በተለያዩ የውድድር አይነቶች የስፖርተኞች የመጨረሻው ግብ ማሸነፍ እንደሆነ ማንም አይጠፋውም፡፡ በእግርኳስም ጉዳዩ ተመሳሳይ ነው፡፡ በእርግጥ ማሸነፍ ብቻውን የማያስደስተው የእግርኳስ ማህብረሰብ አለ-ጨዋታው ላይ ውበት ቢታከልበት የሚመርጥ፤ አዝናኝነቱ ጎልቶ ውጤታማ መሆንን የሚሻ፡፡ ለብዙዎች ሁለቱንም እያሳኩ መጓዝ አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡ የውጤትና የማራኪ አጨዋወትን ጎራ በዋናነት የሚለያያቸው ይኸው የማሸነፍ ጉጉት ጉዳይ ነው፡፡
ይበልጡን ውጤት ላይ ትኩረት የሚያደርገው የእግርኳስ ሥልጠና ማሸነፍን ላይ ብቻ አጽዕኖት ስለሚሰጥ በተጫዋቾች ተፈጥሯዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል-በተለይ በታዳጊዎች ሥነ-ልቦና እና አመለካከት ዙሪያ፡፡ ማሸነፍን በጥብቅ መፈለግ ምንም ስህተት የለውም፡፡ የትኛውም አሰልጣኝ ከመሸነፍ ይልቅ ማሸነፍን እንደሚመርጥ የማያወላዳ ሐቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለማሸነፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እና ማሸነፍን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርጎ መመልከት ይለያያል፡፡ በሁሉም ስፖርቶች ሊገኝ የሚችለው ውጤት ማሸነፍ ብቻ ስላልሆነ “ካላሸነፍን!” ተብሎ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባትም ጤናማ አካሄድ አይደለም፡፡ አሰልጣኞችም በዋናነት ሁለት ጉዳዮች ማሸነፍ እና መሸነፍን እንደሚወስኑ ማወቅ አለባቸው፡፡
1) በአንድ ውድድር ላይ ተጫዋቾች ወይም አጠቃላይ የቡድኑ የተጫወተበት ብቃት
* እያንዳንዱ ተጫዋች በአንድ ቡድን ውስጥ የሚከተተው በተወሰነ ደረጃ ለመጫወት ብቃት ስላለው ነው፡፡ “ተጫዋቹ ካለው ብቃት ምን ያህሉን አውጥቶ ተጠቀመ?” የሚለው ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ማንኛውም ተጫዋች -በተለይ የመጀመሪያ ተሰላፊ- በየትኛውም ሁኔታ ከምርጥ ብቃቱ በታች መጫወት ማለት ለቡድኑ መሸነፍ በር በር ከፋች ሆነ ማለት ነው፡፡
2) መርኃግብር
* ሌላው ማሸነፍን እና መሸነፍን የሚወስነው ጉዳይ የውድድር የጥራት ደረጃ ነው፡፡ አንድ ጊዜ የውድድሩ መርሀ ግብር ከታወቀ ቀጣዩ ነገር ዘላቂ ብቃት የማሳየት ነገር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቡድን ከደካማ ተጋጣሚ ጋር ሲጫወት ወጥ ብቃቱን በአግባቡ ከተጠቀመ እንደሚያሸንፍ እርግጥ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ግን ሁል ጊዜ የሚሳካ ላይሆን ይችላል፡፡ “ስኬታማትን በውድድር ከሚገኝ ውጤት ይልቅ ሙሉ አቅምን አውጥቶ መጠቀም ነው፡፡” ብለን ከተነተነው ለውጤታማነት ሁሉም ሰዉ ዕድል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ተጫዋቾችን ጨዋታ ከማሸነፍ ይልቅ ውጤታማነት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ከቻልን ይህ በራሱ መጨረሻ ላይ አሸናፊ እንድንሆን ይረዳናል፡፡ ውጤታማነትን በሚከተለው ቀመር ልናሳካው ብንጥር ጥሩ ይሆናል፡፡
ውጤታማነት= ብቃት+ዝግጅት+ጥረት+ፍቃድ
ሁሉም ሰው ብቃት አለው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው እኩል ብቃት የለውም፡፡ ይህ ለአሰልጣኝም- ለተጫዋችም ይሰራል፡፡ ብዙውን ጊዜ ብቃት ከተፈጥሮ ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ ግን ውጤታማነትን አያረጋግጥም፡፡ ዋናው ነገር ብቃት መያዙ ሳይሆን የተያዘውን ብቃት ማሳደጉ እና መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ ብቃታችንን በከፍተኛ ሁኔታ መጠቀም የምንችለው በተገቢው መንገድ ስንዘጋጅ ነው ፡፡በማያቋርጥ እና ተከታታይ በሆነ ዝግጅት ብቻ ነው ተስጥኦ ወደ ብቃት ማደግ የሚችለው፡፡ ይህ ሒደት የዝግጅት ልምምድ ይባላል፡፡ በተገቢው ልምምድ ተጫዋቾች ፈጣን፣ ጠንካራ፣ ያላቸውን ክህሎት በአግባቡ የሚጠቀሙ፣ በዕውቀት የሚመሩ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እና በአስተሳሰብ የበሰሉ ይሆናሉ፡፡ ያደገ ብቃት የሚታየው በነጥብ ጨዋታዎች ወይም በውድድር ላይ በሚኖር ፈተና ነው፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚሆነው በአካል እና በአእምሮ የመጨረሻው ጥረት ሲደረግ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾች በመዛል ስሜት ውሰጥ ሆነው እንኳ ያላቸውን ሁሉ የሰጡ ሲመስላቸው ያኔ ተጨማሪ ሃይል እንዲያወጡ ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ያለንን ሁሉ ሰጠን ብለን ስናስብ ተጨማሪ እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ያስገድደናል፡፡ በብዙ ውድድሮች የመሸነፍ እና የማሸነፍ ዕጣ የሚወሰነው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ተጫዋቾች እነርሱ እንኳን “አለን!” ብለው የማያስቡትን እምቅ አቅም ከውስጥ አውጥተው ይጠቀማሉ፡፡ ፈቃድን መጠቀም ማለት ይኸው ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ በውስጣችን ወደ ተቀመጠ ሀይል በመሄድ እሱን አውጥቶ መጠቀም መሆኑ ነው፡፡
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ