ዕድሉ ደረጄ የአውሮፓ የአሰልጣኞች ስልጠናን መውሰድ ጀመረ

በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ያሳካውን ስኬት በአሰልጣኝነቱም ለመድገም እየተንደረደረ የሚገኘው ዕድሉ ደረጄ በአውሮፓ ከፍተኛ የሆነውን ስልጠና መውሰድ ጀምሯል።

እግርኳስን ካቆመ በኋላ የተለያዩ የአሰልጣኞች ስልጠናን በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር እየወሰደ የሚገኘው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አንበል ዕድሉ ደረጄ ስኮትላንድ ከሚገኘው One 10 sport ኮሌጅ ጋር በመነጋገር ነው የስኮትላንድ እግርኳስ ማኅበር ስፖንሰር ያደረገው የአውሮፓ “ሲ” ላይሰንስን ለመውሰድ ስልጠና የጀመረው።

ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የተቋሙ ሌላኛው ቅርንጫፍ የስድስት ቀን የኦንላይን የቅድመ ስልጠናው የወሰደው ዕድሉ ትምህርቱን ለስድስት ቀን በመውሰድ በስኬት አጠናቆ የዕውቅና ምስክር ወረቀት የወሰደ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ የአውሮፓ “ሲ” ላይሰንስ ትምህርትን ከሰኔ 28 ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በንድፈ ሀሳብ ከወሰደ በኋላ በ2021 ወደ ስኮትላንድ በማቅናት የተግባር ትምህርቱን የሚወስድ ይሆናል። እነዚህን ትምህርቶች በብቃት ካጠናቀቀም የአውሮፓ ሲ ላይሰንስን የሚያገኝ ይሆናል። በዚህ እንደማያበቃ የሚናገረው ዕድሉ እስከ መጨረሻው ላይሰንስ ድረስ ለመውሰድ ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳለው ነግሮናል።

የአውሮፓ ላይሰንስ በአገራችን አሰልጣኞች ዘንድ እምብዛም በማንመለከትበት በዚህ ወቅት ዕድሉ ደረጄ በራሱ ተነሳሽነት ባደረገው ግኑኝነት ይህን ስልጠና ለማሳካት የሄደበት ርቀት ለብዙዎች አርዓያ የሚሆን ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ