ስለ አሸናፊ ሲሳይ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

መጀመርያውንም መጨረሻውንም አንድ ክለብ ብቻ በማድረግ ወጥ በሆነ አቋም ለአስራ አምስት ዓመታት አገልግሏል። በቁመት አጭር ከሚባሉ አጥቂዎች መካከል ቢመደብም በቅልጥፍናው እና በፍጥነቱ ጎል በማስቆጠር አቅሙ ይታወቃል። ይህ የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ አሸናፊ ሲሳይ (አሹ) ማነው ?

በዛን ዘመን የተጫዋች ምልመላ ባልነበረበት ጊዜ የክለቡ የልብ ደጋፊና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገለገሉት አደበተ ርዕቱሁ አንጋፋው የቀለም መምህር ጋሽ ታደሰ መሸሻ በሚያስተምሩበት ተፈሪ መኮንን የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ አንድ ብላቴና ይመጣል። ሁሌም በእረፍት ሰዓት ጨዋታ የሚያዘወትረው ይህ ታዳጊ በአንድ ቀን ጋሽ ታዴ አይን ውስጥ ይገባል። የኳስ አያያዙ፣ ቅልጥፍናው፣ ፍጥነቱ አስገርሟቸው ለባልንጀራቸው ለአባቱ እንዲህ ይላሉ “ይሄ ልጅ ጥሩ የእግርኳስ ችሎታ አለው። ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲጫወት ይዤው ልሂድ ? ማን ያውቃል በዚህ ታላቅ ክለብ ውስጥ ኮከብ ተጫዋች ይሆን ይሆናል።” አቶ ሲሳይም ይፈቅዱና ጋሽ ታዴ ኮንትራት ታክሲ ይዘው ሳር ቤት (ብስራተ ገብርኤል) ሜዳ ይወስዱታል። እንዳጋጣሚ ሆኖ ሜዳው ይያዝባቸው እና ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ በሚገኝ ሜዳ በድጋሚ ይዘውት ይሄዳሉ። የወቅቱ የታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝ እንዳልክ ነጋ (በህይወት የለም)። ያን ትንሽ ልጅ አይቶ ለጋሽ ታዴ እንዲህ አላቸው። ” ጋሽ ታዴ ይሄ ልጅ ህፃን ነው። ለ” ሲ” ቡድን ለመጫወት አልደረሰም። ለማንኛውም ይግባና ልየው።” ይላቸዋል። በል ልብስህን አውልቅ ማልያ ልበስ ብለውት ልብሱን ሲያወልቅ ጋሽ ታዴ ደነገጡ። ምክንያቱም ልብስ ለብሶ ሲያዩት ቀጭን፣ ሰውነት የሌለው ይመስላል። ሆኖም ግን በጣም ጠቅጠቅ ያለ ሞላ ያለ ሰውነት ያለው ጠንካራ ሆኖ ያገኙታል። በዚህ ተገርመው የሙከራው ጊዜው ደርሶ ወደ ሜዳ ይገባና መጫወት ይጀምራል። ለጊዜው ሜዳ ገብቶ ኳሱን ለማግኘት ቢቸገርም አጋጣሚ ሆኖ መጀመርያ ያገኘውን ኳስ በደረቱ አብርዶ በሁለት ጉልበቱ አውርዶ አስገራሚ ሁኔታ ጎል ያስቆጥራል። ይህን ያየው አሰልጣኝ በጣም ተገርሞ ለተጨማሪ ቀን ቢቀጥረውም ሙከራውን በስኬት አጠናቆ መጀመርያውም መጨረሻውም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊሆን በዛው ይቀራል። 

ይህ ታናሽ ብላቴና የዛሬ ባለታሪካችን የዘጠናዎቹ ኮለብ አሸናፊ ሲሳይ ይባላል። ተወልዶ ያደገው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አካባቢ ነው። ከላይ በገለፅነው አጋጣሚ በ1981 የቅዱስ ጊዮርጊስ “ሲ” ቡድንን በመቀላቀል የእግርኳስ ህይወቱን ይጀምራል። ከሦስት ዓመት የታዳጊ ቡድን ቆይታ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ አብዛኛው ተጫዋቾቹን ለብሔራዊ ቡድን በማስመረጡ ምክንያት የተገኘውን አጋጣሚ በመጠቀም በ1984 ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል። በዋናው ቡድን ኢትዮጵያ መድን ላይ ጎል በማስቆጠር የጎል አካውንቱን የከፈተው ይህ የጎል አዳኝ ከዚህ በኃላ የሚያቆመው ጠፍቶ በደጋፊዎቹ እየተወደደ ህልሙን መኖር ይጀምራል።

በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው ድንቁ አማካይ አንዋር ያሲን (ትልቁ) ስለ አሹ ይሄን ምስክርነት ይሰጣል። “አሸናፊ ለተከላካዮች የማይመች ነው። አሸናፊ ሜዳ ውስጥ አለ ከተባለ ተከላካዮች ሠላማቸውን ያጣሉ ፣ ይረበሻሉ እና መረጋጋት ያቅታቸዋል። የጎል አጋጣሚ ካገኘ የማይምር ነው። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለረጅም ዓመታት በትልቅ ኃላፊነት አቋሙን ጠብቆ የተጫወተ በጣም የማከብረው ትልቅ ተጫዋች ነው”። ይለዋል።

በታዳጊ ቡድን አራት በዋናው ቡድን አስራ አንድ በጥቅሉ ለአስራ አምስት ዓመት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወት ብዙ ገድሎችን በአስገራሚ ብቃቱ መፈፀም ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ ሦስት ዓመታት የሀገሪቱን ከፍተኛ ውድድሮች ከ1986–88 ባለው ጊዜ ውስጥ ባሳካቸው የአዲስ አበባ ቻምፒዮን ፣ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን፣ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ድል ውስጥ ትልቅ ሚና ነበረው። በግሉ 1986 ኮከብ ተጫዋች በ1987 ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ክብርን አግኝቷል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ አቀራረብ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን እና በ1991 የፌዴሬሽን የመረጃ አያያዝ ስህተት ቢኖርበትም በመጨረሻም ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የረጅም ዓመት ደጋፊ የሆነው ጌዲዮን ስዮም ሲናገር ” አሹ ልባም የሆነ ምርጥ አጥቂ ነው። የተነጠቀውን ኳስ ሳያስጥል የማይቆም ጎል አስቆጣሪ ነው። አመለ ሸጋ በደጋፊ ሁሉ የሚወደድ ነው። አሹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን የልብ ደጋፊ የሆነ አጥቂ ነው”። ይለዋል። ብዙ የሚነገሩለት በርካታ ተስዕጦ ያለው ይህ ፈጣን አጥቂ በብሔራዊ ቡድን በታዳጊ፣ በወጣት፣ በኦሊምፒክ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በመጫወት ሀገሩንም መጥቀም ችሏል።

እስቲ በድጋሚ በወደ ኃላ ልመልሳችሁና ጋሽ ታደሰ መሸሻ እጁን ይዘው የሄዱት ያብላቴና በሚወዱት ክለባቸው የሚወደድ፣ የሚደነቅ እንዲሁም ጎል አስቆጥሮ እራሳቸውን ሳይቀር የሚያስጨፍር ሲሆን ምን እንደሚሰማቸው ወደ ኃላ አስታውሰው እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው። (በእንባ እና ሲቃ በተሞላው አንደበት) እንዲህ ብለው ነገሩኝ ” በዛን ጊዜ እኔ አሸናፊ ሲሳይ አይደለም የሚታየኝ። ከልቤ እውነቱን ልንገርህ? ልቤ ሞልቶ በደስታ ተውጬ የምወደው ክለቤ እንደዚህ ዓይነት ማንም ተከላካይ የማያቆመው በፍጥነቱ ጥሶ ገብቶ ጎል ሲያስቆጥር ፣ ኳስ ሲነጠቅ ወደ ኃላ ተመልሶ ሄዶ አስጥሎ ለጓደኞቹ አቀብሎ እራሱ የሚያገባቸው ጎሎች ሳይ እውነት ከምንም በላይ የሚያረካኝ እርሱ ነበር። ከአባቱ ጋር ሁልጊዜ ሜዳ አብረን ነው የምንገባው አሸናፊ ጎል ባገባ ቁጥር ተያይዘን መተቃቃፍ መሳሳም ነበር። ብቻ አሸናፊ ታሪኩ ትንሽ አይደለም ረዥም ነው። እኔ በዚህ ዘመን አሸናፊን የሚመስል ተጫዋች የለም”። በማለት ተናግረዋል።

ሌላኛው አብሮት የተጫወተው ድንቁ አማካይ ሙሉዓለም ረጋሳ ስለ አሸነፊ ምስክርነት ሲናገር “ፈጣን፣ ጉልበተኛ እና ታታሪ አንድ አጥቂ ሊያሟላ የሚገባቸውን ነገሮች በሙሉ ያሟላ በድፍረት እና በፍጥነት ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችልበት አቅሙ ያለው አጥቂ ነው”። ይለዋል። ይህ ስኬታማ ተጫዋች በ1995 እግርኳስን ካቆመ በኃላ ኑሮውን አሜሪካ ካደረገ አስራ አምስት ዓመት ሆኖታል ሶከር ኢትዮጵያ ካለበት ሀገር አሜሪካ አግኝተዋው አናግራዋለች።

“በቅድሚያ እዚህ ፕሮግራም ላይ እንግዳ  አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ። እንግዲህ እግርኳስን የጀመርኩትም የጨረስኩትም በጊዮርጊስ ነው። C ቡድን ከገባሁበት ከ1981 ጀምሮ እግርኳስን እስካቆምኩበት 1995 ድረስ ወደ አስራ አምስት ዓመት ቆይታዬም ሁሉ እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ጥሩ ፍቅር፣ መከባበር እና መተሳሰብ ነበረን። በአጠቃላይ ልዩ ዘመን ነበር። ያ ጊዜ መቼም መቼም ከአዕምሮዬ አይጠፋም። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሁሉንም ስኬቶች እንደ ቡድን በግሌም ጭምር አግኝቻለው። ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ተሸልሜ አለው። በብሄራዊ ቡድን በነበርኩበት ጊዜ በሁሉም የዕድሜ ዕርከን ተመርጬ ሀገሪን በሚገባ አገልግያለው። በዚህም በጣም ጥሩ እና ውጤታማ የነበርኩበትን ጊዜ አሳልፊያለው። በዚህም እንደማንኛውም ተጫዋች ደስተኛ ነበርኩ።

“ፈጣሪ ይመስገን ምንም ነገር አይቆጨኝም። ሁሉንም ነገር ከሞላ ጎደል አሳክቻለሁ፣ አግኝቻለሁ፣ አድርጌያለሁ ብዬ ነዉ የማስበው። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኔን ያሳለፍኩት። ምንም የምቆጭበት አላሳካሁትም የምለው ነገር የለኝም። ፍጥነቱን ከየት አገኘህው ላልከኝ ያው ቁመቴ አጭር ነው። አጭር ስለሆንኩም ፈጣን እና ቀልጣፋ እንድሆን የረዳኝ መሰለኝ። በተጨማሪ ግን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የፍጥነት እና የቅልጥፍና ልምምዶችን በተደጋጋሚ ያሰራኝ ስለነበረ ከዛም ያመጣሁት ይሆናል። ሁለቱ ተደማምረው ነው ፍጥነት እና ቅልጥፍናዬን ያሳደጉልኝ።

” አቶ ታደሰ መሸሻ የአባቴ የቅርብ ጓደኛ ናቸው።  እሳቸው ናቸው ወደ ጊዮርጊስ C ቡድን ይዘውኝ የመጡት። C ቡድንም ሞክሬ ከዛም አለፍኩ። አቶ ታደሰ ማለት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ለዚህ ታላቅ ክለብ ያበረከቱ ድንቅ ሰው ናቸው። በተጨማሪም  C እና B ቡድኖችን ከጃን ሜዳ አንስተው እስከ ስታዲየም ድረስ እየሄዱ ያበረታታሉ። ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችንም ወደ ጊዮርጊስ በማምጣት ቡድኑ እንዲጠናከር ያደርጋሉ። እጅግ በጣም ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰው ናቸው። ከዚህም መሀል ብርሃኑ ፈየራን፣ እኔን እና ሌሎችንም ተጫዋቾች አምጥተው ጊዮርጊስን ለማጠናከር ላደረጉት ትልቅ ጥረት ሊደነቅ እና ሊወደስ የሚገባው ነው። እኚህን ታላቅ ሰው በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ ።

“ከሀገር ከወጣሁ አሁን 15 ዓመት ሆኖኛል። የአንድ ሴት ልጅ አባት ነኝ። ወደፊት የሀገሬን ስፖርት ለማገዝ ወይም ደግሞ የአሰልጣኝነት ትምህርት ወስጄ አሰልጣኝ ለመሆን አስባለሁ። እስካሁን ግን ምንም ሀሳብ የለኝም። ወደፊት ከራሴ ጋር ተማክሬ አንድ ነገር እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ ።

“በመጨረሻም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፆኦ በማድረግ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን ሰውተው ይህን ታላቅ ክለብ ጥሩ ደረጃ እንዲደርስ ካደረጉ ሰዎች መካከል አቶ ዳዊት አሰፋ ፣ ጀማል ፣ ሳህሌ ወልደሰንበት ፣ ግርማ ነዳ እና ሌሎች ጥሩ እና ድንቅ ሰዎች የነበሩበት እና ያሉበት ክለብ ነው። እነዚህን ከልቤ ሳላመሰግናቸው አላልፍም። እናተም ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለው።”

* በአሸናፊ ሲሳይ ላይ በፌዴሬሽኑ የመረጃ አሰባሰብ ስህተት ምክንያት በ1991 ስለተፈጠረው ጉዳይ እና ወደ ክስ አምርቶ በጓሮ በር መቋጫ ስላገኘው ነገር የፊታችን ሐሙስ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ