ሳላዲን ሰኢድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በቻምፒዮንስ ሊጉ ሩቅ መጓዝን ያልማል 

ሳላዲን ሰኢድ ወደ ቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመልሰው ኮንትራት መፈራረሙን ተከትሎ ለመጀመርያ ጊዜ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ወደ ፈረሰኞቹ ቤት መመለሱ ደስታን እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡

ሳላዲን ወደፊት በሚሻሻል ኮንትራት ከፈረሰኞቹ ጋር የ6 ወራት ኮንትራት የተፈራረመ ሲሆን ወደ ክለቡ በመመለሱ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል፡፡ ‹‹ ብዙ ስኬት ወዳገኘሁበት ክለብ ከቆይታዎች በኋላ በመመለሴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡›› ይላል፡፡ አክሎም ከጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጋር ያለው ግንኙነት ለመመለስ እንዳበቃው ተናግሯል፡፡ ‹‹ አሁን በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ሁሉንም ማለት በሚቻል ሁኔታ አውቃቸዋለሁ፡፡ ወደ ውጪ ከመውጣቴ በፊት አብሬያቸው የተጫወትኳቸው እና በብሄራዊ ቡድን የማውቃቸው ሲሆን ከሜዳ ውጪ ባለ ማህበራዊ ህይወትም ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ይህ ሁኔታ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመመለስ እንድወስን አድርጎኛል፡፡ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ5 አመት በኋላ ብመለስም የእንግድነት ስሜት አልተሰማኝም፡፡ ›› ይላል፡፡

በጃንዋሪ የዝውውር መስኮት ከግብጽ እና ዱባይ ክለቦች ጋር ድርድር እደረገ የነበረው ሳላዲን ያለፈውን አንድ አመት ከግማሽ በእግርኳስ ህይወቱ አስቸጋሪ ከሚባሉ ወቅቶች የሚመደብ ጊዜ አሳልፏል፡፡ በታላቁ ክለብ አል አህሊ ጉዳት እና የመሰለፍ እድል ማጣት ወደ ኤም ሲ አልጀርስ ሲያስገድደው በአልጀርሱ ክለብም ሁኔታዎች ከሳላዲን በተቃራኒው ቆመዋል፡፡

‹‹ አምና እና ባለፉት 6 ወራት ጥሩ ጊዜ እንዳላሳለፍኩ አውቃለሁ፡፡ የገጠሙኝ ሁኔታዎች ከባድ ነበሩ፡፡ አሁን ጥሩ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ያንን አስቸጋሪ ወቅት ለመርሳትም ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ››

በቻምፒዮንስ ሊግ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቶ ወደ ሲሸልስ የሚያመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሴንት ሚሼል ጋር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ሳላዲንን ባለማስመዝገቡ ምክንያት የግብ አዳኙን አገልግሎት አያገኝም፡፡ ነገር ግን ፈረሰኞቹ ወደ ሁለተኛው ዙር የሚሻገሩ ከሆነ የወቅቱን የአፍሪካ ታላቅ ክለብ ቲፒ ማዜምቤን በሚገጥሙበት ጨዋታ ማስመዝገብ ይችላሉ፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው ሁለት ጊዜ በቻምፒዮንስ ሊጉ ቅድመ ማጣርያ ላይ የተጫወተው ሳላዲን ፈረሰኞቹ በቻምፒዮንስ ሊጉ ረጅም ርቀት እንዲጓዙ ለመርዳት እንደተዘጋጀ ይናገራል፡፡ ‹‹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በርካታ መልካም ጊዜያቶች አሳልፌያለሁ፡፡ የሊጉን እና የጥሎ ማለፉን ዋንጫዎች አሳክቻለሁ፡፡ በሴካፋ ውድድር እስከ ፍፃሜ ደርሻለሁ፡፡ በግሌም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ አጠናቅቄያለሁ፡፡ አሁን ህልሜ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በቻምፒዮንስ ሊጉ ብዙ ርቀት መጓዝ እና የሴካፋ ዋንጫ ማንሳትን ነው፡፡›› ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

ያጋሩ