መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ባለውለታዎች መካከል አንዱ መሆናቸው ብዙዎችን የሚያስማማ ሀሳብ ነው። የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆነውን ኢትዮጵያ ቡናን ከጥንስሱ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ ፍላጎት ሀዘንና ደስታውን በማሳለፍ ክለቡን እዚህ ደረጃ አድርሰዋል። መቼም በዚህ የአርባ አራት ዓመታት ጉዞ ውስጥ እንደተመለከቷቸው በርካታ ጨዋታዎች ውስጥ ቁጭ ብድግ ያስደረጓቸው በኢትዮጵያ ቡና ተጫውተው ያለፉ ድንቅ ተጫዋቾችን አይተው ማለፋቸው ይገመታል። ይህን መነሻ አድርገን ወደ ስልካቸው ደውለን መቶ አለቃን አንድ ጥያቄ ጠየቅናቸው? “እስከ ዛሬ ከተመለከቷቸው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎች ውስጥ የእርሶን ምርጥ አስራ አንድ ከእነ አሰልጣኙ ምረጡልን?” አልናቸው። የሰጡን ምላሽ ግን ያልገመትነው ነበር። ይህን አስገራሚ ምላሽ እና እግረ መንገድም ሌሎች ያነሱዋቸውን ሀሳቦች ጨምረን ወደ እናንተ ልናጋራቹሁ ወደድን።
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከምስረታው እስከ አሁን ድረስ አብረው አሉ። እስከ ዛሬ ከተመለከቷቸው ተጫዋቾች ውስጥ የእርስዎን ምርጥ አስራ አንድ ምረጡልን ?
(እየሳቁ ንግግራቸውን በመጀመር) ይሄውልህ ስማኝ… እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ቡና መለያን ለብሰው የተጫወቱት ሁሉ፤ ከመጀመርያው እስከ አሁን ድረስ ያሉት በሙሉ ልጆቼ ናቸው። አንዱን ከአንዱ አልመርጥም። ሁሉም ለእኔ ጥሩ፣ እኩል ናቸው። ሁሉም ምርጥ ተጫዋቾቼ ናቸው።
ትክክል ነው። ግን መቼም በተለያየ ዘመን ኢትዮጵያ ቡና እጅግ በርካታ ኮከብ ተጫዋቾችን አፍቷል። ከሙልጌታ ወልደየስ እስከ ሚሊዮን በጋሻው፣ ከአሰግድ ተስፋዬ እስከ ካሳዬ አራጌ፣ ከአሸናፊ ግርማ አሁን እስከሚገኙት እነ አቡበከር ናስር ድረስ ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ጭምር እያሉ እንዴት ምርጥ አስራ አንድ መምረጥ አቃተዎት ?
(በቁጣ..) እንዴ ነገርኩህ እኮ ለእኔ የኢትዮጵያ ቡናን ማልያ የለበሱት ሁሉ፤ አስር ዓመትም ሆነ አንድ ቀን ማልያውን ለብሶ ያገለገለ ይቅርና በዋናው ቡድን እስከ ታችኛው ታዳጊ ቡድን ድረስ የተጫወቱት በሙሉ እንዲሁም አስራ ሁለት ቁጥር ማልያ ለብሰው የሚደግፉት በርካት ደጋፊዎች ጭምር የማላበላልጣቸው ኢትዮጵያ ቡና የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው። ምን ነካህ አንተ (እየሳቁ) የእኔ ልጆች አስራ አንድ ብቻ አይደሉም። በአርባ ዓመት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች እያሉኝ በአስራ አንድ ብቻ ልትገድበኝ ነው እንዴ?
ይሄን ጥያቄ ወደ እርሶዎ ሳደርስ ቀላል አድርጌ ነበር። ሆኖም የእርስዎ ምላሽ ያልገመትኩት ሆነ…
አዎ ይለያል ? ምክንያቱም የእኔ ሥራ አይደለም። እኔ ተጫዋቾችን ልንመለምል ነው ብለው ሲነግሩኝ “ለቡና የሚመጥን፣ ለክለቡ ፍቅር ያለው፣ ደሙን ሰጥቶ የሚጫወት መልምሉ” ነው የምለው። በዚህ ሂደት ሥራ አስኪያጁ አሰልጣኞቹ፣ ቴክኒክ ክፍሎች አሉ እነዚህ ኃላፊዎች እታች ወርደው መልምለው ለክለቡ የሚመጥን ተጫዋች ያመጣሉ በቃ። ስለዚህ ለቡና ሊጫወት የመጣው ክለቡን ወዶ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም አከብራለው።
ምርጥ አስራ አንዱ ይቅር እና በኢትዮጵያ ቡና ካይዋቸው ተጫዋቾች የእርስዎ ልዩ ተጫዋች ማን ነው ?
እርሱንም አልነግርህም። ወደ ፊት የኢትዮጵያ ቡና አገልግሎቴን በክብር ሳጠናቅቅ ወደ ፊት እነግርሀለው። እኔ እንዳውም ወደ ተጫዋቾቹ ሳንገባ ለታሪክ ያህል ይሄን ልንገርህ። ኢትዮጵያ ቡና እንደተመሠረተ አካባቢ ወደ ላይኛው ዲቪዝዮን ወጣን፤ ሆኖም መቆየት ሳንችል ወርደን ነበር። በነገራችን ላይ እኛ ብቻም ሳንሆን ቅዱስ ጊዮርጊስም ወርዶ ነበር። መውረዳችን ግን ጠቅሞናል። ምክንያቱም እነ መንግሥቱ ቦጋለ የሚባሉ የቀድሞ ተጫዋቾችን ቀጠርን። መንግሥቱ ቦጋለ ማለት ከሥዩም አባተ ጋር በመሆን ለቡና የሚሆኑ ተጫዋቾችን ያደራጀ ሰው ነው። አሁን በኩራት “ቡና” የምንለውን፣ በበርካታ ደጋፊ ታጅቦ የሚወደድ ክለብ እንዲሆን መሰረት የጣለው መንግስቱ ቦጋለ ነው። እነዚህ እነዚህ ሰዎች መታወስ አለባቸው። ብዙም ሥራቸው ሲወራ አልሰማም።
ኢትዮጵያ ቡና ረጅም ዓመት ቆይታዎ የማይረሱት ገጠመኝ የቱ ነው ?
በ1970ዎቹ መጀመርያ 51 ቡድን ተቋቋመ፤ እኛም አስር ቡድን ውስጥ ገብተን አለፍን። ሆኖም ዓመቱን ሙሉ ተወዳደርን ወረድን። ይህ ለእኔ በህይወቴ የማረሳው ትልቅ ሀዘን ነበር። መቼም አልረሳውም። የት ይደርሳል የተባለ ቡድን በመውረዱ ነበር በጣም አዝኜ የነበረው። ግን መውረዳችን ጠቀመን፤ ራሳችንን እንድንፈትሽ ረዳን። በቀጣይ በደንብ ተደራጅተን ብዙ ነገሮችን ወጪ በማድረግ እኔም ሥራዬን ትቼ እያንዳንዱን ነገር መከታተል፣ ውድድሮችን በየሜዳው ሄጄ መከታተል፣ ለኔ በጣም ከባድ ከፍተኛ ፈተና ነበር። እንዳንወጣ የማይፈልጉ ቡድኖች፣ የፌዴሬሽኑ አካሎች ሁሉ ነበሩ። ስንወርድ ሁሉ በዚያው ይቀራሉ አይመለሱም ብለው የገመቱ ሁሉ ነበሩ። ዳግም አድገን ስንመለስ የነበረኝ ደስታ እንዲህ ነው ብዬ የማልገልፅልህ ታላቅ ደስታ ነበር። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቡና በመኖር እና በመሞት መካከል ውስጥ ሆኖ ያለፈበት አጋጣሚ ነው። ከዛም በኃላ ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፍን አውቃለው። ግን ክለቡ ህዝባዊ መሰረት ያለው በሁሉም የሚወደድ እና የሚታወቅ በመሆኑ በደሉ ቢኖርም ይፈርሳል ይበተናል ብለህ አትሰጋም። ስለዚህ ለኔ የማረሳው አጋጣሚ ወርደን መመለሳችን ነው።
አሁን ላይ ሆነው ያኔ ሲመሰረት ከበርካታ ፈተና እና ውጣ ውረድ በኃላ ኢትዮጵያ ቡና የሚወደድ፣ ይህ ሁሉ ደጋፊ ያለው ቡድን ይሆናል ብለው አስበው ያውቃሉ?
እ…እ…እ አላስብም ነበር። እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብሎ መገመት እጅግ በጣም በጣም አስቸጋሪ ነው። የወዛደር (የሠራተኛ) ቡድን ስለሆነ እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችል ተስፋ ነበረኝ። ይሁን እንጂ በዚህ ደረጃ አሁን ያለበት ሁኔታ ይደርሳል ብዬ አስቤ አላውቅም።
ወደፊት ምን አይነት ኢትዮጵያ ቡናን ያልማሉ ?
ቡና አሁን ለብዙ ነገሮች መሠረት ጥሏል። የራሱ ፅህፈት ቤት እና የተደራጀ ቢሮ አለው። የራሱ የሆነ የተጫዋቾች ማረፊያ ካምፕ አለው። የራሱ ሜዳ እንዲኖረው ተደራጅቶለታል፣ አሁን በሜዳው ላይ መጨመር ነው። በአንድ ጊዜ ከባድ ነገር አትሰራም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሀገር ደረጃ እንኳን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሃያ ሺህ ተመልካች በሚይዝ ሜዳ አይደል የተጫወተው። እኛም ሜዳችንን አንድ አንድ ድንጋይ እየጣልን እንገነባዋለን። ከአሁን በኃላ ያለው ትውልድ በተጣለው መሠረት ላይ እየገነባው ይሄዳል። በአንዴ ስልሳ ሺህ ፣ አርባ ሺህ ተመልካች የሚይዝ ስታዲየም እንገንባ ብለን አንነሳም። ቀስ በቀስ የሚጠናቀቅ እናደርገዋለን። ለዚህም የድሬደዋ ስታዲየም የሚደረገው የማስፋፊያ ስራ ስታይ፣ የሀዋሳን ስታዲየም ስትመለከት በሂደት እኛም የራሳችን ሜዳ እንዲኖረን ማስቻል እንችላለን።
የቡድኑን አጨዋወት የመጠበቅ፣ በሊጉ ዋንጫ የሚያነሳ ቡድን መስራት ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው ?
ይህንንም እናስባለን። የራስህ ሜዳ ሲኖርህ አብሮ የሚመጡ ግዴታዎች አሉ። ሁኔታዎች ራሱ ያስገድዳሉ። የራስህ ሜዳ ሲኖርህ የወጣት ማዕከል ትገነባለህ። የምትፈልጋቸውን ታዳጊ ተጫዋቾች ትመርጣለህ። በተለይ ከወጣቱ ጋር ያለን ቁርኝት ይበልጥ እየተጠናከረ ይቀጥላል። ከአሁን በኃላ ለቡና መንገዶች እኛ እንዳሳለፍነው ከባድ አይሆኑም። ለምን ቢባል ክለቡ ታውቋል፣ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ወጣቱ ያፈቅረዋል፣ ከበሬታ ሰጥቶታል። ቅድም እንዳልኩሁ አንዳንድ እሴቶች ተገንብተውለታል። በእነዚህ እሴቶች አንዳድ ነገሮች እየጨመርክ ወጣቱን እያደራጀህ መሄድ እና ኢትዮጵያ ቡና ታላቅ ክለብ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ብቻ ነው። ሁሉም እንደኛ ቢሆን ደስ ይለናል። እንደምታቀው በጀት በራሳችን ነው የምንቀሳቀሰው። ይህ ወረርሺኝ ሲመጣ እንደማንኛውም የመንግስት፣ የግል ተቋማት እኛም ላይ ተፅእኖ አድርጓል እንጂ በእግራችን ቆመን መራመድ የምንችል ክለብ ሆነን ጥሩ መስመር እየያዘን መጥተን ነበር። በሀገር የመጣ ችግር ነው። ችግሩ ነገ ይቀረፋል ቀስ ብለን ወደ ነበርንበት ቦታ እንመለሳለን ብለን ተስፋ አደርጋለው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ