በወቅቱ የነበሩ አሰልጣኞች ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ዕድል የነፈጉትና እግርኳስ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ አቋሙን ጠብቆ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሲፎካከር የነበረውና የተከላካዮች ስጋት፣ ቀንደኛው የጎል አነፍናፊ አህመድ ጁንዲ ማነው ?
አባቱ አቶ ጁንዲ ሁሌም የሚሉት አባባል አላቸው “አንበሳ አንበሳ የተባለው ሥጋ ስለሚበላ ነው። ልጄ ሰላጣ፣ ካሮት ብላ የሚሉትን አልቀበልም። ምንም አያረግም። ጠንካራ እንድትሆን ከፈለክ ሥጋ ብላ” ይሉ ነበር። ከዚህ የተነሳ ሁሌም ለሰውነቱ ጥንካሬ እንዲሰጠው የራሳቸው ከሆነ ልኳንዳ ቤት (ሥጋ ቤት) ጠዋት ጠዋት ጉበት ጥብስ ይበላ ነበር። ለዚህም ይመስላል ተከላካዮች እርሱን እንገፋለን ብለው ራሳቸው ይወድቁ የነበሩት። አህመድ ጁንዲ ተወልዶ ያደገው ድሬደዋ ከተማ ልዩ ስሙ ለገሀሬ አስታጥቄ ሜዳ አካባቢ ነው። ብዙኀኑ የስፖርት ቤተሰብ ከዋናው ስሙ ይልቅ በአባቱ ስም ጁንዲ እያሉ ይጠሩታል። አህመድ አስታጥቄ በተባለ ሜዳ እየተጫወተ አድጓል። በሊጋችን ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች ጎራ የሚመደበው ጁንዲ ከታችኛው ቡድን አንስቶ ከ1984–95 ድረስ ምድር ባቡር እስከ ፈረሰ ጊዜ ድረስ ክለቡን በታማኝነት በማገልገል ስሙን መተከል ችሏል። በክለቡም ቆይታ በ1991 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች፣ በ1988 እና 1995 ደግሞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡
በወቅቱ ከጁንዲ ጋር በጎል አግቢነት ከሚፎካከሩት አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረው ስምኦን ዓባይ ስለ ጁንዲ ሲናገር “ጁዲ ማለት በጣም ጉልበትና ፍጥነት ያለው፣ ጎል የማግባት ጥሩ አቅም የነበረው አጥቂ ነው። በተለይ የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች ምንም ከፍተኛ ጉልበትና አቅም ቢኖራቸውም እሱ ግን ከነሱ በልጦ ለቡድኑ ማድረግ ያለበትን ነገር ሁሉ በተገቢው ሁኔታ የሚያደርግ ምርጥ አጥቂ ነበር።” ይላል።
በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ በወጥ አቋም ጎል በማስቆጠር የዘለቀው ጁንዲ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ሊጠቀሙበት አለመቻላቸው አስገራሚ ሆኖ አልፏል። ለ11 ዓመት ከቆየበት እናት ክለቡ ጋር ከተለያየ በኃላ ወደ ሀዋሳ አምርቶ ሀዋሳ ከተማ የሊጉን ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ በ1996 እንዲያነሳ ከነበረው ከፍተኛ ሚና በተጨማሪ የመጨረሻውን ጎል ኒያላ ላይ ያስቆጠረው እርሱ ነበር። ጎል ካላስቆጠረ እንደሚናደድ የሚገልፀው “ጁንዲ” ከሀዋሳ ከተማ አጭር ቆይታ በኃላ ወደ አዳማ፣ ሐረር ቢራ እና የመን እንዲሁም ጁቡቲ በመሄድ ተጫውቷል። በ2002 ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ ለድሬዳዋ ከነማ ለአንድ ዓመት መጫወት ችሏል።
የተቃራኒ ቡድን አሰልጣኞች እርሱን ለማቆም የሚዘይዱ፣ ብቻውን ቡድን አሸንፎ የሚወጣ፣ በየዓመቱ አስራ አምስት ፣ ሀያ ከዛ በላይ ጎል በማስቆጠር ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ይፎካከር የነበረው ጁንዲ በ2003 ከእግርኳስ ዓለም ሊገለል ችሏል።
ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳያውቅ ለ17 ዓመት በተጫዋችነ የዘለቀው ጁንዲ በአንድ ወቅት በ1991 በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲህ ሆነ። ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቅ ቡድን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆን ስለ ነበር። ወደ አፍሪካ መድረክ የሚጓዘውን ቡድን ለመለየት ኢትዮጵያ ቡና ከባቡር በምሽት ጨዋታ ይጫወታሉ። በበርካታ ተመልካች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታው አንድ ለአንድ ሆነው ቡና በጎል ልዩነት በልጦ ለቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሊሆን ነው በማለት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ደሰታቸውን ችቦ በመለኮስ እየገለፁ ነበር። በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት በአስገራሚ ሁኔታ ጁንዲ አሊ ረዲ መረብ ላይ ያሳርፈዋል። በስታዲየም ውስጥ የነበሩ ደጋፊዎች ደስታቸው በቅፅበት ወደ ሀዘን ተቀየረ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አንጋፋው እውቁ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ እንዲህ ብሎ ገልፆታል። ” አህመድ ጁንዲ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በለኮሱት ችቦ ላይ ዝናብ አዘነበበት” በማለት ተናግሮታል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ ቀርቦለታት የተጫወተ ቢሆንም አዲስ አበባ ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ቢጠቀሙበትም ከሀገር ውጭ በሚደረጉ ጨዋታዎች በአመዛኙ ያስቀሩት እንደነበረ የታሪክ ድርሳኖች ያስረዳሉ። በድሬደዋ ስፖርት ቤተሰብ ተወዳጅ የሆነው ጋዜጠኛ ምትኩ ቶላ ” ጁንዲ ማለት የፈረስ ጉልበት የነበረው ትክክለኛ ዘጠኝ ቁጥር ነው። እግሩ ላይ ኳስ ሲገባ ክህሎት ላይኖረው (ላያምርበት) ይችላል። ሆኖም ከየትኛውም አቅጣጫ ጎል የማስቆጠር አቅም የነበረው ጠንካራ አጥቂ ነበር”። በማለት ይገልፀዋል።
ከ2003 በኃላ የአሰልጣኝነት ኮርስ በመውሰድ በአሁኑ ወቅት ያለውን ልምድ ለማካፈል ለድሬደዋ ከተማ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ያለፉትን አራት አመታት በማሰልጠን እየሰራ ይገኛል። የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን ይህ ድንቅ አጥቂ አህመድ ጁንዲ ስለ እግርኳስ ሕይወቱ እንዲህ ይናገራል።
” በተጫዋችነት ቆይታ እጅግ የተሳኩ ዓመታትን አሳልፌያለው። ከፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እስከ አፍሪካ ክለቦች ውድድር፣ ከኮበብ ጎል አስቆጣሪነት ክብር በየዓመቱ በርከት ያሉ ጎሎችን እስከ ማስቆጠር በእግርኳሱ ኖሬያለው። ሁሉም እየወደደኝ እያከበረኝ እዚህ ደርሻለው። ከዚህ በላይ ምን ስኬት አለ ፈጣሪ ይመስገን።
” አሁን ላይ ሆኜ ወደ ኃላ ሳስብ የሚቆጨኝ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው እኛ በዛን ዘመን ስንጫወት የምናገኘው ጥቅም ክፍያ በጣም አነስተኛ፤ ምንም አልነበረም ማለት ይቻላል። ብዙዎች እግርኳሱን ወደነው ከመጫወት ውጭ በህይወታችን የተቀየርንበት ብዙም ዕድል የለም። እንዲያውም እኔ ኤልያስ ጁሀር ተጫዋች በመሆናችን እና በምንሰራበት መብራት ኃይል እና ባቡር የቋሚ ሠራተኛ የሚከፈለን ደሞዝ ነበር። አሁን ያለውን ክፍያ ስትሰማ ያኔ ይሄ ቢሆን ትላለህ። ሰው ሆነህ መጠቀም የሚገባህን ክፍያ ሳታገኝ ስትቀር ቅሬታ ይሰማሀል። እርግጥ ነው ጊዜው አልፏል። ሆኖም እንደ ለፋሁት ልፋት እና አገልግሎቴ የሚገባውን ጥቅም ባለማግኘቴ እና ራሴ ላይ የተፈጠረውን ጠባሳ ሳስብ በጣም እቆጫለው። ያ ዘመን አሁን ቢሆን ልጆቼ እና ቤተሰቦቼ የተሻለ ነገር ያገኙ ነበር የሚል አመለካከት ውስጥህ ይፈጠራል።
” ሁለተኛ መቆጨትም ባልለው ከእኔ አቅም በላይ የሆነ አሁንም ድረስ እንቅልፍ የሚነሳኝ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የነበረኝ ህልም በወቅቱ በነበሩ አሰልጣኞች እንዳልጫወት የተደረግኩበት ነገር ምክንያቱን አለማወቄ ነው። ለምን ይሄን አደረጉ እላለው፤ ብቻ ጥሩ ነገር አልሰሩም። በእውነት በጣም የሚገርምህ እና ከህይወቴ የማልረሳው አንድ ነገር ልንገርህ የኢትዮዽያ ሻምፒዮና ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኜ በጨረሱኩበት ዓመት (1988) የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ ጋር ለመጫወት ወደ ጣልያን ሲሄድ ተመርጬ ቪዛ ተመቶልኝ ተዘጋጅቼ አውሮፕላን ውስጥ ልገባ ስል በሚገርም ሁኔታ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቀነሰኝ፡፡ እንዴት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ተጨዋች ትቀንሳለህ ሲባል ባዩ ሙሉን ከቤልጅየም መርጫለው አለ፡፡ በጣም ይገርማል። ሆኖም አልፎ አልፎ አጋጣሚውን አግኝቼ ስመረጥ ግብፅ ላይ ተጫውቻለው፣ ከታንዛንያ እና ከሱዳን ጋር ተሰልፌ ተጫውቻለው፡፡
“ከዮርዳኖስ ጋር እኔ እና እርሱ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ እንፎካከር ነበር (1994)፡፡ እኔ በሦስት ጎል እቀድመው ነበር፤ እሱ መብራት ኃይል ሆኖ ከ ጊዮርጊስ ጋር እኔ ደግሞ ከባቡር ጋር ሆኜ መቐለ ላይ ከትራንስ ጋር በእኩል ሰዓት የመጨረሻ ጨዋታ እንጫወት ነበር። ታዲያ አንዲት ጋዜጠኛ ነች ጨዋታው ሳይጠናቀቅ ውጤቱን ሳይሆን እኔ ሦስት ጎል ማስቆጠሬን ስሜን ጠቅሳ አአ ስታድየም ስትናገር ትራንሶች ለቀውለታል ብለው ጊዮርጊሶች ደግሞ አምስት ጎል ለቀውለታል። እንግዲህ በዛ ይመስለኛል መላቀቁ ሊመጣ የቻለው። ይህ ነገር በመፈጠሩ ምንም አልተሰማኝም ሁለታችንም የድሬዳዋ ልጆች ስለሆንን ብዙም አልተሰማኝም። እንዲያውም በኢትዮዽያ እግር ኳስ በዚያ ዘመን ኮከብ ጎል አስቆጣሪ የምንሆነው አሰግድ ተስፋዬ፣ ዮርዳኖስ ዓባይ ፣ ስምኦን ዓባይ እና እኔ ነበርን፡፡
“ይሄን ያህል ዓመት አቋሜን ጠብቄ ለመስራት ያበቃኝ የአባቴ ከልጅነቴ ጉበቱን ሥጋውን እየጠበሰ የሚያበላኝ፣ የሚመክረኝ የአባቴ ትልቁ ድጋፍ ነው። ከዚህ ውጭ ከልጅነቴ ጀምሮ በመስራት ያዳበርኩት ይመሰልኛል አቋሜን ጠብቄ መዝለቅ የቻልኩት። እኔ ጎል የማስቆጥረው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ነው፡፡ በተለይ የእኔ ኳሶች ጠንካራ ጉልበት ያላቸው ስለነበሩ ግብ ጠባቂዎች ለመመለስ ይቸገሩ ነበር። ጎል ሳስቆጥር እንዲሁ በጭፍን አልነበረም የምመታው ፤ የኳሱን ብልት አይቼ ነው። የግብ ጠባቂውን ሁኔታ ፣ ጎሉ የት ጋር ነው ብዬ አይቼ ተረጋግቼ ነው የምመታው። በወቅቱም በግሌ አሰልጣኝ ከሚሰጠን ስልጠና ውጭ ጎል እንዴት ማስቆጠር እንዳለብኝ በአንድ ጎል ላይ ሦስት ግብ ጠባቂዎችን አቁሜ እለማመድ ነበር፡፡ ያ ነው ጥሩ አጥቂ ያደረገኝ።
“የአሰልጣኝነት ህይወቴ ያው ድሬደዋ ታዳጊ ቡድን ማሰልጠን ከጀመርኩ አራት ዓመት ሆኖኛል። ብዙ ስልጠናዎችን ወስጃለው። እውነት ለመናገር ለእኔ የማይመጥን ቦታ ነው እየሰራው የምገኘው። መቀመጥ የሚገባኝ ቦታ ላይ አልተቀመጥኩም። ከእኔ ያነሱ ሰዎች ከነማ ውስጥ እያሰለጠኑ ነው ያሉት። እኔ በአሁን ሰዓት ከማንም አላንስም። እውቀቱም አለኝ ስልጠናዎች ወስጃለው፣ በተጫዋችነት ዘመኔ ያገኛኋቸው ብዙ ልምዶች አሉኝ ግን አልተጠቀሙብኝም። ያው ለሁሉም ነገር ትዕግስት ያስፈልገዋል አልንገበገብም። ወደ ፊት ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል የሚል አመለካከት አለኝ። እርግጠኛ ነኝ ይሆናል ደግሞ።
“በቤተሰብ ህይወቴ ሁለት ሴት ሁለት ወንድ ልጆች አሉኝ። የ13 ዓመት ልጄ አሚልከሪም የእኔን መንገድ በመከተል ጥሩ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን እየሰራ ይገኛል። ”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ