“ኤልፓን ከመውደዴ የተነሳ ለበሽታ ተዳርጌያለሁ ” አንጋፋው የኤሌክትሪክ የልብ ደጋፊ በቀለ ሄኒ (ኮረንቲ)

ውድ የሶከር ኢትዮጵያ ቤተሰቦች! የሜዳው ድምቀት የሆናችሁትን እናተን ደጋፊዎችን አሳታፊ ለማድረግ በማሰብ አሁን ደግሞ የደጋፊዎች ገፅ በሚል ሳምንታዊ አምድ ከፍተናል። በዚህ አምድ ውስጥ ደጋፊዎች በእግርኳሱ ከትናንት እስከ ዛሬ የነበራቸው ሚና ይዳሰሳል። አስተማሪ፣ አሳታፊ፣ አቀራራቢ የሆኑ አዝናኝ እና አሳዛኝ ትውስታዎች ይቀርቡበታል። በዛሬው የመጀመርያ ፁሁፋችን አንጋፋ ከሚባሉ ደጋፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት፤ ውጤት ኖረ አልኖረ የሚወዱትን ክለብ ከ40 ዓመታት በላይ በታማኝነት ያላቸውን እየሰጡ ሲደግፍ የቆዩትን አንጋፋ ደጋፊ ልናነሳ ወደድን። አሁን ህመም እና ድካም ተጫጭኗቸው አልፎ አልፎ ወደ ሜዳ ብቅ ካላሉ በቀር ብዙም አይገኙም። በቀለ ሄኒ (ኮረንቲ) በደጋፊነት ዘመናቸው ደስታቸውን፣ ያዘኑበትን አጋጣሚ ያለውን ሀሳብ አካፍለውናል። እንዲህ አቅርበነዋል።

መብራት ኃይልን የደገፉበት ምክንያት እንዴት ነበር?

ኤልፓን ለመደገፍ ያነሳሳኝ ምክንያት… እግርኳስን እወዳለው። የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ለመከታተል ስታዲየም እገባ ነበር። በወቅቱ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ስለነበርኩ ለምን የምሠራበትን መሥሪያ ቤቴን ክለብ አልደግፍም ብዬ ነፍሱን ይማረው እና ፍቃደ ሙለታ እና ሌሎች ምርጥ ተጫዋቾችን እያየሁ ነው ኤልፓን መደገፍ የጀምርኩት። ደጋፊም ሆኜ ወደ ሜዳ መምጣት የጀመርኩት ከ1968 ጀምሮ ነው። ይሄው እስከዛሬ የምወደውን ኤልፓን በመደገፍ ላይ እገኛለው። ከዛ በፊት የምደግፈው ማንም ክለብ አልነበረም። እውነት ለመናገር ግን ባለቤቴ ቡና እና ሻይ ስለምትሰራ ሁለተኛ ክለቤ አድርጌ ቡናን እደግፍ ነበር። ግን ከክለቤ ኤልፓ በላይ ግን መቼም ቢሆን አልደግፍም። በኃላም ቡድኑ እየተጠናከር እነ ኤልያስ ጁሀር፣ ሁለቱ አንዋሮች፣ ጠንክር አስናቀ፣ ዮርዳኖስ ዓባይ ሌሎቹም ሲመጡ የበለጠ ክለቤን እየወደድኩት መጥቻለው።

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ የቀድሞ ቦታችሁን (የአሁኑ ሚስማር ተራ) ቦታ ለቀው የምድር ጦር ደጋፊዎችን ቦታ ሲቀላቀሉ በፊርማ ነው ይባላል። ታሪኩ እንዴት ነው ?

አስቀድሞ የኤልፓ ደጋፊዎች በተለያየ የስታዲየሙ ቦታ ተበታትነው ነበር የሚደግፉት። በኃላ የልብስ መስፊያ (መኪና) አለችኝ፤ በእርሷ አርማ እየሰፋሁ የተለያዩ ምልክቶችን እያዘጋጀሁ አሁን ሚስማር ተራ በሚባለው አካባቢ ደጋፊ አሰባስቤ መደገፍ ጀመርኩ። ከብዙ ጊዜ በኃላ ደጋፊዎች በተወሰነ መልኩ እየጨመሩ ቢመጡም በኃላ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እየሰፉ፣ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ ቦታዬን ተቀራመቱኝ። እኔም እዛ ቦታ ላይ ሠላም አላገኘሁም ይተናኮሉኝ ጀመር። ከዚህ በላይ በቃኝ ብዬ ከቦታዬ ብድግ ብዬ ምድር ጦር (መቻል) ቦታ ጋር ሄድኩኝ። አሁን የምደግፍበት ቦታ ማለቴ ነው። በዚህ ቦታ አስቀድሞ በርከት ያሉ የሠራዊቱን ልብስ ለብሰው የሚደግፉ የጦሩ ደጋፊዎች ነበሩ። እነርሱ ጋር ጠጋ ብዬ ይህንን ቦታ ለምድነው በጋራ የማንጠቀመው ብዬ ጠየኳቸው፤ እነርሱም እሺ አሉ። አንድ አስጨፋሪ ነበራቸው፤ እርሱን ቃል ግባ ብዬ ሜዳ ላይ ወስጄ ህዝብ እንዲይ አድርጌ ” ከዛሬ ጀምሮ ከበቀለ ኮረንቲ ጋር በዚች ቦታ በጋራ በመሆን የምደግፍበት ቦታ ነው።” ተባብለን ህዝብ እያየ ተፈራረምን። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የቦታ ለውጥ አድርጌ አሁን የማስጨፍርበት ቦታ ሆኛለው። ከዚህ በኋላ ከኪሴ ገንዘብ አውጥቼ አርማ በመዘጋጀት ደጋፊ ማብዛት ጀመርኩ። ደጋፊውም በዛ፤ ብዙ የኤልፓ ማልያ አሰርቼ ስታዲየም አመጣለው፤ ክለባችንን ደግፈን ስንጨርስ ማልያውን ሰብስቤ አንድ ሸንጣ ነበረኝ በእርሱ እያስቀመጥኩ እያመላለስኩ ደጋፊውን ማስተባበር… እንግዲህ የእኔ ትልቁ ስራ ይሄ ነበር።

ኤልፓን መደገፍ ከጀመሩ ጀምሮ በጣም የሚያደንቁት ተጫዋች ማነው ?

ኡ! በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ብዙ ተጫዋቾች አሉ። በችሎታቸው ያስደሰቱኝ የምወዳቸው እኔ ብቻ ሳልሆን የኢትዮጵያ ህዝብም የሚወዳቸው አሉ። ሆኖም ነገረኝ ካልከኝ ኤልፓን ማየት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ የሚያስደንቁ ተጫዋቾችን ብመለከትም ኤልያስ ጁሀር፣ ዮርዳኖስ ዓባይ (ቡሎ)፣ ሁለቱ አንዋሮች እና አፈወርቅ ኪሮስ ለእኔ ልዩ ተጫዋቾች ናቸው።

በአንድ ወቅት ዮርዳኖስ ዓባይ ከኤልፓ ሊለቅ ሲል “ዮርዳኖስ አይሄድም፤ ቤቴን ሸጬም ቢሆን አስቀረዋለው።” ብለው ነበር? ቤቱን ሸጠው ዮርዳኖስን አስቀሩት? የቡና ደጋፊዎች በዚህ ንግግርዎ የቀለዱትን ያስታውሳሉ? እስኪ ጊዜውን አስታውሰው ይንገሩን ?

(እየሳቁ) የእግርኳስ ውበቱ ይሄ ነው። አየህ እኔ። በጊዜው ለክለቤ በነበረኝ ተቆርቋሪነት እና ዮርዳኖስን እወደው ስለነበረ በሌላ ማልያ ላለማየት የተናገርኩት ነው። በጊዜው አስታውሳለው ዮርዳኖስ ዓባይን ጊዮርጊስ እና ቡና ይፈልጉት ነበር ። እንዲሁም ኃይሉ አድማሱንም (ቻይና) ሊወስዱ ሲሉ ምን አልኩ “ቤቴንም ቢሆን ሸጬ አይሄድም” ብዬ ተናግሬያለው። እውነትም ደግሞ ከባለቤቴ ጋር ተመካክሬ ቤቱን ሸጠን ገንዘቡን ለመመለስ ሀሳቡ ሁሉ ነበረን፤ አልተሳካም እንጂ። ከዚህ በኃላ ቡና እና ኤልፓ ሲጫወቱ የቡና ደጋፊዎች የሆኑት አዳነ ሽጉጤ እና አሰግድ (ቼሪ) ስታዲየም ውስጥ “ቤቱ የቀበሌ ነው” ብለው ቢቀልዱብኝም ያው ደስ ይላል በወቅቱ ብዙውን ያዝናና ገጠመኝ ነበር። ዋናው እኔ ለክለቤ ያለኝን ተቆርቋሪነት ለማሳየት በአንድ ሚዲያ የተናገርኩት ነው።

ኤልፓን በደገፉባቸው ዘመናት በጣም የተደሰቱበት ጊዜ መቼ ነው ?

ብዙ ጊዜ ተደስቻለው፤ የዛሬን አያድርገውና! ኤልፓን መደገፍ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ከህይወቴ የማይጠፋ ደስታን አጣጥሜለው። በተለይ በሰማንያዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ዘጠናዎቹ መጀመርያ ድረስ ዋንጫዎችን ያግበሰበስንበት እጅግ የማይረሳ ልዩ ዘመን ነበር። በ1993 ሦስት ዋንጫ በዓመት ውስጥ ያነሳንበት፣ በ1990 የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳንበት ለእኔ ልዩ ትዝታ አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ የኳስ ችሎታቸው አጨዋወታቸው ብዙዎችን ይማርክ ነበር። ለዓመታት ጥቂት ደጋፊዎች ነበርን። በኃላ ቁጥራችን እየጨመረ መጥቶ ነበር። አሁን እየተመናመነ ብዙዎችም እየሸሹ ቢመጡም።

በጣም ያዘኑበት ጊዜስ ?

ምን ጥያቄ አለው! ይህ ብዙ ትውልድ ያፈራ ታሪካዊ ክለብ የወረደበት ቀን ነዋ። የማላውቀው በሽታ ሁሉ ይዞኛል። በጣም አዝናለው። መውረድ የሌለበት ኤልፓ በተለያዩ ምክንያቶች ወረደ። እጅግ ያሳዝናል። የወለድኩት ልጄ ያህል የምወደው፣ ብዙ እውቅና ስም ያተፈኩበት ክለቤ መጨረሻው ይሄ ሲሆን ቆሞ ማየት ስሜቱ ከባድ ነው።

መብራት ኃይል አሁን ያለበት ደረጃ ያሳስብዎታል ?

እንዴት አያሳስበኝ? እንቅልፍ ሁሉ ይነሳኛል። ኤልፓ አሁን ያለበትን ደረጃ ስመለከት አዝናለው። ኤልፓ መውረድ የማይገባው ቡድን ነበር። በጣም ነው የተሰማኝ። ከኮሚቴዎቹ ጋር ብዙ ተነጋገርኩ ፣ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፣ በአቅሜ ሽልማት እየሸለምኩ ተጫዋቾቹ ክለቡ እንዳይወርድ ለማነሳሳት ሁሉ ሞከርኩ፤ አልሆነም። የወቅቱ የክለቡ የበላይ ጠባቂ ዶ/ር ምህረት ደበበ ብዙ ጥረት አደረጉ አልተሳካም። ይህ ታሪካዊ ክለብ በመውረዱ በጣም አዘንኩ። የሌለብኝ በሽታ ሁሉ ያዘኝ በዚህም አሁን ታምሜ ህመሜን እያስታመምኩ እገኛለሁ። የክለቡ ኃላፊዎችም ደጋፊዎችም እየመጡ ይጠይቁኛል።

አሁን ክለቡ ቢወርድም ታች ወርደው (ከፍተኛ ሊግ) ይመለከታሉ ?

አሁን ክፍለ ሀገር ሄጄ ባልደግፍም ህመሙም ስላለብኝ አዲስ አበባ ሲሆን ጨዋታውን አያለው፤ እከታተላለው። ግን ብዙም የሚያስደስት አይደለም። ለክለቡ የማልያ ፍቅር የሌላቸው ተጫዋቾች አያለው። ወደ ፊት የቀደሞ ስሙ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አድርጋለው። እኔ ግን ከኤልፓ መቼም አልለወጥም። መብራት አርማዬ ነው። ከህመሜ አሁን እያገገምኩ ነው። ወደ ፊት ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ጥረት አደርጋለው።

እስኪ የድሮና የአሁኑን ደጋፊዎች ያነፃፅሩልኝ ?

የዚህ ዘመን ደጋፊ እና የድሮውን ለማነፃፀር ከባድ ነው። አሁኑ ጥሩ ደጋፊዎች አሉ። አዲስ አበባም በክልልም የመጡ አዳዲስ ደጋፊዎች እየተመለከትኩ ነው። ይህ ጥሩ እና ሊበረታታ የሚገባ ነገር ነው። ሆኖም አቋም የላቸውም። የድሮዎቹ እስከ መጨረሻው ለክለባቸው ውጤት ኖረ አልኖረ ታማኝ ናቸው። የአሁኖቹ ውጤት ተኮር ናቸው። ውጤት ካለ ይደግፋሉ ውጤት ሲርቅ ሁለቴ ቡድናቸው ሲሸነፍ ከሜዳ ይሸሻሉ። አንተ እውነተኛ ደጋፊ ከሆንክ ሲወርድ አብረህ መውረድ አለብህ። ሌላው ለእግርኳስ የማይጠቅሙ አንዳንድ ነገሮች አያለው፣ እሰማለው ይህን ማቆም አለባቸው። በኤልፓም አንጀቴን ያቆሰለኝ ይሄ ውጤትን ብቻ ፈልገው ይመጡ እና ውጤት ሲያጡ የሚሸሹ መብዛታቸው ነው።

የቤተሰብ ህይወት ምን ይመስላል? እንደ አባታቸው እነርሱም ደጋፊ ናቸው ?

ስምንት ልጆች አሉኝ፤ አራት ወንድ አራት ሴት ልጆች። ከአንዱ በቀር ሁሉም አግብተው ትዳር መስርተው እየኖሩ ነው። የቤተሰቤ አባላት ሁሉም ኳስ ይወዳሉ። ሜዳ ይገባሉ የሚደግፉት ክለብ አላቸው። የቡና፣ የኤልፓ እና የጊዮርጊስ ደጋፊ ናቸው። አንዳንዴም ከጨዋታ በኃላ በበሰለ መንገድ እንከራከራለን፣ እንጨቃጨቃለን ፣ እንጫወታለን። ባለቤቴ ከድሮም ጀምሮ የቡና ደጋፊ ናት።

በመጨረሻም መልዕክት ካለዎ ?

ኤልፓ ብዙ ሰው ያወኩበት፣ ትልቅ ስምና ክብር ያገኘሁበት፣ በሽታ ሳይቀር የተያዝኩበት እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ውጤት ራቀ ብዬ የማርቀው የምደግፈው ክለቤ ነው። ለሀገራችን ሠላም እመኛለው። ይህን ክፉ በሽታም ያርቅልን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ