ለ13 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ግልጋሎት የሰጠችው እና በ4 የተለያዩ ክለቦች 26 ዋንጫዎችን ያነሳችው ብዙሃን እንዳለ በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን ትዳሰሳለች።
ጊንጪ በምትባል የኦሮሚያ ከተማ ተወልዳ ነገር ግን ገና አንድ ዓመት ሳይሞላት ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ብዙሃን እንደ አብዛኞቹ የሴት ተጨዋቾች ኳስን ከልጅነቷ ጀምሮ እንደልቧ መጫወት አልቻለችም። በተለይ ከአንድ አመቷ ጀምሮ ያደገችበት ቶታል 3 ቁጥር መዞሪያ አካባቢ የነበሩ ወንድ ኳስ ተጫዋቾች በጨዋታ እሷን ለማሳተፍ ያመነቱ እንደነበረ ታስታውሳለች። በቤት ውስጥም ከወንዶች ጋር ኳስ እንዳትጫወት ስትከለከል የነበረችው ብዙሃን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩባትን ጫና ተቋቁማ ስሜቷን እንደምንም ተደብቃ ታስታግዝ ነበር። በተለይ ወላጅ አባቷ የሴትነት ጥቃት እንዳይደርስባት ስለሚሰጉ እና በቀለም ትምህርቷ እንድትገፋ ስለሚሹ ኳስን አደለም እንድትጫወት እንድትነካ እንኳን አይወዱም ነበር። ጊዜ እየቆጠረ ሲመጣ ግን ታላቅ ወንድሟ ምክሮችን እየለገሳት ወደ ሜዳ እንድትሄድ ይፈቅድላት ጀመር። ከምንም በላይ ደግሞ ወላጅ አባቷ ካረፉ በኋላ ቤተሰቧ ጠበቅ ያደረጉትን ክልከላ በማላላታቸው ኳስን እንደልቧ ማግኘት ጀመረች።
“አባቴ ከቤት እንድወጣ አይፈልግም ነበር። በተለይ በሴትነቴ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ስለሚሰጋ ፈፅሞ ከቤት አያሶጣኝም ነበር። ነገርግን እሱ ካረፈ በኋላ ቤት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቼ የነበረውን የጠበቀ ቁጥጥር ማላላት ጀመሩ። በተለይ ታላቅ ወንድሜ ስሜቴን ይረዳ ስለነበረ እየመከረኝ እንድጫወት ያደርገኝ ነበር። እኔም በማገኛቸው አጋጣሚዎች ኳስን መጫወት ጀመርኩ። ነብሱን ይማረው እና ፋሲል የሚባል አሰልጣኝ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በትምህርት ቤት እያለሁ ያሰለጠነኝ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በኤስ ኦ ኤስ (አሁን ከፍተኛ 23 ተብሏል) እየተማርኩ እና በፋሲል እየሰለጠንኩ ባለሁነት ሰዓት ደግሞ የትምህርት ቤቶች ውድድር ደረሰ። በዚህ ውድድር ላይ እየተጫወትኩ ደግሞ አቶ ኢተፋ የሚባሉ አሰልጣኝ አይተውኝ ወደ ራሳቸው ቡድን ቀላቀሉኝ። የሳቸው ቡድን ውስጥ እየሰለጠንኩ 2 ወር ሳይሞላኝ ደግሞ ለአዲስ አበባ ምርጥ ተመረጥኩ። ከዚህ በኋላ የእግርኳስ መንገዴን በደንብ አገኘሁት።”
በፊት በፊት ከእኔ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴት እግርኳስ ተጫዋቾች ያሉ አይመስለኝም የምትለው ብዙሃን መለስ ብላ ሴት ተጨዋቾችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችበትን ቅፅበት ታስታውሳለች።
“በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከእኔ ውጪ ሴቶች ኳስ የሚጫወቱ አይመስለኝም ነበር። እኔ ብቻ ነበር ሃገሪቱ ውስጥ ያለሁ ሴት ተጫዋች የሚመስለኝ። እርግጥ እነ ሰሚራ እና ራውዳ ከእኔ በፊት ይጫወቱ ነበር። በጊዜው እነሱ ታዋቂ የነበሩ ቢሆኑም እኔ ግን አላውቃቸውም ነበር። እንደውም ‘ሌሎች ሴት ተጨዋቾች አሉ’ ተብዬ እነሱን ላይ ስሄድ በጣም ነው የተገረምኩት። ከመገረሜ የተነሳ ፈዝዤ ነበር ሳያቸው የነበረው።”
በትምህርት ቤት ውድድሮች የእግርኳስ ህይወቷን “ሀ” ብላ የጀመረችው ተጫዋቿ የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ውስጥ ከተመረጠች በኋላ በፍጥነት የሃገሪቱን ክለቦች ቀልብ መግዛት ጀመረች።
“እንደገለፅኩት አቶ ኢተፋ ቡድን ውስጥ እየሰለጠንኩ 2 ወር ሳይሞላኝ ነው የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ውስጥ የተካተትኩት። እርግጥ የአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለብዙ ጊዜያት ተጫውቻለሁ። የተለያዩ አሰልጣኞችም እዚህ ቡድን ውስጥ አሰልጥነውኛል። እኔም ደግሞ ብቃቴን እያጎለበትኩ የእግርኳስ ህይወቴን ቀጠልኩ። በክለብ ደረጃ የመጀመሪያ ክለቤ አቶ ኢተፋ ጋር የነበረው ነው። ከዛን በመቀጠል ለአንድ ጨዋታም ቢሆን አዲስ ኮከብ የተባለ ክለብ ተጫውቻለሁ። ከዛም ለኢትዮጵያ ቡና፣ ሴንትራል የጤና ኮሌጅ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግያለሁ። ዘንድሮ ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ እየተጫወትኩ ነው። ከምንም በላይ ግን እዚህ እንድደርስ ያደረጉኝ አቶ ኢተፋ ናቸው። እሳቸው ናቸው የእግርኳስ ህይወቴን ያሳመሩልኝ። እርግጥ ግን ይህንን ስል ሌሎች አሰልጣኞች በእግርኳስ ህይወቴ ምንም አላደረጉም እያልኩ አደለም። በርካታ አሰልጣኞች ከጀርባዬ ሆነው ሲደግፉኝ እና ሲያጎለብቱኝ ነበር። ግን አሰልጣኞቹ ጋር ከመድረሴ በፊት ወንድሜ ትልቅ መሰዋትነት ከፍሎልኛል። በተለይ ታዳጊ እያለው ጥሩ መንገድ እንድይዝ በጣም ረድቶኛል።”
ለ13 ዓመታት በወጥነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረችው ብዙሃን በ1994 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ጫፍ ደርሳ ነበር። ነገርግን በአካላዊ አቋሟ ምክንያት ከመጨረሻዎቹ 18 ተጨዋቾች ተቀንሳ ከቡድኑ ተለያይታለች። ከዛ ግን በተከታታይ በአዲስ አበባ ምርጥ ቡድን ውስጥ ባሳየችው ድንቅ አቋም ለብሔራዊ ቡድን ተመርጣለች ።
“እውነት ለመናገር የክለብም ሆነ የብሄራዊ ቡድን እድሉን ያገኘሁት ሳልጠብቅ እና ሳላስበው ነው። በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ሁሉ ነገር የተሳካልኝ። ለአዲስ አበባ ምርጥ ስመረጥ እራሱ ስለ ተጫዋች ቦታ ምንም አላቅም ነበር። አጥቂ፣ አማካይ እና ተከላካይ ስለሚባሉት ነገሮች በደንብ ሳላውቅ ነው ለአዲስ አበባ ምርጥ የተመረጥኩት። የሆነው ሆኖ እድሎች በቶሎ ጥሩ መስመር አስያዙኝ። ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመመረጥ እድሉን ያገኘሁት ለአዲስ አበባ ምርጥ ስጫወት ነው። ወደ ብሄራዊ ቡድንም እንደመጣሁ በጣም የማከብራት እና የምወዳትን የእየሩሳሌም ነጋሽ ቦታ ተክተሽ ትጫወቻለሽ ተባልኩ። እኔ ግን ስለቦታው ምንም አላቅም ነበር። የእርሷንም ቦታ የያዝኩት ተጨዋቿ ስትጎዳ ነው። ብቻ ይህንን እድል ካገኘሁበት ጊዜ አንስቶ ለብሄራዊ ቡድን ግልጋሎት መስጠት ጀመርኩ። ከ1995 ጀምሮ እስከ 2007 ደግሞ በቋሚነት ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫውቿለሁ።”
ፀባየ ሰናይጠእንደሆነች የሚነገርላት ብዙሃን ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግልላሎቷ በተጨማሪ በ4 የተለያዩ ክለቦች ተጫውታለች። በተጫዋችነት ህይወቷም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዋንጫን 6 ጊዜ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 8፣ ከሴንትራል የጤና ኮሌጅ ጋር 2 እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 10 በድምሩ 26 ዋንጫዎችን አንስታለች። ለዚህ ክብር እንድትበቃ ደግሞ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጥሩ እርዳታ እንዳደረገላት ትመሰክራለች።
“አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ከእርሱ ጋር በጣም ብዙ ዓመታት ሰርተናል። መጥፎም ሆነ ጥሩ ጊዜያትን አብረን አሳልፈናል። እንደውም ስለራሴ ከእኔ ይልቅ እሱ በደንብ የሚያውቅ ይመስለኛል። በአጠቃላይ እኔም እንደተጫዋች እንዳድግ አድርጎኛል። ስለዚህ እርሱን በእዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።”
ተጫዋቿ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ወደ ምስራቂቱ የሃገሪቱ ክፍል ተጉዛ ለድሬዳዋ ከተማ እየተጫወተች ትገኛለች።
“አሁን ያለሁበት ክለብ በጣም ተመችቶኛል። የድሬዳዋ የስፖርት ማህበርንም አመሰግናለሁ። ለእኔ የተለየ ጥሩ ቦታ ነው ያላቸው። ይህ ማለት ግን ከሌሎች ተጨዋቾች ለይተው ያዩኛል ማለት አደለም። ግን በጣም አክባሪዎቼ ናቸው። ከአሰልጣኞቹ ጀምሮ ያሉት አካላት ሁሉም ቀና ናቸው። ለዚህም ደግሞ አመሰግናቸዋለሁ። አምላክ ይህንን የኮሮና ወረርሽኝ ያጥፋው እና እስካገኛቸው ናፍቄያቸዋለሁ።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ