ሀዋሳ ከሰብሰቤ ደፋር በኃላ ያገኘችው ምርጡ ባለተሰጥኦ አማካይ ነው። በሀገሪቱ ለሚገኙ ታላላቅ ክለቦች በስኬት ተጫውቷል። ኳስን የሚቆጣጠርበት ብቃት ልዩ ከመሆኑ የተነሳ ‘እንኳን ኳስ ብርጭቆ ቢወረወርለት ራሱ እንደ እርሱ ኮንትሮል የሚያደርግ የለም’ የሚባልለት የመልካም ስብዕና ባለቤት የዘጠናዎቹ ኮከብ አማካይ በኃይሉ ደመቀ ማነው?
የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ ማትሪክ ለመውሰድ ተወልዶ ካደገበት ነገሌ ቦረና ከተማ እህቱን ፍለጋ ሀዋሳ ከተማ ይመጣል። እንዳጋጣሚ ሆኖ ታላቅ እህቱ የምትኖርበት አካካባቢ ደግሞ የስመጥር ተጫዋቾች መፍለቂያ የሆነው ኮረም ሜዳ ይገኛል። ያለ እግርኳስ መኖር ለእርሱ ከባድ በመሆኑም በነገሌ ቦረና የጀመረው የእግርኳስ ፍቅር ኮረም ሜዳ ላይ አገረሸ። ከትምህርቱ ይልቅ ጊዜውን ታዳጊዎችን ሰብስቦ በኮረም ሜዳ ሲጫወት በመዋል ማሳለፍ ጀመረ። በኮረም ሜዳ ፍቅር የተለከፈው ይህ ታዳጊ ሲሳይ ሎሬሶ ሰው ማተሚያ ወደሚባል ቡድኑ ወስዶት ይልማ በሚባል ሰው እየሰለጠነ መጫወት ጀመረ። ከራሳቸው ገንዘብ እያዋጡ አለታወንዶ እና ይርጋለም እየሄዱ ይጫወቱ ነበር። አጨዋወቱን አይተው የተደሰቱት አለታ ወንዶዎች እንዲጫወትላቸው ጠይቀውት 26 ክለቦች በሚሳተፉበት ለደቡብ ክልል የክለቦች ሻምፒዮን ውድድር ጅንካ ሄዶ ቡድኑ አራተኛ ቢወጣም እርሱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተሸልሟል። ከእርሱ ጋር በተቃራኒ የተጫወቱ ሁሉ ቡድናቸው ውስጥ እንዲገባ ይፈልጉ ስለነበር በ1993 የክልል ክለቦች ውድድር ላይ አሸናፊው ይረረጋለም ከነማ ወስዶት በብሔራዊ ሊግ ቢጫወትም ውድድሩ በተለያየ ምክንያት ይቋረጥ የነበረ መሆኑ እና ውድድሩ ሳይጠናቀቅ ከነአካቴው መቋረጡ የበኃይሉ የነገ የእግርኳስ ህይወቱ ላይ ፈተና ተጋረጠበት። ወደ ፊት ትልቅ ተጫዋች የመሆን ህልሙን ለማሳካት ሁሌም የሚተጋው በኃይሉ ወደ ሀዋሳ በመሄድ ሙከራ ቢያደርግም በወቅቱ ሀዋሳ ብዙ ተጫዋቾችን ከአዲስ አበባ ገዝቶ የነበረ በመሆኑ አልተሳካለትም። ሆኖም የክለቡ አመራሮች ‘ተሰፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩትን እንዲሁ ከምንበትን እንደ ” ቢ” ቡድን ዓይነት እንፍጠርና እናሰባስባቸው’ በማለት በሰሩት በዚህ ስብስብ ውስጥ መካተት ቢችልም ብዙም ሳይቆይ ቡድኑ ይፍረስ ተብሎ ሲወሰን አምጣቸው ኃይሌ (የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ም/አሰልጣኝ) ‘አይበተኑም እኔ አሰለጥናቸዋለው’ ብሎ እርሱ ጋር መስራት ጀምሯል።
ሀዋሳ ከተማ ለዝግጅት እንዲረዳው አምጣቸው ከያዛቸው ታዳጊዎች ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ሲያደርግ በኃይሉ በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጉም በተጨማሪ ጎሎችን ያስቆጥራል። ታዲያ በዚህ ወቅት በዛን ዘመን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበረው አዲሴ ካሳ ለበኃይሉ መልክት ይልክለታል። ” በሦስተኛው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ የምትጫወተው ከዛኛው ቡድን ጋር ሳይሆን የሀዋሳን መልያ አድረገ ስለሆነ ተዘጋጅ” ይለዋል። በዚህ በጣም ተደስቶ ዕድሉን ለመጠቀም በሀዋሳ መልያ የራሱን ቡድኑን ገጥሞ ጎል አስቆጥሮ ዕድሉን በአግባቡ ተጠቅሞ በአምስት መቶ ብር ደወሞዝ በ1994 ሀዋሳ ከተማ ሊቀላቀል ችሏል። ሀዋሳ በገባበት ሁለቱ ዓመታት እንደ ቡድን ላለመውረድ የሚጫወት ደካማ ቡድን የነበረ ቢሆንም በኃይሉ በግሉ መልካም እንቅስቃሴ አሳይቷል።
በደደቢት በአዳማ ፣ በመድን ፣ በሙገር እና በሌሎች ክለቦች ሲጫወት የምናቀው ግሩም ባሻዬ በኃይሉን እንዲህ ይገልፀዋል። ” እግርኳስን ሲጫወት አቅልሎ የሚጫወት ጭንቀት ምናምን የሌለበት ነው። አንዳንዱ ለምሳሌ ልምምድን አቅልሎ ይጫወት እና ወደ ጨዋታ ሲገባ የሚችለው ነገር ጠፍቶት የሚያደርገውን ሲያጣ ትመለከታለህ። እርሱ ግን የትም ክለብ ይጫወት ምንም ነገር የማይገድበው እግርኳስን በትክክል ተዝናንቶባት የሚጫወት ሰው ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥም ሌላ ሀገር ካየሁዋቸው ከዚዳን ቀጥሎ እስካሁን ድረስ ነው የምልህ ኳስ አይደለም በአየር ላይ ብርጭቆ ብትሰጠው ሁሉ ኮንትሮል ማድረግ የሚችል የለም። እርሱ አማካይ ብቻ አይደለም ማግባት ሲፈልግ የሚያገባ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች የሚያመቻች ዘጠና ደቂቃውን ሙሉ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፍ። ምን ብዬ ልንገርህ በጣም ሲበዛ መልካም ሰው ነው”።
አመለሸጋው በኃይሉ የ1996 ሀዋሳ ከተማ የሚያቆመው ጠፍቶ በጥንካሬ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የክልል ቡድን ሆኖ ሲያነሳ በርከት ያሉ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ከመፍጠሩ በተጨማሪ የውድድሩ አጥቂዎች የዓመቱን ጎላቸውን አስራ ሦስት አድርሰው ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆነው ሲሸለሙ እርሱ ከአማካይ ስፍራ ተነስቶ 11 ጎል ማስቆጠር የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቁ በኃይሉ ምንያህል ድንቅ ተጫዋች መሆኑን ያሳያል። በ1997 የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ሀዋሳ ጋር አሳክቶ፣ ሁሉንም ጨዋታዎች ለሀዋሳ በሁለት ዓመት ውስጥ በመጫወት መልካም የውድድር ዓመትን አሳልፎ በአሰልጣኝ ሚቾ ከፍተኛ ፍላጎት በ1998 ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀል ችሏል። ሆኖም እንዳሰበው ሳይሆን ያልጠበቀው ነገር አጋጥሞት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ ከፈረሰኞቹ ጋር አሳክቶ ኮንትራቱ ሳይጠናቀቅ በስምምነት ተለያየ ሲሆን በድጋሚ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ሀዋሳ በመመለስ የ1999 የሊጉ ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ማግኘት ችሏል።
ምንም እንኳን የልብ ደጋፊነቱ ለኢትዮጵያ ቡና ቢሆንም በሀዋሳ የእግርኳስ ቤተሰብ ዘንድ ከዘጠናዎቹ መጀመርያ ጀምሮ የሊግ ውድድሮችን በመከታተል የሚታወቀው ቴዎድሮስ ታዬ በኃይሉን እንዲህ ይገልፀዋል። “በሀዋሳ ከነማ ታሪክ ከ1990 ከሰብስቤ ደፋር በኋላ የመጣ ድንቅ አማካይ እርሱ ነው። በጣም እልኸኛ ፣ ከመሐል እየተነሳ ጎል የሚያገባ እና እርሱ ከሚያገባ ይልቅ ለአጥቂዎች ጨርሶ በመስጠት እነርሱ ሲያገቡ ከእነሱ በላይ የሚደሰት በጣም ታታሪ ተጫዋች ነው። ከሜዳ ውጪ ሰው አክባሪ ለጓደኞቹ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ለተቸገሩ ደራሽ ቅን የሆነ ተጫዋቾች ነው”።
ከሁለት ዓመት ሀዋሳ ከተማ ቆይታ በኋላ 2001 ላይ ኢትዮጵያ ቡና በመቀላቀል ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት እርሱ በሚያስቆጥራቸው ጎሎች ቡና የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ማንሳት ችሎ እንደነበረ ይታወሳል። ሆኖም ክለቡም ደጋፊዎቹም አይተውት ሳይጠግቡ ኮንትራቱ ገና ሳያልቅ ሳይታሰብ ወደ ጀርመን ሀገር አቅንቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰቦች ማዘናቸው እና እርሱም ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።
በጀመርን ሀገር እስካሁን ኳስ እየተጫወተ የሚገኘው በኃይሉ ምንም እንኳን በሀገሪቱ በሦስት በተከፈሉ የቡንድስሊጋ ዲቪዚዮንኖች ውስጥ ባይጫወትም በክልል ደረጃ በሚደረጉ ብዛት ባላቸው ቡድኖች በሚገኙበት ሊግ ውስጥ ተጫዋችም ም/አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
በሀዋሳ አብሮት እንደተጫወተ የሚታወቀው እና የወንድሙ ያህል የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የሚነገረው ለረጅም ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለወልቂጤ ከተማ በአሰልጣኝነት እና በተጫዋችነት እየሰራ የሚገኛው አዳነ ግርማ ስለ በኃይሉ እንዲህ ይላል። ” የፈጣሪ ያለህ!! በኃይሉ ማለት አማካይ ሆኖ ጎል በጣም የሚያገባ ፣ ኮንትሮሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደርሱ አላየውም ፣ አያቆመውም ያልከውን ኳስ እርሱ በቀላሉ ይቆጣጠረዋል። በራስ መተማመኑ ደስ የሚል ፣ አጭር ይመስላል ግን የግንባር ጎል በጣም የሚያገባ። በጣም ቅን መልካም ሰው ነው። አንተ ማንኛውንም ነገር ብታስብ እርሱ በመልካም የሚረዳ፣ እውነቴን ነው የምልህ የቅኖች መጀመርያ የምለው ምርጡ ወንድሜ ነው”።
በብሔራዊ ቡድን ከ1996 – 2000 ለተከታታይ አራት ዓመት ተመርጦ ሲጫወት ሁለት የሴካፋን ዋንጫዎችን ማሳካት የቻለ ተጫዋች ነው። በዘጠናዎቹ ኮከቦች አምዳችን የዛሬው እንግዳችን በኃይሉ ደመቀን ከጀርመን ሀገር አግኝተነው የእግርኳስ ህይወቱን አጋርቶናል።
“በእግርኳስ ህይወቴ እስካሁን ድረስ በጣም ደስተኛ ነኝ። በሀገሬ በተጫወትኩባቸው ሦስት ክለቦች ሁለት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፣ ሁለት የጥሎ ማለፍ ዋንጫ፣ እና አንድ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አንስቻለው። ለሀገሬም በብሔራዊ ቡድን ሁለት የሴካፋ ዋንጫን አሳክቻለው። ይህ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው። ከሀገሬም ከወጣው በኃላ በምኖርበት ጀርመን ሀገር በትልቅ ደረጃ መጫወት የምችልበት ዕደል አግኝቼ ነበር ። ሆኖም የጀርመን ሀገር ህግ በተለያየ ምንክንያት እዚህ ሀገር እንደገባህ ወድያውኑ እንደልብህ እንድትንቀሳቀስ አይፈቀድልህም ፤ ከሆነ አካባቢ በቀር ወደ ሌላ መንቀሳቀስ አትችልም። በዚህ ምክንያት በጀርመን ትልቅ ክለብ የመጫወት ዕድሌ ሳይሳካ ቀርቷል። እስካሁን እግርኳስ እየተጫወትኩ እያሰለጠንኩ እገኛለው። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ለእኔ የእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ ስኬት ነው።
“ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደገባሁ ሀዋሳ እንደነበረኝ ብቃት እና ጥሩ የውድድር ጊዜ ጊዮርጊስም እደግመዋለው ብዬ ጠብቄ ነበር። ሆኖም የሚገባውን ያህል አገልግሎት አልሰጠውም። ያለኝን አቅም አውጥቼ እንዳላሳይ የተለያዩ ችግሮች ነበሩብኝ። ከአሰልጣኝ ሚቾ ጋር ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ። ያለ ቦታዬ ማሰልፍ እና ተጠባባቂ ወንበር ላይ ማስቀመጥ። በአጠቃላይ ብዙ አለመስማማቶች ነበሩ። ይሄን ስል ከሚቾ ጋር ብቻ ነበር ጥሩ ግኑኝነት ያልነበረኝ። ከዚህ ውጪ ቡድኑ የሚገርም ስብስብ የነበረበት በብቃትም በስብዕናም በጣም ምርጥ የተባሉ ተጫዋቾች የነበሩበት ክለብ ነበር። የማልረሳው ደስ የሚል አሪፍ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። በመጨረሻም ለሁለት ዓመት ነበር የፈረምኩት። ቀሪ አንድ ዓመት ኮንትራት ቢኖረኝም ክለቡ እንድቆይ ብፈልግም ከሚቾ ጋር በነበረኝ አለመስማማት ከሰጡኝ ብር ላይ የአንድ ዓመቱን ከፍዬ ወደ ሀዋሳ ተመልሻለው።
“ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሁለት ዓመት ውል ነበርኝ። አስደሳች የሆነ በዋንጫ የታጀበ ደስ የሚል ቆይታ እያደረኩ ባለበት ወቅት የአሁኗ ባለቤቴ የቀድሞ እጮኛዬ ቀድማኝ ወደ ጀርመን ሀገር ትሄዳለች። በአንዳንድ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ መቀመጥ አትችልም ነበር። ከሄደች በኋላ ለአንድ ዓመት ተለያይተናል። በብዙ ሰው እንደሚታወቀው እኔ ለመሄድ ብፈልግ ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅ ይታወቃል። ለኔ እንደአጋጣሚ ሆኖ ፕሮሰሱ በአንድ ሳምንት አለቀ። ኢትዮጵያ ቡና ከመግባቴ በፊት ይሄን አደርጌ ገንዘብ ወስጄ እሄዳለው፣ የሚል ነገር ስለ እውነት ለመናገር ምንም ዓይነት ሀሳብ አልነበረኝም። ጭራሽ ከሀገሬ የመውጣት ፍላጎት ዓላማው ሀሳቡም የሌለኝ ሰው ነበርኩ ። እንዳጋጣሚ ሆኖ ነገሮች ባላሰብኩት ሁኔታ ሄደው ዕድሉ ሲመጣ ደነገጥኩ ፤ ለመወሰን ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኛል። ግን መጨረሻ ላይ የህይወት ነገር ሆኖብኝ እንጂ ኢትዮጵያ ቡናን ለመጉዳት (አቅጄ ለመጥፋት ያደረኩት) ነገር አይደለም። በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም፣ የክለቡ አመራሮችም ይህን ቃለ መጠይቅ ለሚያነቡ ሁሉ ከዚህ በፊት እንዳደረኩት እጅግ በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ።
“አሁን ላይ ሆኜ በዛን ጊዜ ባደርገው ብዬ የምቆጨው ነገር የለም። ቅድም እንዳልኩት በክለብም በብሔራዊ ቡድንም ውጤታማ ጊዜን አሳልፌያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኳስ ተጫዋች ማሳካት የሚፈልገው ነገር ሁሉ አግኝቻለው። የምቆጨው ካለ በሁለት ነገር ነው። አንደኛው አሁን ላይ ሆኜ ምን አለ የዚህ ዘመን ተጫዋች በሆንኩ በማለት እቆጫለው። ምክንያቱም ወደ ውጪ ወጥቶ ለመጫወት አሁን ዕድሉ ሠፊ ነው። በእኛ ጊዜ ውጪ ወጥቶ ለመጫወት ዕድሉ አልነበረም። እንደዚህ ትኩረት አድርጎ ስለ ተጫዋቾች ግለ ታሪክ የሚነሳበት የሚዲያ ዘገባ እንኳን በኛ ጊዜ አልነበረም። ተጫወትክ ማታ የተወሰነ ዜና ይሰራል። አሸነፈ፣ ተሸነፈ አለቀ። የዚህ ዘመን ተጫዋች ብሆን ኖሮ ፕሮፌሽናል ሆኜ ሌላ ቦታ እገኝ ነበር። ሌላው የአፍሪካ ዋንጫ የገባው ስብስብ ውጥ አለመኖሬ ይቆጨኛል። ከእኔ ጋር አብረው ይጫወቱ የነበሩ ልጆች የአፍሪካ ዋንጫ መጫወታቸውን ሳይ ተቆጭቻለው።
“በእግርኳስ ህይወቴ መቼም የማረሳው አጋጣሚ በ1997 ሀዋሳ ከሙገር የጥሎማለፍ የዋንጫ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል። እኔ ደግሞ የዛኔ ኮንትራቴ በዚያኑ ዓመት ስለሚያልቅ ከሰኔ ወር በፊት በዘጠና ስምንት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመሄድ አስቀድሜ ፈርሜ ለሀዋሳ እየተጫወትኩ ነበር። ይሄንን ነገር የሀዋሳ አመራሮች ሰምተው ለሁለት ዓመት ከማንኛውም የእግርኳስ ውድድር ተቀጥተሀል የሚል ደብዳቤ ሰጡኝ። በዚህም ብዙ ችግር ውስጥ ገባሁ። ጨዋታዎችም እንዳልጫወት ልምምድ እንዳልሰራ ሁሉ አድርገውኛል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሀዋሳ ከተማ ለጥሎ ማለፉ የፍፃሜ ጨዋታ ከሙገር ጋር ደረሰ የጨዋታው ቀን ሊደርስ ሲል ኃላፊዎቹ መጥተው አናገሩኝ ለጊዜው ቅጣትህን አንስተህልናል። እኔ መጫወት እንደምፈልግ እነርሱም እንድጫወትላቸው ፈለገው ጠየቁኝ እሺ ብዬ የጨዋታው ቀን ደረሶ ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀመጡኝ። ሙገር ቀድሞ አግብቶ እየመራ ነበር። ከእረፍት በኃላ ገባሁ፤ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አካባቢ በጣም በጣም ቆንጆ ጎል ነበር ያገባሁት። ከአስራ ስድስት ሃምሳ ውጭ አዳነ ግርማ በግንባሩ ያቀበለኝን በቮሊ መትቼ አገባሁ። በዛን ሰዓት የነበረው ደስታ በህይወቴ በኳስ ከተደሰትኩባቸው፣ በራሴ ከኮራሁባቸው ቀናቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ጎሉን እንዳስቆጠርኩ ቀጥታ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሄጄ በቪ ምልክት ደስታዬን ገልጫለው። አንደኛ ችግር ውስጥ የገባሁት ጊዮርጊስ በመግባቴ ነው። ሁለተኛ ተቀይሬ ስገባ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች በጣም አነቃቅተውኝ ነበር። እንዲሁም ፈርሜያለው በቀጣይ ዓመት የጊዮርጊስ ተጫዋች ነኝ። አጠቃላይ የኔ መቀጣት ብዙ ነገሩ ከጊዮርጊስ ጋር ይገናኝ ስለነበረ ደስታዬን ከጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጋር ምልክት እያሳየው ገልጫለው። ሌላው በጣም የሚገርምህ ይሄም ሌላ ታሪክ ነው። እኔ ጎል ሳገባ በአለቀ ሰዓት ወሳኝ እኩል ለኩል ያደረገ ጎል ነው። አዳነ ግርማ እና አንዷለም ነጋ (ቢጣ) ሁለቱም አንዳንድ ቢጫ ነበረባቸው። ጎል አግብቼ ደስታቸውን ማልያ አውልቀው ሲገልፁ ሁለቱም በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጡ። በቃ ቀሪው ሠላሳ ደቂቃ ጭማሪ በዘጠኝ ልጅ እኔና አህመድ ጁንዲ በጉልበት ቀጥ አድርገናቸው በመለያ ምት አሸንፈን ዋንጫ ያነሳንበት ሙሉ ቲሙ ወደ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሄዶ ደስውታውን የገለፀበት መንገድ መቼም የማረሳው ነው።
“የተክለ ሰውነት ጥንካሬዬ የመጣው በልጅነቴ ከአቅሜ በላይ እጅግ ደክሜ ነበር የምሰራው። ይህ ደግሞ በዕውቀት የታገዘ ስላልነበረ ከዕድሜ ጋር ያልተመጣጠነ ነገር እሰራ ስለነበር። በጣም ቀጫጫ ነበርኩኝ። ‘እንድያውም ቁመቱ አይጨምርም እንጂ በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው።’ እስክባል ድረስ አጭር ቀጫጫ ነበርኩ ይህ የሆነው ተፈጥሮዬ ሳይሆን ከልክ በላይ ራሴን በማድከም ሰውነቴ እና ቁመቴ እንዳያድግ አድርጎታል። ያ ነገር አለፈ እና በኃላ በትልቅ ክለብ መጫወት ስጀምር፣ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች ስትመራ፣ የተመጣጠነ ትክክለኛ ልምምድ ስትሰራ ታፍኖ የነበረው ሰውነቴ እየወጣ መጣ። ሌላው ትልቁ ነገር ተወልጄ ያደኩበት ነገሌ ቦረና በመሆኑ ይመስለኛል። ነገሌ ለሰውነት ገንቢ የሆኑ ነገሮች ሁሉ በቂ ሁኔታ በመኖሩ ጥንካሬውን እያገኘው የስፖርተኛ አካል እንዲኖረኝ አድርጎኛል።
“ከሀገር ከወጣው በኋላ ሦስት ጊዜ ወደ ሀገሬ መጥቻለው። ስታድየም ተገኝቼ ጨዋታዎችን ለመከታተል አጋጣሚ ነበረኝ። እኛ በነበርንበት ዘመን የሚጫወቱ እና የአሁኑ ዘመን ያሉ ተጫዋቾች ዘንድ የጎላ ልዩነት አለ። ከተበላ በፍላጎት የመጫወት ችግር አያለው። ሌላው በእኛ ጊዜ አንድ ሁለት ተጫዋች ብለህ ነጥለህ የምትጠራው ጊዜ አልነበረም። በሁሉም ቡድን ውስጥ ብዙ ቁልፍ ብለህ የምትጠራቸው ተጫዋቾች ነበሩ። አሁን ላይ ሆነህ ስታየው በአጠቃላይ በሊጉ ምርጥ ብለህ የምትጠራው፣ የምትሰማው ብትቆጥር ከአስር አያልፉም። ሁሌም ተደጋጋሚ ስም ነው ያለው። ይህ ማለት የበፊቱ የተጫዋቾች ጥራት የተሻለ ይመስለኛል። ለመተቸት አይደለም ፤ አነፃፅር ከተባለ ይህ ልዩነት ስለሚታየኝ ነው።
“ቴክኒካል ክህሎቱን በተፈጥሮ የተሰጠኝ ቢሆንም ልጅም እያለው ጀምሮ የሰው ምክር እሰማለው አድናቆትም ቢኖር በሚጠቅመኝ በኩል እጠቀምበታለው። ጠንክሬ በመስራቴ ያመጣሁት ነው። ሌላው ግን እኔ ጋር ጨዋታም ልምምድም አንድ ነው ምንም ልዩነት የለውም። ተመሳሳይ ስሜት ይዤ ነው ወደ ሜዳ የምገባው። ቀልድ ምናምን አላቅም ሜዳ ከገባው ልምምድ ጨዋታ አልመርጥም። ለጨዋታ የምጨምረው ለልምምድ የምቀንሰው ነገር የለም። ማንኛውም ጨዋታ ስገባ ራሴን አስጨንቄ መግባት አልፈልግም ራሴን ነፃ አድርጌ ነው የምጫወተው። ብዙ ሰውም ይለኛል። ‘ራስህን ነፃ አድርገህ ሳትጨናነቅ ነው የምትጫወተው’ ይሉኛል። የማበላልጠውም ቡድን አይኖርም ሜዳ የምገባው ለማሸነፍ ብቻ ነው። መሸነፍ አልወድም።
“አሁን ኳስ እየተጫወቱ ያሉ ወደፊትም መጫወት ለሚያስቡ ከኔ ህይወት ሊማሩ ይገባቸዋል ብዬ የማስበው ነገር አለ። አመጣጤን ስታየው ከነገሌ ቦረና ነው የመጣሁት። ነገሌ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ካሉበት በጣም የራቀች ክፍለ ሀገር ናት። እንዲያውም ያኔ ብሔራዊ ሊግ የሚሳተፍ ቡድን ሁሉ አልነበረም። እና እኔ ከዛ ነገር ውስጥ ነው የወጣሁት። ኳስ ተጫዋች መሆን የሚፈልግ ሰው ጠንክሮ ከሰራ ያለውን ነገር ለማዳበር የሚሮጥ ከሆነ ጥሩም ይሁን ጥሩ ያልሆነ የሰዎችን አስተያየት እየተቀበለ። ከፊት ለፊቱ ያለውን ዓላማ እያየ ከሰራ እና ከጣረ የማይደረስበት የለም። ሩቅ ሀገር የሚኖሩ ወጣቶች ከእኔ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል። አሁን ያለውን ነገሌ ቦረና አይደለም የምነግርህ በዛን ሰዓት ያለውን ነው። ቢያንስ አሁን ብሔራዊ ሊግ የሚጫወት ቡድን አለ። ስለዚህ ሰው ከለፋ እና ዓላማ ካለው ለዚያ ነገር መቶ ፐርሰንት እየሰጠ የሚሔድ ከሆነ ያሰበበት ይደርሳል። እኔን አስበኝ ከዛ ውስጥ ወጥቼ ነው በትልቅ ክለብ የተጫወትኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁሉ ዋንጫ ያነሳሁት። አንድ ኳስ ተጫዋች ማሳካት የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አሳክቻለው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት የቻልኩት ከዛ ወጥቼ ስለሆነ ከኔ ህይወት ሊማሩ ይገባል እላለው።
“የቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነኝ ሁለት ሴት አንድ ወንድ ልጅ አለኝ። ሁሉም የእግርኳስ ፍቅር አላቸው። ኳስ ሲባል ይደነግጣሉ! በጣም መጫወት ይፈልጋሉ። ወንድ ልጄ አሁን ስምንት ዓመቱ ነው። ወደፊት ትልቅ ደረጃ ይደርሳል አይደርስም ለማለት ገና ስምንት ዓመቱ ስለሆነ አሁን በርግጠኝነት መናገር አይቻልም። የመጫወት ፍላጎቱ አለው። በሳምንት ሁለቴ የሚጫወትበት ቡድን አላቸው። የእርሱን ነገር ዕድሜው አስር አስራ አንድ ሲደርስ የኔ ደም አለው የለውም የሚለውን ወደ ፊት ነው ማየት ነው የምችለው። ሴቶቹም ቢሆን በጣም የኳስ ፍቅር አላቸው ይጫወታሉ።
“በመጨረሻም በዚህ ቃለመጠይቅ ሳላመሰግናቸው ማለፍ የማልፈልጋቸው ሰዎች አሉ አዲሴ ካሳ ፣ ጋሽ ከማል፣ ነገሌ ቦረና እያለው የስፖርት አስተማሪዬ በእኔ ላይ በጣም ብዙ የለፋ ሰውም አለ ግዛቸው አሰፋ ይባላል ፤ ነፍሱን ይማረው በህይወት የለም። እነዚህ ሦስት ሰዎች በልዩነት እጅግ በጣም የማመሰግናቸው ናቸው። ወደ ትልቅ ደረጃ ከደረስኩ በኃላ አሥራት ኃይሌ ገና በታዳጊነቴ በእኔ አምኖ ብሔራዊ ቡድን እንድጫወት ያደረገኝ እርሱ ነው። በአጠቃላይ እነዚህ እና ሌሎች ሰዎችን ጭምር አመሰግናለው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ