“የዘመኑ ከዋክብት ገጽ” ከይሁን እንደሻው ጋር

የመተሐራው ፈርጥ፣ በዕይታውና የተሳኩ ኳሶችን ለአጥቂዎች በማቀበል የሚታወቀው የሀዲያ ሆሳዕናው አማካይ ይሁን እንደሻው የዛሬው የዘመኑ ከዋክብት ገጽ እንግዳችን ነው።

የአልሸነፍ ባይ፣ ታታሪ እና ልባም ተጫዋች መሆኑ የእርሱ መገለጫዎቹ ናቸው። በተለይ ሳይታሰብ ዕይታውን ተጠቅሞ ወደፈለገው አቅጣጫ ለቡድን ጓደኞቹ የሚያቀበለው ኳስ አስገራሚ ነው። በ2007 ድሬዳዋ ከተማን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከማሳደጉ በተጨማሪ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋችም የመሆን ክብርን አግኝቷል። በመተሐራ መርቲ ጀጁ የተወለደው ይሁን እንደሻው በ2010 ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አንስቷል። ምንም እንኳ ዘንድሮ የሚገኝበት ሀዲያ ሆሳዕና ደካማ የውድድር ዓመት ቢያሳልፍም እርሱ በግሉ ጥሩ የሚባል ጊዜን አሳልፏል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት አጋጣሚዎች ብቻ የመጠራት ዕድል ቢያገኝም የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስብስብ ውስጥ የመጫወት ዕድል አግኝቶ በሚገባ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በቁመቱ አጭር በሰውነቱም ቀጠን ያለ ቢሆንም ጥንካሬው ቀላል እንዳልሆነ አብረውት የተጫወቱት ይመሰክራሉ። የዛሬው የከዋክብት ገፃችን እንግዳ የሆነው ይሁን እንደሻው በአዝናኝ ጥያቄዎቹና ገጠመኞቹ ዙርያ ይሄን አካፍሎናል።

በሀድያ ቋንቋ ሠላም በለን እስቲ ?

(በጣም እየሳቀ) ኧረ ብዙም አላውቅም። አንድ ቃል አቃለው እርሱም ጡማ ሒንኪዴ (ደህና ነህ ወይ እንዴት ነህ?) ይሄ ነው ከዚህ ውጭ አላቅም። እየለመድኩ ነበር። ያው ኮሮና መጥቶ ውድድሩ ተቋረጠ እንጂ።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን?

ኤሌክትሮኒክስ ጠጋኝ እሆን ነበር። ምክንያቱም በልጅነቴ አንዳድ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን እገጣጥም ነበር። የማልሰራው ሥራ አልነበረም። ኤሎክትሮኒክ ግን በጣም የምወደው ነገር ነበር። ስለዚህ ኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ ወይም ቴክኒሻን እሆን ነበር።


አብረኸው ብትጫወት የምትፈልገው?

ከተከላካዩ አስቻለው ታመነ ጋር አብሬው ብጫወት ደስ ይለኛል። መሐል ላይ ከሆነ ከሽመልስ ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። አንተን ነፃ እያደረገህ፣ በራስ መተማመንህን እያሳደገ አጠገብህ መጥቶ የሚያጫውት ጥሩ አማካይ ነው ሽመልስ።

የማትረሳው ያዘንክበት ጨዋታ?

በ2006 ብሔራዊ ሊግ ድሬዳዋ እያለው ወደ ፍፃሜው (ፕሪምየር ሊጉ) ለመግባት… አዳማ የገባበት ዓመት ማለት ነው። በዚህ ውድድር እድል ኖሮን በጣም እንጠበቅ ነበር። ጥሎ ማለፉን አልፈን ግማሽ ፍፃሜ ላይ ተሸነፍን የወጣንበት ጊዜ በጣም ያስቆጨኛል።

የአንተ ምርጡ ጎል?

ጅማ አባ ጅፋር እያለሁ አዳማ ከተማ ላይ ያስቆጠርኩት ጎል ሁሌም የማስታውሰው ነው። በዕለቱም የአዳማ ደጋፊዎች ሳይቀር ያደነቋት ጎል ናት። እንዲሁም ድሬዳዋ እያለሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ከሳጥን ውጭ ያስቆጠርኳቸው ሁለት ጎሎች ምርጥ ነበሩ።

የሰውነትህ ጥንካሬ ከኪሎህ በላይ ነው። ከምን የመነጨ ነው?

በግሌ በጣም ብዙ የተለያዩ ልምምዶችን እሰራለው። ያ ይመስለኛል ሰውነቴን እዛው ጥብቅ እንዲል ያደረገው። እንዲሁም በተወሰነ መልኩ እራሴን እጠብቃለው።

ከምግብ የምትወደው?

ሽሮዬን ነዋ (እየሳቀ) ከእርሷ ውጭ ምን ምግብ አለ? እግርኳስ ተጫዋች ሁሉ ሽሮ ነው የሚወደው። ያው በውድድር ላይ ሽሮ ስለማገኝ (እየሳቀ) ሽሮ ነው የምንወደው። ሌላ ምን እንወዳለን።

በእግርኳስ የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

ከድሬደዋ ጀምሮ የማቀው አሁን በአንድ ክለብ አብሮኝ እየተጫወተ የሚገኘው የጥሩ ስብዕና ባለቤቱ ሱራፌል ዳንኤል እንዲሁም ድሬዳዋ አብሮኝ የተጫወተው በጣም ቀልድ አዋቂው ቁም ነገረኛው ሄኖክ አዱኛ የቅርብ ጓደኞቼ ናቸው።

ከእግርኳስ ውጭ የሚያዝናናህ?

ከእግርኳስ ውጭ ሙዚቃ በማዳመጥ፣ የተወሰነ መፅሀፍ በማንበብ ነው ጊዜዬን የማሳልፈው።

ድምፅ ላይ እንዴት ነህ? አንጎራጉርልኝ

አዎ ጥሩ ድምፅ አለኝ… (እየሳቀ) ሶከር በኦዲዮ ድምፅ የሚያስተላልፈው ቢሆን ኖሮ አሪፍ ድምፅ እንዳለኝ ህዝቡ ያውቅ ነበር። በጣም የቴዲ አፍሮ አድናቂ ነኝ።

ገንዘብ አጠቃቀም እንዴት ነህ?

ገንዘብ ላይ አባካኝ አይደለሁም። በጣምም ቆንቋና አይደለሁም። ብቻ መውጣት ባለበት ጊዜ አወጣለው። በአጠቃላይ በአግባቡ በስነ ሥርዓት የምጠቀም ሰው ነኝ

ባለትዳር ነህ? ልጅስ ?

አዎ ባለ ትዳር ነኝ። ትዳር ከመሠረትኩ በቀጣይ ነሐሴ ሲመጣ ሁለተኛ ዓመቴ ይሆናል። ፈጣሪ ከፈቀደ መንገድ ላይ ነኝ። የልጅ አባት እሆናለው ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

ሊጉ ተቋረጠ እንጂ ደስታ አገላለፅህ ልጅህን በተመለከተ ይሆን ነበር ?

አዎ ሊጉ ተቋረጠ እንጂ አደርገው ነበር። ቀጣይ መስከረም ውድድሩ ከተጀመረ እስከዛ ባለቤቴ ትደርሳለች። ያንጊዜ ደስታዬን በደንብ እገልፃለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ