በቢሾፍቱ ከተማ የጋብቻ ሥነ ስርዓቱን በፎቶ ፕሮግራም እያጀበ ባለበት ቅፅበት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድንገት ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ያስደሰቱት የቀድሞ የኦሮሚያ ሻምፒዮን እና የቢሸፍቱ ከተማ ተጫዋች ዐቢይ ተሰማ (ብላክ) ይናገራል።
ዐቢይ ተሰማ የተወለው በቢሸፍቱ ከተማ ነው። እንደማንኛው ተጫዋች በሰፈር ቡድን በጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ምንም እንኳን አሁን የህይወት አጋጣሚ ሆኖ ከእግርኳስ ዓለም በመራቅ በሌላ የስራ ዘርፍ ቢሰማራም ቢሸፍቱ ከተማ በምስረታው ወቅት ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። የሠፈር ጓደኛው ከሆነው የቀድሞው የአየር ኃይል፣ ደደቢት፣ ሀዋሳ፣ ወልዋሎ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዳዊት ፍቃዱ (አቡቲ) ጋር በፊት መስመሩ ላይ አጣማሪ በመሆን ተጫውቷል። የወቅቱ የቡታጅራ ከተማ አሰልጣኝ ከሆነው አሥራት አባተ ጋርም በኦሮሚያ ሻምፒዮን አብረው እንደተጫወቱ ሰምተናል። በትናንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ አዲስ በተገነባው የባቡር መስመር (ሀዲድ) ላይ የፎቶ ፕሮግራም ከባለቤቱ ወይንሸት ሽፈራው ጋር እየተነሳ ባለበት አጋጣሚ ሳያስበው በድንገት ከመኪና ወርደው ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ አብረውት ፎቶ በመነሳት ሰርፕራይዝ አድርገውታል።
ዐቢይ የነበረውን ሁኔታ እና የተሰማውን ስሜት አስመልክቶ ይህን ብሎናል።
“በመጀመርያ በጣም አመሰግናለው። የሶከር ኢትዮጵያ ተከታታይ ነኝ። በመቀጠል በትናንትናው ዕለት የተፈጠረውን ነገር መናገር በጣም ከባድ ነው። እስካሁን ደስታው እና ድንጋጤው አለቀቀኝም። እቅልፍም አልወሰደልኝም። የሚደውል እንኳን ደስ አለህ የሚለውም ብዙ ነው። አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አብሮኝ በቆየበት ቅፅበት የመቶ አስር ሚሊዮን ህዝብ መሪ ከየት እንደመጣ ሳላስበው አብሮኝ ፎቶ ሲነሳ ምን እንደምሆን አላቀውም ደንዝዤ ነበር የቆምኩት። ይህ በህይወት ዘመንህ ከስንት አንዴ የሚያጋጥም ነገር ነው። ዐቢይ ዓለሜን (ሠርጌን) ዓለም አድርጎልኛል። ሚዜም አልነበረኝም ዐቢይ የሠርጌ ሚዜ ሆኖልኛል። በጣም ደስተኛ ነኝ።
“እግርኳስ ከልጅነቴ ጀምሮ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት፤ ምንም እንኳን በህይወት አጋጣሚ ወደ ሌላ ዘርፍ ባመራም። አሁንም በማገኘው አጋጣሚ የኢትዮጵያን እግርኳስ አከታተላለው። አሁንም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነኝ። በልጅነቴ የነ ፀጋዬ ባቲ ፣ ፋሲል ተካልኝ ፣ አሸናፊ ሲሳይ ሌሎችም ተጫዋቾች እየተመለከትኩ ነው ያደኩት። የእነርሱ አጨዋወት በአይምሮዬ ተቀርጿል። በተለይ ፀጋዬ ባቲ በጣም የምወደው ውስጤ የገባ ጎበዝ ተከላካይ ነበር። ቢሸፍቱ ምግብ ድርጅት የሚባል ሜዳ ይመጡ ነበር። እዛ ሲሰሩ እያየው ነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍቅሩ ያደረብኝ። ከዛን ጀምሮ ነው እንግዲህ ደጋፊ የሆንኩት። ያው የድሮ ታሪክ ስነግረህ እድሜዬ ትልቅ እንዳይመስልህ ልጅ ነኝ (እየሳቀ)። የሶከር ኢትዮጵያም ተከታይም ነኝ”።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ