“ፌዴሬሽኑና የቁጥር ስህተት” የአሸናፊ ሲሳይ ትውስታ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከቁጥር አመዘጋገብ ጋር ያጋጠመውን ስህተት እና አሸናፊ ሲሳይን በጓሮ በር ለመሸለም የተገደደበትን የ1991 ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሽልማት ክስተት ልናወሳችሁ ወደድን።

ራሱን ወደ ዘመናዊ አሰራር ለመቀየር እየጣረ የሚገኘው የአሁኑ ፌዴሬሽን በቀደመው ዘመንም አሁንም ቢሆን በተለያዩ ጊዜዎች ከቁጥር አመዘጋገብ ጋር ተያይዞ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ በግላጭ እና በስውር ይቅርታ ሲጠይቅ መኖሩ ይታወቃል። የቅርቡ እንኳን ብንመለከት የወላይታ ድቻን የቢጫ ካር አመዘጋገብ ስህተት ተከቶሎ ሌላኛው ቡድን ሦስት ነጥብ ቀንሶ ቢሰጥም በድጋሚ ሲጣራ የአመዘጋገብ ስህተት መሆኑን ፌዴሬሽኑ አምኖ በአደባባይ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል። በተመሳሳይ ሌሎች በታሪክ አጋጣሚ የተፈፀሙ የቁጥር ስህተቶች በሌሎች ፅሑፎቻችን የምንመለስበት ቢሆንም በዛሬው ዕለት በ1991 የተፈፀመውን የቁጥር ስህተት ከባለ ጉዳዩ አሸናፊ ሲሳይ ጋር እና በዕለቱ ጨዋታውን መቐለ ተገኝቶ በመከታተል የተለያዩ ዘገባዎችን የሠራው አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ በጊዜው የነበረውን ኩነት እንዲህ አስታውሰውን እንዲህ አቅርበነዋል።

“በጣም የሚገርም ጊዜ ነው። ወቅቱ ትንሽ ራቅ ቢልም የሆነውን ሁሉ አስታውሰዋለው። መቐለ ላይ ነው ከጉና ጋር ነበር ጨዋታውን ያደረግነው። ግልፅ የሆነ የማያሻማ ጎል ነው አስቆጥሬ የነበረው። ሆኖም ጎሉን በእኔ ሳይሆን ዳኞቹ በፋሲል ተካልኝ ስም ነው የመዘገቡት፤ ለምን እንደሆነ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ። በዚህ ምክንያት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ኮከብ ጎል አግቢነቱን ላጣ ችዬ ነበር። በኃላ ግን ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በጋዜጣው ላይ ከአንድም ሁለቴ ሦስቴ ቀኑን ፣ ጎሉ የተቆጠረበት ደቂቃ፣ ሰከንዱን ሁሉ ሳይቀር በጋዜጣው ላይ ፅፎ ስለ ነበርና ቪዲዮም ስለነበረ ታይቶ ፌዴሬሽኑ በጓሮ በር ጠርቶኝ ይቅርታ ተጠይቄ ሽልማቱ ተሰጥቶኛል። እኔም በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ሳይሆን ገነነ ከኪሱ አውጥቶ እንደሰጠኝ ነው የቆጠርኩት። በወቅቱ የተፈጠረው ነገር ይሄ ነው።”

ገነነ መኩርያ ወቅቱን እንዲህ ያስታውሰዋል “ታሪኩ ብዙ ነው። ፌዴሬሽን ያሉ ሰዎች በወቅቱ አሸናፊ ሲሳይ ከበረከት ጋር እኩል ጎል አግቢ በመሆን ሽልማቱን መጋራት እና መውሰድ እንዳለበት ያውቃሉ። ግን አሁን ለጊዜው ምክንያቱን መጥቀስ ባያስፈልግም ሆኖም በአዲስ ዘመንም፣ በእኔም ጋዜጣ ላይ ያለውን ነገር እየተከታተልኩ ሁኔታውን እፅፍ ነበር። ፌዴሬሽኑ የአሸነፊን ጎል የቀነሱበት ስህተት ደግሞ መቐለ ከጉና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ጎል አላገባም የሚል ነበር። እንደ አጋጣሚ ደግሞ የዛን ቀን እኔ ክልል እሄድ ስለነበር ጨዋታውን ቁጭ ብዬ መቐለ አይቼ ነበር። ያለውን ሁኔታ በግልፅ ጋዜጣዬ ላይ በተደጋጋሚ እፅፍ ስለነበር ክለቡ እና አሸናፊ ይህን ማስረጃ በማየት ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት አግኝቶ ስንት ብር እንደሆነ አሁን አላቅም ሸልመውታል። የሚገርምህ በሌላ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ፌዴሬሽኑን ተቃውማችኋል በሚል 35 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አስተላልፎባቸዋል። ያው የመልስ ምት መሆኑ ነው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ