በሕይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞውና በበርካቶች ዘንድ የምንጊዜም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን ይዘን ቀርበናል። በዚህ ፅሁፍ ከቋራ የተነሳው መንግሥቱ ወርቁ እንዴት እግር ኳስን እንደተዋወቀ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደተገናኘ እንዲህ እናስቃኛችኋለን።
ማስታወሻ፡ በገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በመፅሐፍ መልኩ የተዘጋጀውና ከመንግሥቱ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እንደ ዋንኛ የመረጃ ግብዓት ተጠቅመናል።
መንግሥቱ ወርቁ የተወለደው ቋራ ልዩ ስሙ ዮፍታ ጊዮርጊስ የሚባል ቦታ ነበር። የጀግና ልጅ ጀግና እንዲሉ የሜዳ ላይ እልኸኝነቱ እና አልሸነፍ ባይነቱን ላስተዋለ ከወላጆቹ የወረሰው አንድ ነገር እንዳለ የእናት እና የአባቱ ህይወት ማሳያ ይሆናል። አባቱ እሱ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ቅፅበት ድረስ ጫካ ገብተው ጣልያንን በመዋጋት ነበር ያሳለፉት። ወላጅ እናቱም አባቱን አሳልፈው ባለመስጠታቸው በተመሳሳይ በጠላት ታስረው ከእስር እስከማምለጥ የሚደርስ ታሪክ ነበራቸው። መንግስቱ የሚለውን ስያሜም ያገኘው በጣልያኖች አማካይነት ከእናቱ ጋር እስር ቤት በነበረበት ወቅት ነው። ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስም ግን ‘አሻግራቸው’ ይሰኝ ነበር። የእናቱ እስር ባይኖር ኖሮ ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ፣ ስኬታማው ተጫዋች እና አሰልጣኝ ፣ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የእስከሁኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ‘አሻግራቸው ወርቁ’ ይባል ነበር።
ጠላት ከሀገር ወጥቶ ንጉሱ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የፊት አውራሪ ወርቁን አደራ ይወጡ ዘንድ ከእናቱ ጋር በብዙው ተደራድረው መንግስቱን ወደ አዲስ አበባ አስመጡት። የቤተ መንግስትን ህይወት ቀስ በቀስ እየለመደ የመጣው ትንሹ መንግስቱ እስከዚህ ወቅት ድረስ ስለ እግር ኳስ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም። ቀሪ ዘመኑን ሙሉ ያሳለፈበትን ተወዳጁን ስፖርት ለመተዋወቅ ትምህርት ቤት መግባት ነበረበት። በወቅቱ ‘የባላባት ትምህርት ቤት’ ይባል የነበረው እና ከጊዜ በኋላ ‘መድኃኒያለም’ ወደተሰኘው ትምህርት ቤት ገብቶ መማር በጀመረበት ወቅት በአሜሪካዊ አስተማሪው አማካይነት ነበር ኳስን ያወቃት ፤ ከዚህ በኋላም መንግስቱን ከኳስ መለየት ከባድ ሆነ። በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በእረፍት ቀናቱ ቅዳሜ እና እሁድም ከቤተ መንግስት በጠዋት ጠፍቶ ርቆ በመሄድ እስኪመሽ ድረስ ኳስ በመጫወት ያሳልፍ ነበር። መንግስቱ ከእግር ኳስ ባለፈም አጠር በሚል ቁመቱ ቅርጫት ኳስ ጭምርም ይጫወት ነበር። ምንአልባትም በኋላ ላይ የግንባር ኳሶችን በቁመት ከሚበልጡት ተከላካዮች በላይ እየዘለለ ማስቆጠር ቀላል ያደረገለት ይሄ ልምዱ ሊሆን ይቻላል።
መንግሥቱ በዕድሜ ትንሽ ከፍ ሲል ከጓደኞቹ ጋር አንድ ቡድን መሰረቱ። የቡድኑን ጥሩነት የተመለከቱ የወቅቱ የመርካቶ ልጆች ቡድኑን ተከራይተው ለግጥሚያ ይወስዱት ነበር ፤ በአሁኑ ቋንቋ ‘ስፖንሰር’ እንደማድረግ። መንግስቱ እና ጓደኞቹም በለሊት ከጅብ ጋር እየተጋፉ ጉገሌ አባሲዮን ሜዳ በመሄድ ስፖንሰር አድራጊዎቻቸው በሚያሲዙት ገንዘብ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ከተለያዩ ቡድኖች ጋርግጥሚያዎችን ያደርጉ ነበር። በዚህ ጊዜም ነበር መንግስቱ ሙሉ የተጫዋችነት ዘመኑን ያሳለፈበት የጊዮርጊስ ቡድን ጉለሌ ራስ ኃይሉ ሜዳ ልምምድ ለማድረግ ሲመጣ እየጠበቀ መመልከት የጀመረው። ልባሙ መንግስቱ በጊዮርጊስ የአይን ፍቅር ይለከፍ እንጂ ከጓደኞቹ ጋር የመሰረተው የትምህርት ቤት ቡድን ውስጥ ሆኖ እነ ይድነቃቸው ተሰማ ፣ ዘውዴ ሳሙኤል ፣ ነፀረ አሸናፊ ፣ ፈለቀ ኃይሉ እና ሌሎችንም የያዘውን ጊዮርጊስን መግጠም አልፈራም። በተማሪዎቹ ሀሳብ አቅራቢነት መነሻ በተደረገው ጨዋታም የነመንግስቱ ቡድን ጊዮርጊስን 2-1 አሸነፈ። መንግስቱ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ጊዮርጊስም ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርት ቤት ቡድን ተሸነፈ። ይህ አጋጣሚም ቅዱስ ጊዮርጊስ የምን ጊዜም ምርጡ ስምንት ቁጥሩን ወደ ቡድኑ እንዲቀላቅለው አደረገው።
በወቅቱ ክረምት ገብቶ መንግስቱ ከቋረ መጥተው የሚጠብቁትን ቤተሰቦቹን ጥየቃ ንጉሱ በሚያዘጋጁለት የአውሮፕላን ትኬት ወደ ጎንደር ሊያቀና ሲል በሁለት የጊዮርጊስ ተጫዋቾች አግባቢነት ከጉዞው ቀርቶ ከቡድኑ ጋር ለአንድ ጨዋታ ወደ ድሬዳዋ ሄደ። ድሬዳዋ ላይ ጊዮርጊስ ከኮተን ጋር ሲጫወት መንግስቱ ተጠባባቂ ሆነ። ነገር ግን ቡድኑ 3-1 መመራት ጀመረ። ከቤተሰብ ጥየቃ ቀርቶ ድሬዳዋ ድረስ መጥቶ ተጠባባቂ መሆኑ እልህ ውስጥ የከተተው መንግስቱ በመጨረሻ በሰባት ቁጥር ቦታ ላይ ተቀይሮ የመግባት ዕድል ገጠመው። ማንነቱን ለማሳየት የጓጓው ታዳጊም ዕድሉን አላባከነም ሦስት ግቦችን አስቆጠረ። ይህ ችሎታው ሲታይ ምንም እንኳን ለአንድ ጨዋታ ብለው ቢሆንም ከአዲስ አበባ ያመጡት ከድሬዳዋ በቀጥታ ወደ ናዝሬት ወሰዱት። በናዝሬትም ፖሊስ ፣ ጦር ሰራዊት ፣ ኦሎምፒያኮስ ፣ ጁቬንቱስ ፣ ዳኘው እና ሌሎች የወቅቱ ትላልቅ ቡድኖች ጋር በነበረው የክረምት ውድድር ላይ የካፋይ ሆነ። በውድድሩ በትላለቆቹ ቡድኖች ላይ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው መንግስቱ አዲስ አበባ ላይ አንድም ጨዋታ ከማድረጉ በፊት ስሙ በእግርኳሱ አካባቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታዋቂ ሆነ። በዚህ መልኩም ስኬታማውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታውን ጀመር። ይህ የሆነው 1949 ክረምት ላይ ነበር።
ይቀጥላል
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ