜዳ ውጪም የተረጋጋ ህይወት ከሚመሩ በሳል ተጫዋቾች አንዱ ነው።
በብሔራዊ ቡድን ቆይታው ስድስት ግቦችን አስቆጥሯል ፤ የኢትዮጵያ የቻን ውድድር ብቸኛ ግብም ባለቤት ነው።
ተጫዋቹ ከተለመደው የመስመር ተከላካይነት ሚና ወጥቶ በመስመር ተጫዋችነት ተሰልፎ ወሳኝ ግብ ባስቆጠረበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያ (ሱዳን 5-3 ኢትዮጵያ) በነበረው የሱዳኑ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ያሳለፈውን ትውስታ እንደሚከተለው አጋርቶናል።
” ወደ ሱዳን በጥሩ ተነሳሽነት በአሪፍ የማሸነፍ መንፈስ ነበር የሄድነው ፤ ቡድኑ በሁሉም ረገድ ጠንካራ ነበር። ለዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ እንገኝ የነበረ መሆኑ እና ሁላችንም ለሀገር የመጫወቱ ትርጉም በደንብ ስለገባን ነበር። በሱዳን ቆይታችን ብዙ ነገር አጋጥሞናል ፤ ገና ኤርፖርት እንደገባን ጀምሮ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። ከአቀባበሉ ጀምሮ ብዙ መጉላላቶች ነበሩ ፤ ሆቴልም በአግባቡ አልተያዘልንም ነበር። ገና ጨዋታው ከመጀመሩ የገጠሙን ፈተናዎችም እንዲሁ ብዙ ነበሩ። ከዚያ ወደ ጨዋታው ገባን ፤ የጨዋታው ድባብ ጥሩ ነበር። ነገር ግን በጨዋታው መጀመር በኋላ በሰባተኛው እና በአስራ አምስተኛው ደቂቃ ሁለት ግቦች አስተናገድን። ወደ ጨዋታችን ቅኝት ለመግባት ብዙ ጣርን ጥረታችን ፍሬ አፍርቶ ሦስት ግቦች አስቆጥረን አቻ ሆንን። የኔ ጎልም አቻ የምታደርግ ሦስተኛ ጎል ስለነበረች ስሜቱ ልዩ ነበር። ልክ አበባው በረጅሙ ሲልካት የተከላካዩ እና የግብ ጠባቂውን አቋቋም አይቼ በግንባሬ ነበር ያስቆጠርኳት። እኔ ሦስተኛውን ጎል ካስቆጠርኩ በኃላ ትልቅ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ከኃላ ነው የተነሳነው ጨዋታውም ከባድ ነበር። ያን ሁሉ ነገር አልፈን ከሜዳችን ውጪ ሦስት ጎል ማግባታችን ትልቅ ተስፋ ነበር። ከዛ በኃላ የተፈጠረው ግን ለማመን ይከብዳል። ብዙ የዳኝነት በደል ደረሰብን ሁለት የማያሰጡ ፍፁም ቅጣት ምቶች ተሰጡብን ፤ በግልፅ ለነሱ ያዳላ ነበር። አፍሪካ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የተለመዱ ቢሆኑም የሱዳኑ ግን ለየት ይላል። ካለፈ በኃላ ነገሮች እንደ ቀላል ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም ብዙ ብዙ ፈተናዎች የነበረበት ነው የማጣርያው ሂደት ፤ በተለይም የሱዳኑ ጨዋታ። የሱዳን ቆይታችን ለኛ ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎቻችንም ጥሩ አልነበረም ፤ በተለይም ሦስተኛውን ጎን ካገባን በኃላ። ደስ የሚለው ነገር ግን ከዛ ሁሉ ነገር በኃላ በመልሱ ጨዋታ እዚህ አዲስ አበባ ሁለት ለባዶ አሸንፈን ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኃላ ሀገራችንን ወደ አህጉራዊ ውድድር መልሰናል። በከባዱ ጨዋታ ለሀገራቸው ያላቸውን ነገር በሙሉ ሳይሰስቱ ያበረከቱት ሙሉ የብሄራዊ ቡድኑ አባላትን በያሉበት ማመስገን እፈልጋለው ፤ በጋራ የማይረሳ ታሪክ ነው የሰራነው። በሰዓቱ ብዙ ነገር ተቋቁመው ዘጠና ደቂቃ ሙሉ ለደገፈን ደጋፊም ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ