ለተስፋዬ ኡርጌቾ ወላጅ እናት የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ

በቅርቡ በህይወት ያጣነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ለነበረው ተስፋዬ ኡርጌቾ ወላጅ እናት የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

አቅመ ደጋማ የነበሩት እናቱ ወ/ሮ መብራት ጋሻው ያሉበት ሁኔታ ያሳሰባቸው በአሜሪካ እና በአውሮፓ የሚኖሩ አብረውት የተጫወቱት የቀድሞ ጓደኞቹ በአሜሪካ ኑሯቸውን ያደረጉት ብርሃኑ ወልደሥላሴ (የቀድሞው የሜታ ተጫዋች/ በዋናነት ያስተባበረ)፣ ብርሀኑ (ፒያሳ)፣ አብዲ ሰዒድ (ከላስቬጋስ) እና ቢንያም ኃይለሥላሴ (ሳንፍራንሲስኮ) ባደረጉት ከፍተኛ ማስተባበር 155,000 ብር (አንድ መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ ብር ) አሰባስበዋል። በዛሬው ዕለትም በሚኖሩበት ወንጂ ሸዋ ከተማ ድረስ በመሄድ የቀድሞ ድንቅ ግብጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊሰ፣ ዳንኤል ካሣ (የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሪ) እና ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር አስር ሺህ ብር በእጃቸው ያስረከቡ ሲሆን የቀረውን 145 ሺህ ብር ደግሞ በአካውንታቸው እንዲገባ አድርገዋል።

ከዚህ ቀደምም ከአሜሪካ 66 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉት የቀድሞ ጓደኞቹ የኮሮና ወረርሽኝ የበለጠ ተሰባስበው ድጋፉን ለማድረግ እክል ቢፈጥርባቸውም በቀጣይ ይህ ድጋፍ በዚህ የሚቆም እንዳልሆነ እና ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ነግረውናል።

በዛሬው ዕለትም ወላጅ እናቱ ይህን በጎ ተግባር ላደረጉት ሁሉ በያሉበት ፈጣሪ ብድር ይከፍላቸው በማለት መርቀዋል። ሁለቱ የተስፋዬ ወንድማማቾች ተከተል ኡርጌቾ እና ይታገስ ኡርጌቾም በርክክቡ ወቅት በቦታው ተገኝተዋል።

በአሜሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ የተስፋዬ ኡርጌቾ ወዳጆች ያደረጉት ተግባር የሚያስመሰግናቸው ሲሆን ይህን በማስተባበር ረገድ የቀድሞ ግብጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊሰ፣ ዳንኤል ካሣ (የቀድሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሪ) እና ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያር ለዚህ ዓላማ መሳካት ላደረጉት ጥረት ሊደነቁ ይገባል።



👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ