የቤተሰብ አምድ | ከኳስ ሜዳ ሠፈር የተገኘው ቤተሰብ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ከአንድ ቤተሰብ ወጥተው የስኬት መንገድን የተጓዙ በርካታ ተጫዋቾችን ተመልክተናል፡፡ በዛሬው የቤተሰብ አምዳችንም በሁለቱም ፆታዎች ሦስቱን አባላቱን ለስፖርቱ ያበቃውን የኳስ ሜዳውን ቤተሰብ እናያለን፡፡

የቤተሰቡ ልጆች ቁጥር ስምንት ነው ፤ አራት ወንዶች አራት ሴቶች፡፡ አምስቱ ከእግር ኳስ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ቢኖራቸውም በተለይ ሦስቱ ግን ዛሬም ድረስ እንጀራቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡ ትውልድ እና ዕድገታቸው በመዲናችን አዲስ አበባ መሳለሚያ እግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት በማይታማው ‹ኳስ ሜዳ› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የአቶ ቦጋለ ልጆች ወይንም ከቤቱ በእግር ኳሱ ከፍ ያለ ደረጃ በደረሰው ብርሀኑ ቦጋለ ተቀፅላ ስም በሚታወቀው የፋዲጋ ቤተሰብ ውስጥ ብርሀኑ ቦጋለ ከታላቅ ወንድሙ ደረጄ ጋር በመሆን በአካባቢው በሚገኝ ፕሮጀክት ውስጥ መጫወት ቢጀምሩም ደረጄ ዕድሜህ አልፏል በሚል ከፕሮጀክቱ የመቀነስ ዕጣ ይገጥመዋል፡፡ የእሱ ታናሽ የነበረው ብርሀኑ ግን ዕድሜው ገና ለጋ በመሆኑ በቡድኑ ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ ከብርሀኑ ቦጋለ ጎን ለጎን ከሠናይት ታላቅ የሆነች እህታቸው ገነት ቦጋለም ኳስን በተወሰነ መልኩ ተጫውታ ያሳለፈች ሲሆን የሱን ፈለግ በደንብ በመከተል ዛሬም ድረስ የዘለቁት ግን ታናሽ እህቱ ሠናይት ቦጋለ እና በአሁኑ ሠዓት በአንደኛ ሊጉ ክለብ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እየተጫወተ የሚገኘው ፋሲል ቦጋለ ሲሆኑ እኛም የሦስቱን ስፖርተኞች የእግር ኳስ አነሳስ ተመልክተናል፡፡

<<ፋዲጋ>> በሚል ስያሜ የሚጠራው የመስመር ተከላካዩ ብርሀኑ እግር ኳስን ከሠፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን በኃይሌ ካሴ ፕሮጀክት ኃይሌ ወደ አሜሪካ ካቀና በኃላም በግርማ ደቻሳ በሚሰለጥነው ቡድን ውስጥ የልጅነት ጊዜው አሳልፏል፡፡ ብርሀኑ በዚህ ቡድን በነበረው ቆይታ መልካም የሚባሉ ዓመታትን በማሳለፉ ለአዲስ አበባ ምርጥ ተመርጦ መጫወት የቻለ ሲሆን ፈጣን ዕድገት እያሳየ በመምጣትም ወደ ኪራይ ቤቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክት አምርቶ ነበር፡፡ በቡድኑ መልካም ቆይታ የነበረው ይህ ወጣት የክልል ምርጥ የእግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ሲካሄድ ከመላው ሀገሪቱ ከመጡ ቡድኖች ጋር የራሱን ቡድን ወክሎ በመጫወት ላይ እያለ ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ናሚቢያ በተካሄደው ውድድር ላይ የመካፈል ዕድልን አግኝቷል፡፡

በብሔራዊ ቡድን ቆይታው ስኬታማ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻለው እና ራሱን እያበቃ የመጣው ብርሀኑ ከብሔራዊ ቡድን ጥሩ ግልጋሎት መልስ የያኔውን መብራት ኃይል የአሁኑን ኢትዮ-ኤሌክትሪክን በአሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴ ጥሪ መሠረት ተቀላቅሎ በክለቡ ረዘም ያለ ጊዜን አሳልፏል፡፡ “በኤልፓ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ፤ ወደ ስድስት ዓመታት ተጫውቼ አሳልፌበታለሁ፡፡ የዛን ጊዜ እኛ በኤልፓ እያለን ልዩ ቡድን ነበር፡፡ ለኔ ይሄን ስል በታዳጊዎች ላይ የነበረው ትኩረት ይገርመኛል፡፡ እኔም ወጣት በመሆኔ ለመጫወት ረጅም ጊዜን አልወሰደብኝም፡፡ አንድ ዓመት ብቻ ልጅ ነው ተብዬ አልተጫወትኩም እንጂ እስከወጣሁበት ዓመት ድረስ በቋሚነት ስጫወት ነበር፡፡ በኤልፓ ቆይታዬ እጅጉን ደስተኛ ነበርኩኝ፡፡” በማለት የመጀመሪያ ክለቡ የሆነው መብራት ኃይልን ያስታውሳል፡፡

ከ1990ዎቹ መጨረሻ እስከ 2002 በኢትዮ-ኤሌክትሪክ ቆይታ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ በመቀጠል ከ2003 እስከ 2010 ድረስ ለስምንት ዓመታት በደደቢት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ከመሆን አንስቶ በአምበልነትም ጭምር ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን 2005 ላይም የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከሰማያዊዎቹ ጋር አንስቷል፡፡ “አነሳሴ በኤልፓ ይሁን እንጂ ዋንጫን ያገኘሁት በደደቢት ቤት ውስጥ ነው ፤ ምርጥ ጊዜም ነበረኝ፡፡” ሲል በደደቢት ስኬቱ ደስተኛ መሆኑን ያነሳል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም ከወጣት እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ብርሀኑ በ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው ቡድን አካልም ነበር። ተጫዋቹ አምና ከደደቢት ከለቀቀ በኃላ ወደ ወልዋሎ ተጉዞ የአንድ ዓመት ቆይታን ያደረገ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ መድን ውስጥ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ከቤተሰቡ ቀድሞ ጥሩ ደረጃ ላይ በመገኘቱ ለታናናሾቹ አርአያ የሆነው ብርሀኑ ለታናሽ እህቱ ሠናይት ቦጋለ እና ወንድሙ ፋሲል ቦጋለ የእግር ኳስ ህይወት ፈር ቀዷል፡፡ ሠናይት ቦጋለ የታላቅ ወንድሟን ፈለግ ተከትላ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በሚገባ ለመታወቅ በቅታለች፡፡ ኳስን የጀመረችው በሠፈሯ ኳስ ሜዳ ውስጥ ነው፡፡ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ነበር የትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ራሷን በደንብ ማሳደግ የቻለችው፡፡

ሠናይት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ባደገችበት ወቅት በኮካ ኮላ ውድድር ላይ ትምህርት ቤቷን በመወከል ተሳታፊ ከሆነች በኃላ ቢኒ ትሬዲንግ እየተባለ ወደሚጠራው የሴቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ውስጥ ገብታ ተጫውታለች፡፡ ከዚህ የፕሮጀክት ቆይታዋ ቀጥላ ግን የገባችው በብዙዎች ዓይን ውስጥ ወደገባችበት ደደቢት ነበር፡፡ “ወደ ደደቢት ስገባ ከአጠገቤ የነበሩ አሪፍ አሪፍ ተጫዋቾች ስለነበሩ ከነሱ ብዙ ነገር እየተማርኩ አሰልጣኜም የሚሰጠኝ መመሪያ ጥሩ ስለነበረ ይሄን ያህል አልከበደኝም ፤ ቀለል ብሎኝ ነው የተጫወትኩት” ስትል ወደ ደደቢት የገባችበትን ጊዜ ታስታውሳለች፡፡

ታላቅ ወንደሟ ብርሀኑ በደደቢት የወንዶች ቡድን ሲጫወት ሠናይት ደግሞ ለሴቶች ቡድኑ ትጫወት ነበር፡፡ የዚህ ቤተሰብ የእግር ኳስ ጉዞ ሲቀጥልም ሦስተኛው የቤተሰቡ አባል የሆነው ወንድማቸው ፋሲል ቦጋለ በደደቢት የታዳጊ ቡድን የመጫወት አጋጣሚን ያገኘ ሲሆን በተወሰነ መልኩ 2009 ላይ ደግሞ ከብርሀኑ ጋር በዋናው የደደቢት ቡድን ውስጥ አብሮ በመጫወቱ ሦስቱም ሰማያዊውን መለያ የማጥለቅ ግጥምጥሞሽ ነበራቸው፡፡

“እኔ ከቤቱ ቀድሜ በመውጣቴ በተለይ ለሠናይት ትልቅ አድቫንቴጅ ሆኗታል፡፡ ከአነሳሷም ከልጅነቷ ነበር የጀመረችው፡፡ አሁን ያላት ብቃት ላይ እንድትደርስም እኔ በፕሮጀክትም ሆነ በክለብ ስጫወት በማየት ሁለተኛ በሠፈራችን ሜዳ ሲሆን በግላችን ስለምናገኝም ትንሽ ትንሽ ከእኔ ጋርም ትሰራ ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በኳሱ ጥሩ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ እሷ ደግሞ ትንሽም ስለሆነች የእኔን ነገር ትመለከታለች፡፡ እኔም የሚያስፈልጋትን አደርግላታለሁ፡፡ ቤተሰብም ጥሩ እገዛ ያደርግላታል ፤ ወንድሞቼም በደንብ ይረዷታል፡፡ በተለይ ታናሼ ፋሲል እና ታላቄም ያግዟታል፡፡ እኔም ያለፍኩበትን እነግራታለሁ፡፡ ጥሩ ደረጃ እንድትደርስ ስለምፈልግም ያለባትን ጉድለት እነግራታለሁ ፤ አንዳንዴም አሰራታለሁ፡፡ አሁን ወቅቱ የኮሮና ስለሆነም ከእኔ ጋር የምትሰራበት ጊዜ አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ቤተሰቦቼ ለሷ ሙሉ ድጋፍ እና ትኩረት ያደርጉላታል፡፡ እኔ ጥሩ ደረጃ በመድረሴ ቤተሰቦቼ ጫና ማንም ላይ አላሳደሩም፡፡ ነፃነት አለን በተለይ ለሷ፡፡” ሲል ብርሀኑ ቤተሰቡ ለእህቱ ሲያደርግላት ስለነበረው ድጋፍ ተናግሯል፡፡

ሠናይት በደደቢት ረጅም ጊዜን ከቆየች በኃላ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን አዳማ ከተማን የተቀላቀለች ሲሆን በክለቡ የመጀመሪያው ዓመት ቆይታዋም ልክ ከደደቢት ጋር እነደነበራት ጊዜ ሁሉ በአዳማም ጥምር ዋንጫን አጣጥማለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጫዋቿ አሁን ላይ የሉሲዎቹ ቁልፍ ተጫዋች መሆንም ችላለች። ታላቅ ወንድሟ ብርሀኑ ምንያህል እየደገፈ እዚህ እንድትደርስ እንዳደረጋት እና ከደደቢት ተስፋ ተገኝቶ በቢሾፍቱ ዘንድሮ ደግሞ በአዲስ ከተማ የአንደኛ ሊግ ቡድን የሚገኘው ፋሲል ቦጋለ ከጎኗ ሆነው እንደሚረዷት ስትናገር “ቤተሰቦቼ ብርሀኑ ትልቅ ደረጃ ደርሶ ሲያዩት እኔን አላገዱኝም፡፡ እንደሱ ትሆናለች ብለው ስለሚያስቡ ይሄን ያህል ጫና የለብኝም ነበር ፤ ያበረታቱኛል፡፡ እህቴም ትጫወት ነበር፡፡ ኪ ኤንድ ኤፍ (አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ) በሚባል ቡድን እኔ በቡድን ውስጥ ሳልታቀፍ በፊት እሷም ታግዘኝ ነበር፡፡ የእኛ ቤተሰብ አብዛኛውን ተጫዋች የወጣበት ስለነበር እንዲሁም ኳስ ሜዳ እንደመወለዳችን ኳስ ተጫዋች በማውጣት ስለማይታማ ለዛም ይመስለኛል ለዚህ የደረስኩት፡፡ የብሬ መውጣት ግን ለኔ ይሄን ያህል እንዳይከብደኝ አድርጎኛል ፤ ቶሎ ነው ልወጣ የቻልኩት፡፡ አሁን ግን ከፋዲጋ ይልቅ ታናሼ ፋሲል ጨዋታዬን ስለሚያይ ይነግረኛል፡፡ የእሱም ምክር ከብርሀኑ ቀጥሎ በዚህ በኩል የረዳኝ ይመስለኛል፡፡ ቤተሰቤም የተለያዩ ማቴሪያሎችን በልጅነቴ እየገዙ አበረታተውኛል፡፡” ትላለች፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ