የጨዋታ ዘይቤዎች… ኤክሌክቲካዊ እግር ኳስ (በሚኒሊክ መርዕድ)

(በአሰፋ ካሣዬ ግብዣ የተፃፈ)

ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን በተለያዩ ዘመናት በሀገር ዉስጥ ዉድድር በቀጥተኛ ጨዋታና ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ዉጤታማ ሆኖ የዘለቀ ነዉ፡፡ መስራቾቹ አየለ አትናሽና ጆርጅ ዱካስ በ1920ዎቹ መጨረሻ ቀጥተኛ እግር ኳስ፤ ምታና ሩጥ የጨዋታ ዘይቤ የሚከተል ቡድን አቋቋሙ፡፡

ከጣልያን የአምስት ዓመታት ወረራ በፊትና በኃላ ባሉት የመጀመሪያ ዘመናት ኳስ አርቆ በረጅሙ የመታ ጎበዝ፤ጀግና እና ቴክኒካል ተጫዋች ተደርጎ በብርሃንና ሰላም፤በሮማ ብርሃንና በቄሣር አገር መልዕክተኛ ጋዜጦች የሚወደስበት ጊዜ ነዉ፡፡

“ ‘ጂንጋ’ ለተሰኘዉ ሀገር በቀል ስታይል ልቦናዉ ተከፈተ፡፡”

ጎልማሳዉ ይድነቃቸዉ ተሰማ የ1958 እ.እ.አ የስዊድን ዓለም ዋንጫን በየስታዲዬሞቹ በአካል ተገኝቶ ሲከታተል የማርሻል አርት የሰዉነት ቅልጥፍና፤ የካፑየርና ሳምባ ዳንስ መተጣጠፍ፤ኳስን በሁሉም የሰዉነት ክፍል አንጠባጥቦ፤ አርት አሳይቶ፤ ኳስ መሬት ሳይወድቅ ለሌላ ተጫዋች ማቀበል ለብራዚላዉያን ተፈጥሯዊና ቀላል ለሆነበት ‘ጂንጋ’ ለተሰኘዉ ሀገር በቀል ስታይል ልቦናዉ ተከፈተ፡፡

የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነዉ ይድነቃቸዉ ተሰማ ወደ ሀገር ቤት ሲመለስ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ፊልም ከስዊድን አስላከ፡፡ለፍቅሩ ኪዳኔ ፊልሙን አሳየዉ፡፡ሁለቱ በብራዚል ዉብ ጨዋታ ፍቅር ከነፏ፡፡ፍቅሩ ኪዳኔ የብራዚልን ጂንጋ ስታይል ከማፍቀሩ የተነሳ ብቸኛ ወንድ ልጁን የብራዚል የ1958 ዓ.ም ኮከብ ተጫዋች በሆነዉ ‘ዲዲ’ ብሎ ስም እስከመሰየም ደረሰ፡፡

ፍቅሩ ኪዳኔ በመላዉ የኢትዬጵያ ጠቅላይ ግዛቶች ላሉ ወጣት ኳስ ተጫዋቾች የብራዚልን ጨዋታ ማሳየትና ማብራሪያ መስጠትን ስራዉ አደረገዉ፡፡ብራዚላዉያን በኢትዬጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስ ተጫዋቾች ተፈቀሩ፡፡

የቅዱስ ጊዬርጊስ ተጫዋቾች ብራዚላዉያን አርት የሚሰሩበትን ፊልም ተመለከቱ፡፡ ጥቋቁሮቹ ብራዚላዉያን የሚሰሩት ምትኃት ዉስጣቸዉን አሸነፈዉ፡፡የጋሪንቻ አዝናኝ ፌንታ እና የፔሌ ማራኪ ጎሎች በቅዱስ ጊዬርጊስ ቤት ቦታ አገኙ፡፡

በመንግሥቱ ወርቁ የፔሌን ዉብ ጎል የማስቆጠር ጥበብ፤ በሸዋንግዛዉ አጎናፍር የጋሪንቻ ድሪብሊንግና የኳስ አሰጣጥ ጥበበ መታየት ጀመረ፡፡አሰልጣኝ ይድነቃቸዉ ተሰማ በሂደት ቅዱስ ጊዬርጊስ ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን አደረገዉ፡፡ሌሎች አሰልጣኞችም ዘይቤዉን እየተቀባበሉት በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ጠንካራዉን ዋንጫ አሸናፊዉን ቅዱስ ጊዬርጊስ ቡድን ገነቡ፡፡

‘ሸዋ እና ካሳዬ’

መንግሥቱ ወርቁ፤ሸዋንግዛዉ አጎናፍርና ሥዩም አባተ ዘይቤዉ በይበልጥ ገባቸዉ፡፡ሥዩም አባተ በኢትዬጵያ ቡና እግር ኳስ ቡድን ከይድነቃቸዉ ተሰማ የቀሰመዉን ዉብ የጨዋታ ዘይቤ ከ1977 እስከ 1990 ዓ.ም ባሉት ዘመናት በኢትዬጵያ ቡና ክለብ ዉስጥ አሰረፀ፡፡

ሸዋንግዛዉ አጎናፍር በ1979 ዓ.ም የቅዱስ ጊዬርጊስ ቡድን አሰልጣኝ ሆነ፡፡የዳኛቸዉ ደምሴ፤ገብረመድህን ኃይሌ እና ሙሉጌታ ከበደን ቴክኒካል ክህሎት አስተዋለ፡፡’የተራራ ሩጫ በተራራ ዉድድር ለአሸናፊነት ያበቃ እንደሆነ እንጂ ለእግር ኳስ ተጫዋች ጠቀሜታ የለዉም’ በሚል ከዘመኑ በቀደመ መርሆ በቅደመ ዝግጅት ልምምድ ጊዜ ኳስን መሰረት ያደረገ ሥልጠና ለቅዱስ ጊዬርጊስ ተጫዋቾች ሰጣቸዉ፡፡ጊዬርጊስ ዓመቱን ሙሉ ዉብ ጨዋታ አሳየ፡፡ በዉድድር ዓመቱም የተዘጋጁትን ሁሉንም ዋንጫዎች ወሰደ፡፡

ሸዋንግዛዉ አጎናፍር በ1980 ዓ.ም የምድር ጦር እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ሆነ፡፡ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እቅዱን ሲያቀርብ ‘ጦሩ ይጠልዛል የሚለዉን ስም የሚቀይር ቡድን ልንገነባ ይገባል! ‘ የሚል ፕሮፖዛል አቀረበላቸዉ፡፡ቃልና ተግባር ሰምረዉ ጦሩ በታሪኩ አሳይቶት የማያዉቀዉን አስደናቂ ቡድናዊ አጨዋወት አሳይቶ የ1980 ዓ.ም የኢትዬጵያ ሻምፒዬና ሆነ፡፡

ሸዋንግዛዉ አጎናፍር በአሰልጣኝነት አለመቀጠሉ ይቆጨኛል፡፡ለእኔ ሸዋንግዛዉ አጎናፍር የካሳዬ አራጌ ማሳያ መስታዎት ነዉ፡፡የሸዋንግዛዉ አጎናፍርን የጨዋታ አስተምህሮ በካሳዬ አራጌ ዉስጥ አነበዋለሁ፡፡ሸዋ እና ካሳዬ የአንድ ሀገር የሁለት ክለብ ዉብ እግር ኳስ አፍቃሪ አሰልጣኞች ናቸዉ፡፡

መንግሥቱ ወርቁ በ1980ዎቹ መጀመሪያ የቅዱስ ጊዬርጊስ ቡድን አሰልጣኝ ሆነ፡፡ በ1970ዎቹ ተስፋ ሚካኤል ዳኜን የመሳሰሉ ቴክኒካል ተጫዋቾች ይዞ በመብራት ኃይል ቡድን የፈጠረዉን ዓይነት በወጣቶችና ልምድ ባላቸዉ ተጫዋቾች የተዋቀረ ማራኪ ቡድን በቅዱስ ጊዬርጊስ ቤት ሊፈጥር የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ ተነሳ፡፡መንግሥቱ ወርቁ ፕሮጀክቱን ከግብ ሳያደርስ በኢትዬጵያ ሻምፒዬና ዋንጫ በመብራት ኃይል በመነጠቁ በ1985 ዓ.ም ከኃላፊነቱ ተነሳ፡፡


‘ዋንጫዎች ጎረፉ’

አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ በ1985 ዓ.ም የቅዱስ ጊዬርጊስ ቡድን አሰልጣኝ ሆነ መጣ፡፡ በ3-5-2 ፎርሜሽን በሥስት ኳስ ጎል ጋር የሚደረስበትን ቀጥተኛና የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ዘይቤ መስታዎት፤በርና ግድግዳ የሆኑበትን ሕንፃ አቆመ፡፡ዋንጫዎች ከ1986 እስከ 1988፤ በ1991 እና 1992 ዓ.ም በጊዬርጊስ ቤት ጎረፏ፡፡

ቅዱስ ጊዬርጊስ በ1989/90 በሥዩም አባተ ኢትዬጵያ ቡና እና በ1993 ዓ.ም ታዳጊዎችን በያዘዉ በኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዬኑ የጉላልት ፍርዴ መብራት ኃይል ከተፈተነበትና ከዋንጫ ከራቀበት ዘመን ዉጭ ባሉት ጊዜያቶች የአሥራት ኃይሌ ቅዱስ ጊዬርጊስ በሀገር ዉስጥ ዉድድር ዉጤታማ ሆኖ ዘልቋል፡፡

አሥራት ኃይሌ በ1993 ዓ.ም ከቅዱስ ጊዬርጊስ ጋር ቢለያይም አሰልጣኙ ያቆመዉ ሕንፃ ከ1993 እስከ 2012 ዓ.ም ባሉት ዘመናት ሰርዶቪች ሚቾን በመሳሰሉ አሰልጣኞች እየታደሰና እየተጠገነ አዳዲስ መልክ እየያዘ ዘልቋል፡፡

ቅዱስ ጊዬርጊስም ከየትኛዉም ዘመን በላይ የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግና የኢትዬጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ያሸነፈበት ጊዜም ሆኖ በሪከርድነት ተመዘገበ፡፡

ለ2012 ዓ.ም የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዉድድር ዘመን ዉበቱ አባተ በቅዱስ ጊዬርጊስ ተፈላጊዉ አሰልጣኝ ሆነ፡፡የባርሴሎና ክለብ የደጋፊዎች ማኅበር አባል በሆኑት የቅዱስ ጊዬርጊስ ስፓርት ክለብ አመራሮች ዉበቱ ቢፈልግም ዉል ሳይቋጠር ተሰናከለ፡፡የቅዱስ ጊዬርጊስ አመራሮች ዉብ ጨዋታ፤የዋንጫ አሸናፊነትና ዉጤታማነትን አዋሕዶ የሚያመጣላቸዉን አሰልጣኝ አንድ ቀን መቅጠራቸዉ አይቀርም፡፡

የኢትዬጵያ ቡና ስፓርት ክለብ ’ሐሯዊ የኳስ ንክኪ’

ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የ1970 እ.እ.አ የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን በሜክሲኮ ስቴካ ስታዲዬም በጋዜጠኛነት ተከታተለ፡፡ብራዚሎች ጣልያን ላይ አራተኛዉን ግብ ከጎል እስከ ጎል ተቀባብለዉ ሲያስቆጥሩ የሚዲያ ክፍል ዉስጥ የተቀመጠዉ ፍቅሩ ኪዳኔ ደስታዉን መቆጣጠር አቅጦት አለቀሰ፡፡

በአይሮፕላን ተሳፍሮ ወደ ሪዬዲጄኔሮ ሄደ፡፡ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን የድል ማብሰሪያ በተዘጋጀዉ የሪዬ ካርኒቫል ከብራዚላዉያን ጋር ፈነጠዘ፡፡

ፍቅሩ ወደ ኢትዬጵያ ተመልሶ መጣ፡፡ከሜክሲኮ ይዞ የመጣዉን የብራዚልና ጣልያን ሙሉ ጨዋታ በኢትዬጵያ ቴሌቪዥን እሑድ ነሐሴ 10 ቀን 1962 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት እንዲተላለፍ አደረገ፡፡

ወጣቱ ፍቃደ ማሞ ፊልሙን ተመለከተ፡፡’ሐሯዊ የኳስ ንክኪ’ (Silk Touch) የሚባለዉን የብራዚላዉያን አዲሱን አጨዋወታቸዉን ወደደላቸዉ፡፡

የሐር ጨርቅ ለስላሳነቱና ቀላልነቱ ደስ እንደሚለዉ ሁሉ ብራዚሎችም ‘ተሯሩጠዉ ታግለህ ተጫወት’ የሚለዉን ዘይቤ በማስቀረት ቀላልና ፈጠራ የተሞላበትን፤ቅብብል የነገሰበትን፤ዉብ ጎሎች የሚቆጠሩበትን ፤ለተመልካች ተዝናኖትን የሚሰጠዉን፤በዋንጫ የታጀበዉን የብራዚላዉያን የጨዋታ ዘይቤ ፍቃደ ማሞ አድናቂ ሆነ፡፡

ጎልማሳዉ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የቡና ገበያ ኮርፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ ሆነ፡፡የቡና ገበያ እግር ኳስ ቡድን በ1977 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዥዬን አደገ፡፡ቼንቶ የብራዚሎችን ሐሯዊ እግር ኳስ ወደ ቡና ሊያመጣለት የሚችል ሰዉ አፈላለገ፡፡የጋሽ ይድነቃቸዉ ተሰማ ተማሪ የሆነዉ ሥዩም አባተ ተፈላጊዉ ሰዉ እንደሆነ ተረዳ፡፡

‘ማርና ወተት’

ሥዩም አባተ ከ1977 እስከ 1989 ዓ.ም ድረስ ወጣ ገባ እያለ በቡና ገበያ ቡድን ዉስጥ ሰራ፡፡ የሥዩም አባተ ስልጠናን በ1980ዎቹ የቡና ተጫዋች የነበረዉ አንተነህ አላምረዉ ‘ማርና ወተት’ የሚል ሥያሜ ሰጠዉ፡፡

የማርና ወተት ሥልጠናዉ አርታዊና ዉጤታማዊ ተጫዋቾች የሆኑትን ፀጋዬ ፋንታሁን ፤መንግሥቱ ቦጋለ ፤ ሙሉጌታ ወልደየስ፤ ሚሊዬን በጋሻዉ፤ ዬናስ ተፈራ፤ አሸናፊ በጋሻዉ፤ ካሳዬ አራጌ፤ አብዱራዛቅ አብዱሰዒድ (ናይጄሪያ)፤ ጥላሁን መንገሻ፤ አቢ ሰይድ ችሎታቸዉን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያወጡ፤ በተጋጣሚ ቡድን ላይ የጨዋታ የበላይነት እንዲወስዱ ፤ ዉጤታማ እንዲሆኑ፤ በ1978 እና 1981 ዓ.ም ምድር ጦርን የመሳሰሉ ብረት ቡድኖችን ‘በሐሯዊ የኳስ ንክኪ’ እያሸነፋ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዬን ሻምፒዬና፤ የኢትዬጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ እንዲሆኑ አደረጋቸዉ፡፡

ኢትዬጵያ ቡና ከ1984 እስከ 1988 ዓ.ም በይበልጥ ወደ ቀጥተኛ እግር ኳስ አጨዋወት የተሳበበትና በዉጤት ሲመዘን እዚህ ግባ የማይባል ዘመን አሳለፈ፡፡በ1986 ዓ.ም በሕጋዊ ባለቤት እጦታና በበጀት እጥረት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት ከገደልና ከሞት አፋፍ ተረፈ፡፡

በ1989 ዓ.ም ሥዩም አባተ ‘ተናካሹን አንበሳዉን ቡናን እፈጥራዋለሁ!” ብሎ ቃል ገባ፡፡ለአሥር ዓመታት ከሥዩም ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰሩት የካሳዬ – አሰግድ የተጫዋቾች ትዉልድ በኳስ ቁጥጥር ተጋጣሚዎቻቸዉ ላይ ከፍተኛ ብልጫ እየወሰዱ አሸንፈዉ መዉጣትን መደበኝ ሥራቸዉ አደረጉት፡፡

በዉጤት ልኬት የሥዩም አባተ ቡድን የ1989 ዓ.ም የኢትዬጵያ ሻምፒዬና፤የ1989 ዓ.ም የኢትዬጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ባለቤት፤የ1990 ዓ.ም የኢትዬጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት፤በ1990 ዓ.ም ዛንዚባር በተከናወነዉ የምስራቅና መካከለኛ የአፍሪካ ዋንጫ የነሐሴ ሜዳልያ ተሸላሚ፤አልአህሊን በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በጥሎ ማለፍ ገንድሶ ያለፈ፤ በ1992 ዓ.ም በካሳዬና-አሰግድ የጨዋታ ስትራቴጂ የግብፁን ዛማሌክ በጨዋታ ዘይቤ የተፈታተነ በአህጉራዊ ዉድድር ምርጡ ኢትዬጵያ ቡና ተፈጠረ፡፡

‘ ለዉብ ጨዋታ ዘመሩ፤ ጨፈሩ’

በ1990 ዓ.ም በኢትዬጵያ ብሔራዊ ሊግ የመዝጊያ ሥነሥርዓት ሻምፒዬና ከሆነዉ ከመብራት ቡድን ደጋፊዎች በላይ ስታዲዬም ዉስጥ ሲዘምርና ሲጨፍር የታየዉ ሦስተኛ ሆኖ የጨረሰዉ የቡና ደጋፊ ሆነ፡፡

በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ዋንጫ አጥተዉ ነገር ግን ለዉብ እግር ጨዋታ ደጋፊዎች ሲዘምሩና ሲጨፍሩ የታዩት በ1974 እ.እ.አ የጀርመን ዓለም ዋንጫ ሻምፒዬናዉን ከወሰደዉ የጀርመን ቡድን ደጋፊዎች ከጨፈሩት በላይ በሚሼልስ-ክሯይፍ ቶታል ፍትቦል ለተዋበዉ የብር ሜዳልያ ተሸላሚዉ የሆላንድ ቡድን ደጋፊዎችና ሆላንዳዉያን ዜጎች ወራቶችን በሙሉ የጨፈሩበትና በ1990 ዓ.ም የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚዉ የኢትዬጵያ ቡና ደጋፊዎች የዘመሩበትና የጨፈሩበት ታሪካዊ አገጣሚ ነዉ፡፡

ሥዩም አባተ ከ1992 እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት ዓመታት በፍጥነት ቶሎ ቶሎ የሚያጠቃ፤ቀጥተኛ እግር ኳስ የሚጫወት፤ከመከላከል ወደ ማጥቃት ፈጣን ሽግግር የሚያደርግ፤ለመልሶ ማጥቃት የተዘጋጀ ቡድን ሰራ፡፡

በ1992 ዓ.ም የኢትዬጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫንና በ1993 ዓ.ም የሊጉን አሸናፊ ቅዱስ ጊዬርጊስን በደርሶ መልስ ዉጤት በማሸነፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳ፡፡

“ከወረቀት ወደ መሬት ወረደ፡፡”

በ1994 ዓ.ም የዉድድር ዘመን ሥዩም አባተ ከኃላፊነት ሲለቅ በቦታዉ አንደበተ ርቱዑ ካሳዬ አራጌ ተተካ፡፡ከ1990 እስከ 1994 ዓ.ም በገነነ መኩሪያ ሊብሮ ጋዜጣ ሲተነተንና በካሳዬ አራጌ ርቱዕ አንደበት ሲብራራ የቆየዉ ተጠጋግቶ መጫወት ‘ጂኬ’ በሚል አዲስ ስያሜ በ1995 ዓ.ም ከወረቀት ወደ መሬት ወረደ፡፡

በአዲሱ ፍልስፍና ቁንጅና የተነሳ የቡና ደጋፊ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ፡፡ ሜዳ ላይ በአጨዋወት አስተምህሮ የበላይነት መዉሰድ ከዋንጫ ሽልማት በላይ ትርጉም ያገኘበት ዘመንም ሆነ፡፡አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በአንድ ዓመት የሥልጠና ልምድ ኢትዬጵያ ቡናን የ1995 ዓ.ም የኢትዬጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤትና እና በኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሥስተኛ ሆኖ እንዲጨርስ አደረገዉ፡፡

‘’የታክቲክ ጦርነት ተጀመረ’’

በ1995 ዓ.ም የታክቲክ ጦርነት ተጀመረ፡፡ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወት ከቀጥተኛ እግር ኳስ ጋር ለፍልሚያ ቀረቡ፡፡Ball Possession በሚለዉ የፊፋ ሳይንሳዊ ስታትስቲክስ ቀጥተኛ እግር ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖችን በኳስ ቁጥጥር የቁጥር ብልጫ አሳምኖ ማሸነፍ እንደሚቻልና ለዋንጫ ባለቤትነትም መብቃት ቀላል እንደሆነ ማመሳከሪያ ቡድኖች የተገኙት በካሳዬ አራጌ የ1995 ዓ.ም ኢትዬጵያ ቡና፤በዉበቱ አባተ የ2003 ዓ.ም የኢትዬጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዬኑ ቡና፤በፔፕ ጋርዲዬላ 2009-2012 ዓ.ም ባርሴሎና፤ በካሳዬ አራጌ 2012 ዓ.ም ኢትዬጵያ ቡና ቡድኖች ላይ ነዉ፡፡

ቀጥተኛ እግር ኳስ የሚከተሉ ቡድኖች ካሳዬና ጋርዲዬላን መሰል አሰልጣኞች ኳስ ተቆጣጠረዉ ለመጫወት በታክቲክ የሚደራጇዉን ቡድኖችን ሜዳቸዉ ላይ አፍነዉ በመያዝ አጣድፈዉ ጎል በማስቆጠር እና በራሳቸዉ ሜዳ ላይ ጥቅጥቅ ብለዉ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ፈጣን ሽግግር የተከፋፈቱ ቦታዎችን ቶሎ አጥቅቶ ጎል አስቆጥሮ ማሸነፍ እንደሚቻል በብዙ አጋጣሚዎች አሳይተዋል፡፡

‘ከፕላን ሀ እስከ ፐ’

ካሳዬ አራጌ በ1995 እና 2012 ዓ.ም በአሰልጣኝነት በሰራበት ዘመናት ዉስጥ የራሱን አጨዋወት ተፈጥሯዊ እድገት ለመጠበቅ ለተጫዋቾች በክፍል ዉስጥ በሚሰጠዉ ትምህርት፤ሜዳ ዉስጥ በሚያሰራዉ ልምምድ፤ተጋጣሚ ቡድኖችን በልጦ ለመገኘት በሚነድፋቸዉ ታክቲኮች ሁሌም ከፕላን ሀ እስከ ፕላን ፐ ድረስ የሚሄድ ከችግር መዉጫ ታክቲኮች አሉት፡፡

ተጋጣሚ ቡድኖችም በቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዳይወስድባቸዉ፤የራሳቸዉን ቀጥተኛ እግር ኳስ ታክቲክ ተግባራዊ አድርጎ በጎል አሸንፎ ለመዉጣት በሚነድፏቸዉ ታክቲኮች በ1995 እና 2012 ዓ.ም የዉድድር ዘመናት ጥሩ እግር ኳሳዊ ፏክክር አይተናል፡፡

የወደፊቶቹ ቅዱስ ጊዬርጊስ እና ኢትዬጵያ ቡና ቡድኖች በአጨዋወት አስተምህሮና ዘይቤ ምን ዓይነት ኢኖቬሽንና አዲስ ነገር ይዘዉ ይመጡ ይሆን? ጊዜ የሚመልሰዉ ይሆናል፡፡

ከተጋባዥነት ወደ ጋባዥነት ፈጣን ሽግግር

በጓድ አሰፋ ካሳዬ ተጋብዤ የጨዋታ ዘይቤዎች ላይ ንባቦቼንና ምልከታዎቼን አካፍያለሁ፡፡በተራዬ ደግሞ ቀጣይ ፀሐፊ እንዲሆን ፍፁም ትሬኳትሬስታን ጋብዤዋለሁ፡፡

ጓድ ፍፁም ትሬኳትሬስታ በኳስ ተጫዋችነት አጭር ዘመኑ ቴክኒካል ተጫዋች እንደነበር በተስፋ ለኢትዬጵያ ቡድን ዉስጥ ሲጫወት አስታዉሰዋለሁ፡፡ በፌስቡክ ከዓለም ዓቀፍ እስከ ሀገር ዓቀፍ የእግር ኳስ ታክቲኮችን ጥሩ አድርጎ መተንተን የሚችል ነዉ፡፡

ጓድ ፍፁም ትሬኳትሬስታ በኢትዬጵያ ክለቦች ዉስጥ በየዘመናቱ ያስተዋላቸዉን የጨዋታ ዘይቤዎች በፌስቡክ ፅሁፏ እንዲያካፍለን ጋብዥዋለሁ፡፡እሱም በተራዉ ፅሑፏን በፌስቡክ ፖስት አድርጎ እንደጨረሰ በፈጣን ሽግግር ተረኛ ፀሐፊ ይጋብዛል፡፡



ጸሃፊው ምኒሊክ መርዕድ ነው፡፡ ምኒሊክ በ1990 ዓ.ም በኤልያስ እንዳለ ፕሮጀክት ዉስጥ ለአጭር ጊዜ ሰልጥኗል፤ በታዳጊነቱና ወጣትነቱ ጊዜም በመሃል አማካይነት ለትምህርት ቤትና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጫዉቷል፡፡ በወቅቱ ለቡድን ሥራ የሚጠቅሙ ቴክኒካዊ እና አዝናኝ ጨዋታዎችን በማሳየት ይታወቅ ነበር፡፡ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ዓመታት ከማክሰኞ እስከ እሁድ ድረስ ታትመዉ ይወጡ የነበሩትን ሊብሮና ኢንተር ስፓርትን… መሰል ጋዜጦች አጠቃላይ ገጾች አንብቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፊልም ሙያ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ አሁንም የእግር ኳስ ጨዋታዎች አያመልጡትም፡፡ የስልጠና መፅሐፎችን እና በቪዲዬ የአሰልጣኞች ድሪል ማስተማሪያዎችን ይከታተላል፡፡ በፌስቡክ ገፁ እግርኳሳዊ ጉዳዬችንም ይፅፋል፡፡