በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ በጨዋታ እንቅስቀሴ ላይ ከባድ ጉዳት ከተመለከትንበት አጋጣሚ መካከል የኢትዮጵያ ቡና እና ብሔራዊ ቡድን ታላቅ ተጫዋች ሙሉጌታ ወልደየስ አሳዛኝ ጉዳት አንዱ ነው።
በ1981 በዕለተ ማክሰኞ ምሽት መጋቢት 19 ቀን ነው ይህ አስከፊ ጉዳት በሜዳ ውስጥ የተስተናገደው። ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርጉ በአዲስ አበባ ስታዲየም ነፋሻማና በካፊያ በተቀላቀው አየር ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ የገቡት። አይተኬው ድንቁ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ሙሉጌታ ወልደየስ ሀገሩን ለማገልገል ሰውነቱን አፍታቶ ወደ ሜዳ ገባ። ሆኖም ጨዋታው ቀጥሎ በእረፍት ሰዓት ላይ ሙሉጌታ መልበሻ ክፍል ውስጥ በወቅቱ ለነበረው የቡድኑ አሰልጣኝ ቀይረኝ ከዚህ በላይ መጫወት አልፈለኩም ይለዋል። አሰልጣኙም አሁን ግባ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ እቀይርሀለው ይለዋል። ይህን ተነጋግረው ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ቀጥሎ ነጋሽ ተክሊት (የአሁኑ የኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዝደንት) ሙሉጌታን ለመቀየር ሰውነቱን እያፍታታ በነበረበት ሰዓት ጌቱ ከበደ በጥሩ መንገድ አንድ ኳስ ከመሐል ሜዳ (በአሁኑ አጠራር ከዳፍ ትራክ ወደ ሚስማር ተራ አቅጣጫ) ወደ ፊት ይጥልለታል። ኳሱ ላይ ለመድረስ በሙሉጌታ እና በማላዊ ግብጠባቂ መካካል በሚደረግ ንክኪ የተፈጠረው ሁኔታ አስደንጋጭ ነበር። ሙሉጌታ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዶ ሕይወቱ ያለፈ በሚመስል ሁኔታ ተዘረረ። ተመልካቹ ዘሎ ሜዳ በመግባትም ከፍተኛ ሁከት ተፈጠረ። ብዙ የሚጠበቀውን ያህል መጥቀም ሳይችል ጉዳቱ ሙሉጌታን በጊዜ እንደተወደድ እግርኳስን እንዲያቆም አድርጎታል። ይህንን አስደንጋጭ ጉዳት በቅርብ ርቀት ቀድመው በመመልከት ጨዋታው እየቀጠለ ወደ ሜዳ ሩጠው በመግባት ጩኸታቸውን ያሰሙት ረዳት ዳኛ ጌታቸው ገ/ማርያም እና ተመልካቹ ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት የተፈጠረውን ሁኔታ የተመለከተው ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ጊዜውን ወደ ኋላ 31 ዓመታት በፊት አስታውሰው ይህን አጫውተውናል።
ጌታቸው ገብረማርያም
በወቅቱ እኔ ረዳት ዳኛ ነበርኩ፤ ይሸበሩ ደግሞ ዋና ዳኛ ነበር። ጌቱ ከበደ ወደ ጦሩ የሜዳ ክፍል ጥሩ አድርጎ ያቀብለዋል። ሙሉጌታ ከማላዊው ግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ጉልበቱን መቶት ሲወድቅ አየሁት። ለእኔ በጣም በቅርቤ ስለነበረ ሳየው ጨዋታው ቀጥሏል እኔ ግን ሮጬ ገባሁ። ይሸበሩ እያየው ነው ተጎድቶ ምን እንደነካው የዛኔ እኔንጃ አላውቅም ጨዋታውን አስቀጥሎታል። እኔ ሮጬ ስገባ ሙልጌታ ” ጋሽ ጌቾ ተበላሸው” አለኝ አይዞህ ብዬ ሳልጨርስ ወድያውኑ እግሩ ተንጠልጥሎ እየተንቀጠቀጠ ጉልበቱ በጣም ማበጥ ጀመረ። ከዚህ በኃላ ራሴን ስይዤ ስደናገጥ በቃ ምን ልበልህ ረብሻው ግርግሩ ተኩሱ የጉድ ነበር። ጨዋታውም መቀጠል አልቻለም፤ ጎል ሳይስተናገድበት ሊቋረጥ ችሏል። ይሄን አስታውሳለው። ከዛ ሆስፒታል ሄጄ ጠየኩት በጣም አዝኗል። እስካሁን ድረስ ለእኔ ያለው ፍቅር ልዩ ነው አንተነህ ሩጠህ ህመሜን ያየኸው ይለኛል። አሜሪካ ሆኖ ይደውልልኛል። ሲመጣም አስቦ ይጠይቀኛል። እንደቤተሰቦቹ ነው የሚያየኝ።”
ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ
በወቅቱ የተፈጠረው ነገር አንደኛ ጌታቸው ገብረማርያም ህጉን ጥሶ ነው የገባው። ጨዋታው እየተካሄደ ባንዲራውን ጥሎ እየሮጠ ገብቶ ራሱን ሲይዝ ሰዉ ሙሉጌታ ወልደየስ የሞተ መስሎት አጥሩን ዘሎ ገብቷል። ያ ሁሉ ረብሻና ተኩስ ምን ልበልህ ለዚህ ሁሉ ግርግር መፈጠር ምክንያት ጌታቸው ነው። እኔ እንዳውም ትዝ ይለኛል አበበ ቢቂላ (ከማን አንሼ) በኩል የሆነ ሰውዬ በትልቅ ሰሀን ቆሎ ከምትሸጥ ልጅ ሳህኗን (ኒኬሉን) ነጥቆ ቆሎውን አፍሶ በረኛውን ሊመታ ወደ ሜዳ ገባ። በወቅቱ ፖሊስ ባይኖር ኖሮ ይገሏቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ሜዳው አንድ ዓመት ኢንተርናሽናል ጨዋታ እንዳይካሄድበት ተቀጥቷል። ሙሉጌታም ከእግርኳስ ዓለም ተገለለ። የማላዊው ግብጠባቂ ሀገሩ ገብቶ ከሞተ ከስድስት ዓመት በኃላ ለሙሉጌታ ይቅርታ መጠየቁን ነግረውታል። ይገርምሀል ዋና በረኛ አልነበረም ተጠባባቂ ግብጠባቂ ነበር፤ አጋጣሚ ነው የገባው። ሙሉጌታ ራሱ በእረፍት ሰዓት መልበሻ ክፍል ውስጥ ቀይሩኝ ቀፎኛል እያለ አሰልጣኞቹ እንዴት ብለው ይቀይሩት በጨዋታው ጥሩ እየተንቀሳቀሰ እና የጎል ሙከራ እያደረገ የነበረው እርሱ ነው። እርሱን ካስወጡት ደግሞ ተመልካቹ ይጮህባቸዋል። ስለዚህ ሰው እስክናዘጋጅ ድረስ ተጫወት ብለውት ሊቀይሩት ነጋሽ ተክሊት እያሟሟቀ ነበር ሙሉጌታ የተሰበረው።”
ምስሎች © ከጌዲዮን ሥዩም የፌስቡክ ገፅ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ