አፍሪካ እና ኮቪድ 19 – ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ሀገር…

ሱፐር ስፖርት ከኮሮና ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ የሊግ ውድድሮችን አስመልክቶ ይዞት በወጣው መረጃ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ሃገር እንደሆነች ተመላክቷል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ላይ የሚደረጉ የእግርኳስ የሊግ ውድድሮች ዘለግ ላለ ጊዜ ተቋርጠው እንደነበር ይታወቃል። ምንም እንኳን ወረርሽኙ ከዓለም ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም የአውሮፓ ሃገራት ሊጎቻቸውን በጥብቅ የጤና ህጎች አጥረው ውድድሮችን ከቆሙበት እያስቀጠሉ ይገኛሉ። የአፍሪካ ሃገራት የእግርኳስ አስተዳደሮችም እግርኳስን ወደ ሜዳ ለመመለስ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህንን አስመልክቶ በደቡብ አፍሪካ መቀመጫውን ያደረገው ሱፐር ስፖርት ከእግርኳስ ጋር የተገናኘውን የአፍሪካ ሃገራትን አቋም እና እቅድ አስታውሷል። በዘገባውም ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የአህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ የሌላት ብቸኛ ሃገር አስብሏታል።

በርካታ ሃገራት በኮቪድ 19 ምክንያት ሊጎቻቸውን ባቋረጡበት ወቅት የእግርኳስ ሊጓን ያላቆመች ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሃገር ብሩንዲ ናት። ሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሃገር ታንዛኒያ በበኩሏ ዜጎቿ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን ሊጓን ከሁለት ቀናት በፊት አስጀምራለች። ኢሲዋቲኒ፣ ሴኔጋል፣ ሲሸልስ እና ቱኒዚያ ደግሞ እንደ ታንዛኒያ ሊጎቻቸውን ለማስጀመር እያጤኑ ይገኛሉ።

ቦትስዋና፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ በበኩላቸው ሊጎቻቸውን ለመጀመር ለየመንግስቶቻቸው ጥያቄ አቅርበው ምላሾችን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ካሜሮን ፒ ደብሊው ቲ ባሜንዳን፣ ኮንጎ ብራዛቪል ኤ ኤስ ኦቶሆን፣ ዲ አር ኮንጎ ቲፒ ማዜምቤን፣ ኬንያ ጎር ማህያን፣ ሩዋንዳ ኤ ፒ አርን፣ ቶጎ ኤ ኤስ ኬ ኦ ካራን የሊጎቹ አሸናፊ እንደሆኑ የወሰኑ ሲሆን አንጎላ እና ጊኒ ግን የሊግ አሸናፊ የለኝም ብለው አውጀዋል። አንጎላ የሊግ አሸናፊ አይኖረኝም ብትልም ግን በቀጣይ ዓመት በካፍ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን በሊጉ ከ1-4 ያጠናቀቁት ክለቦችን መርጣለች።

ከሌሎቹ ሃገራት በተቃራኒ ኢትዮጵያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ላይቤሪያ እና ደቡብ ሱዳን ሊጎቻቸውን ከነአካቴው ሰርዘዋል። ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉት ሦስቱ ሀገራት ግን ለቀጣይ ዓመት የካፍ ውድድሮች ላይ በሙሉ እና በከፊል ተሳትፎ ለማድረግ አስበዋል። በዚህም ቡርኪና ፋሶ በ2019/20 በካፍ ውድድሮች ላይ የተካፈሉት ራሂሞ እና ሳሊታስ በቀጣይም ዓመት እንዲሳተፉ ፈቅዳለች። ላይቤሪያ በበኩሏ የተለየ ውድድር በቅርቡ አድርጋ የአህጉራዊ ተሳታፊ ክለቦቿን እንደምትለይ ጠቁማለች። ደቡብ ሱዳን በበኩሏ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ እንደማይኖራት ነገርግን በኮንፌደሬሽን ካፕ አል ሃቢታ የተባለው ክለቧ በቀጣይ ዓመት ሃገሯን እንዲወክልላት ወሳኔ አስተላልፋለች።

በሱፐር ስፖርት ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያ የሊግ አሸናፊ የሌላት እና በቀጣይ ዓመት የአህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ የማይኖራት ብቸኛዋ ሃገር ናት።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ