ኑሮውን አሜሪካ ባደረገው አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን እና በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አስተባባሪነት እየተሰጠ ያለው የአሰልጣኞች የማነቃቂያ ስልጠና ትናንት ምሽትም ለ3 ሰዓታት ያህል ተሰጥቷል።
ከዚህ በፊት ለ4 ጊዜያት በተለያዩ አሰልጣኞች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ትላንት ምሽትም በሁለት የሃገር ውስጥ አሰልጣኞች አማካኝነት በተሰጠ ትምህርት ቀጥሏል። ከ12:30 ጀምሮ የነበረው የኦንላይን የቪዲዮ ትምህርት “ኮቪድ-19 እና እግር ኳስ” በሚል ርዕስ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ተሰምቷል። ትምህርቱንም አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን እና ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከአሜሪካ እና ከኢትዮጵያ ለሃገራችን አሰልጣኞች ሰጥተዋል።
በተለይ አሰልጣኝ አምሳሉ ከኮቪድ እና እግርኳስ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ሃገር ያለውን ተሞክሮ እና ልምድ በማጣቀስ ትምህርቱን ሰጥተዋል። ኢንስትራክተር አብርሃም ደግሞ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር በተያያዘ ያለውን ነገር እያነሱ ትምህርቶችን አስተላልፈዋል።
በኮንፍረንሱ ላይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች፣ የዋሊያዎቹ፣ የሉሲዎቹ እና ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እንዲሁም የፌደሬሽን የቴክኒክ ክፍል ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 29 የሃገራችን የእግርኳስ ግለሰቦች ተካፍለዋል። ፕረዘንቴሽኑ ከተጠናቀቀ በኋላም በኮንፍረንሱ ላይ የተካፈሉት ግለሰቦች ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ውይይቶችን እንዳደረጉ ተጠቅሷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አብዛኞቹ አሰልጣኞች እግርኳስን ወደ ሃገራችን ለመመለስ የሚያስችል መመሪያ እንዲዘጋጅ ለፌደሬሽኑ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል። በተለይ አሰልጣኞቹ በሃገራችን ያለውን የእግርኳስ እንቅስቃሴ ህይወት ለመስጠት ጥንቃቄ የታከለበት መመሪያ እንዲዘጋጅ ምክሮችን አንስተዋል። አብዛኞቹም አሰልጣኞች እግርኳስን ወደ ሃገራችን ለመመለስ በግላቸው ዝግጁ እንደሆኑ እንደገለፁ ታውቋል።
ሶከር ኢትዮጵያ ስልጠናውን ካዘጋጁት አካላት እንደሰማችው ከሆነ ደግሞ ይህ ስልጠና በቀጣይ ሳምንትም እንደሚቀጥል ተረጋግጧል። በቅርቡ የከፍተኛ ሊግ አሰልጣኞችን ያሳተፈ የኦንላይን ትምህርት መርሃ ግብር ይዘጋጃል ተብሏል። በተለይ ከሚቀጥለው የፈረንጆች ወር ጀምሮ ደግሞ ከእንግሊዝ ሃገር ከሚጋበዙ የእግርኳስ ሰዎች ጋር በመተባበር ስልጠና ለማሰጠት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተገልጿል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ