” በትልቅ ደረጃ መጫወት እፈልጋለሁ”
ትውልድ እና እድገቱ ባህር ዳር ከተማ፣ ህዳር 11 የተባለ ሰፈር ነው። እግር ኳስን በፉትቦል ባህርዳር ጀምሮ በታዳጊ ቡድን ደረጃ በአውሥኮድ እና ደደቢት የተጫወተው ይህ ተከላካይ በዚህ ወቅት በወልዋሎ የሚገኝ ሲሆን በተከላካይ ቦታ ላይ ተስፋ ካላቸው ተጫዋቾ አንዱ ነው።
የአማራ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ መኖርያ ካደገበት መንደር በቅርብ ርቀት መኖሩ እግር ኳስ ተጫዋች እንዲሆን ተፅዕኖ እንዳሳደረበት የሚገልፀው ዳዊት በአውሥኮድ ታዳጊ ቡድን ቆይታው አማራ ክልልን ወክሎ በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፏል። ባለፈው ዓመት የደደቢት ቆይታው ከተለያዩ የመሐል ክፍል ተጫዋቾች በመጣመር ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው ይህ ተከላካይ በውድድር ዓመቱ ከጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር በቋሚነት ተሰልፎ ተጫውቷል።
ከደደቢት ጋር በግሉ ጥሩ ጊዜ ካሳለፈ በኃላ በዓመቱ መጀመርያ ወደ ወልዋሎ በማምራት ከነባር የመሐል ተከላካዮች ጋር ብዙ ልምድ እንደወሰደ የሚገልፀው ዳዊት ክለቡ በርካታ ተከላካዮቹን በጉዳት ባጣበት ወቅት የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል ካገኘ በኃላ ከዕድሜው አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል።
ከሶከር ኢትየጵያ ጋር አጭር ቆይት የነበረው ይህ ተከላካይ የታዳጊ ቡድን ቆይታው እና የዋናው ቡድን ቆይታዎቹ እንዲ ይገልፃቸዋል።
” የእግር ኳስ አጀማመሬ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰፈር ውስጥ ነው፤ እንደ አጋጣሚ ግን ከቤታችን አጠገብ የአማራ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ ልምምድ ይሰራ ነበር። ከጊዜ ሒደት በኃላ ከተጫዋቾቹ ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። ወደ ልምምድ ቦታም ይዘውኝ ይሄዱ ነበር። በዛ አጋጣሚ ነው በደምብ ወደ እግር ኳስ የገባሁት። ከዛ በኃላ ወደ ፉትቦል ባህርዳር የሚባል የታዳጊዎች ፕሮጀክት ገባሁ በ2005 ደግሞ አማራ ክልል ወክዬ ሻሸመኔ በተዘጋጀው የታዳጊዎች ውድድር ሄድኩ። እዛም ጥሩ ቆይታ ነበረን ኪሩቤል ኃይሉም የቡድናችን አባል ነበር። ከዛ ከተመለስኩ በኃላ ደግሞ በ2006 አውሥኮድ ታዳጊ ቡድን አሳለፍኩ፤ የአውሥኮድ ጊዜዬም በጣም አሪፍ ነበር።
” በ2007 ደደቢት ታዳጊ ቡድን የምቀላቀልበት አጋጣሚ አገኘሁ። የታዳጊ ቡድን አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም ነበር ክለቡ እንድቀላቀል ያደረገው። እኔም ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። አዲስ አበባ ቤተሰብ እንደሌለኝ ለኤልያስ ነገርኩት፤ እሱም ሁሉም ነገር እንደሚያመቻችልኝ ነገረኝ። በትንሽ ግዜ ቆይታዬ ግን የአዲስ አበባ ኑሮ አልተመቸኝም፤ ወደ ባህርዳር ተመለስኩ። ባህርዳር ብዙ አልቆየሁም አዲስ አበባ ተመለስኩ እና ታዳጊ ቡድን እየተጫወትኩ ቤት ተከራይቼ መኖር ጀመርኩ። በዛን ሰዓት ገና ልጅም ስለነበርኩ የአዲስ አበባ ኑሮ ከብዶኝ ነበር። በታዳጊ ቡድን አሪፍ ቆይታ ነበረኝ፤ የታዳጊዎች ዋንጫም ያሸነፍምበት ወቅትም ነበር። እስከ 2009 መጀመርያ በታዳጊ ቡድን ቆየሁ። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በድጋሚ ደደቢት ይዞ ለዝግጅት ወደ መቐለ ሲሄድ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት ጀመርኩ። በዛ ሰዓት ከሀገሪቱ ትላልቅ ተጫዋቾች ልምምድ መስራት ትልቅ ዕድል ነበር ። በዛ ዓመት ከዋናው ቡድን ልምምድ ሰርቼ በታዳጊ ቡድን ወርጄ የመጫወት እድል ተሰጠኝ። ያ ወቅት በእግር ኳስ እድገቴ ትልቅ ቦታ ነበረው፤ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር ልምምድ ማድረግ ትልቅ ነገር ነው።
በ2010 ነብሱን ይማረው ንጉሤ ደስታ ቡድኑ ሲረከብ በተሻለ ከዋናው ቡድን ጋር የማሳለፍ ዕድል ነበረኝ ፤ ብዙ ልምድ የወሰድኩበት ደረጃዬን ከፍ ያደረግኩበት ጊዜ ነበር። በ2011 ደደቢት ከበፊት አሰራሩ ለውጥ ሲያደርግ ሙሉ በሙሉ የዋናው ቡድን አባል ሆኜ ብዙ ጨዋታዎች ያደረግኩበት፤ አቅሜን አውጥቼ የተጫወትኩበት ነበር። በርግጥ በ2010 መጨረሻ ለዋናው ቡድን ሁለት ጨዋታዎች አድርጌ ነበር። በ2011 የታዳጊ ቡድን አሰልጣኞቻችን ቡድኑን ሲይዙት ግን ብዙ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፌ ተጫውቻለው። ቡድኑ በጣም አሪፍ ቡድን ነበር። በውጤት ደረጃ የሚፈለገው ነገር ባናመጣም የኳስ ቁጥጥር ተበልጠን የተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች ጥቂት ናቸው። ዕድሜያችን ተመሳሳይ ስለነበር የቡድናችን ስሜትም ጥሩ ነበር ፤ ሁላችንም ራሳችም ለማሳየት አሪፍ እንቅስቃሴ ያሳየንበት ዓመት ነበር።
በ2012 ደግሞ በታዳጊ ቡድን እያለሁ የሚያውቀኝ እና ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እንድሰራ ዕድሉ የሰጠኝ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወልዋሎን ሲረከብ ለወልዋሎ የመፈረም ዕድል አገኘሁ። በመጀመርያ አከባቢ ትላልቅ ተከላካዮች ያሉበት ክለብ ስለሆነ በቂ የመሰለፍ ዕድል አልነበረኝም። በመጨረሻ አከባቢም የመሰለፍ ዕድሉ አግኝቼ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቻለው። አሰልጣም ዘማርያም ከመጣ በኃላም እምነት አሳድሮብኝ በወሳኝ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድሉ ሰጥቶኛል። በቀጣይም በትልቅ ደረጃ መጫወት እፈልጋለሁ ፤ በብሄራዊ ቡድን መጫወት የቀጣይ እቅዴ ነው።
ለዚ ደረጃ እንድደርስ የረዱኝን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ ፤ በተለይም የምወዳት እናቴን ወጣትነትዋን መስዋዕት አድርጋ እዚ ደረጃ ላይ አድርሳኛለኝ። በወጣት ቡድን ያሰለጠኑኝን ሁሉም አሰልጣኞች ፤ በወልዋሎ ዕድል የሰጡኝ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ማመስገን እፈልጋለው። ውለታ የዋሉልኝ ስማቸውን ጠርቼ አልጨርሰውም በሕይወቴ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ