ዳንኤል ፀሐዬ እና የታዳጊነት ትውስታዎቹ

በጉና ንግድ ክለብ ታሪክ ውስጥ በትልቅ ደረጃ ስማቸው ከሚጠቀሱት ተጫዋቾች አንዱ ነው። ለክለቡ ለአስራ ሁለት ዓመታት የተጫወተው ይህ ተጫዋች በዘጠናዎቹ መጀመርያ በትልቅ ደረጃ ዝናቸው ከናኙ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። በእግርኳስ ሕይወቱ በሦስት የዕድሜ እርከን ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች እና “እንደ እናት እና አባቴ አሳድጎኛል” ከሚለው ጉና በመቀጠል ለአዳማ ከተማ ተጫውቷል።

በአስራ ስድስት ዓመቱ በክለብ ደረጃ እግር ኳስ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እና እግር ኳስን በጋራ ያስኬደው ዳንኤል ፀሀዬ ተማሪ እያለ ያጋጠሙትን እግርኳሳዊ ትውስታዎች እንዲህ ይገልፃቸዋል።

” የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በመቐለ አፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። አክሱም በተደረገ የትግራይ የፕሮጀክት ውድድር ባሳየሁት ብቃት ጉና ንግድ እኔን ለማዘዋወር ጥያቄ አቀረቡ። ቤተሰቤም ትምህርት እና እግር ኳስ አብሮ ማስኬድ አለበት አሉ። እኔም በትምህርት ጎበዝ ከሚባሉት ውስጥ ነበርኩ። ሆኖም ዝውውሩ በጣም ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩት። ልጅም ስለነበርኩ በዛ ዕድሜ መቐለ ሄጄ እግርኳስ ለመጀመር ለኔ ከባድ ነበር። መጨረሻ ግን መቐለ የሚኖር የአባቴ ወንድም ነበር፤ በሱ አግባቢነት ጉና ንግድ ፈረምኩ፤ ወቅቱም 1986 ነበር። የዛኔ እኔ ገና በአካልም በዕድሜም ገና ነበርኩ። ከዛ መቐለ መጣሁና ቀጥታ ወደ ጉና ዋናው ቡድን ተቀላቅዬ በክለቡ ካምፕ እየኖርኩ አፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። ደብተር ፣ እስክርቢቶ እና ሌላ የሚያስፈልጉኝ ነገሮች ክለቤ እያሟላልኝ ነበር የምማረው።

” ጉና ንግድ እና ብሔራዊ ቡድን እየተጫወትኩ ለትምህርት ቤት ውድድር አልጫወትም ስል ብዙዎች ይናደዱብኝ ነበር። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እየተጫወትክ ወርደህ ለትምህርት ቤት ውድድር መሳተፍም ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም የጨዋታ መደራረብ አለ። እንደውም አንድ ቀን ቅዳሜ የትምህርት ቤት ጨዋታ አድርጌ እሁድ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያደረግኩበት ጊዜ ነበር።
እንደ አጋጣሚም ሁለቱም ላይ ሁለት-ሁለት ግብ ነበር ያስቆጠርኩት። በወቅቱ በጣም ጥሩ ብቃት የነበርኩበት ጊዜ ነበር፤ እንደውም ፕሪምየር ሊግ ከመግባታችን ከአንድ ዓመት በፊት የትግራይ ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ነበርኩ። እንደ ቡድንም በግሌም ጥሩ ነበርኩ። ገና ታዳጊ፣ በባህሪም በጣም ዝምተኛ እና ቁጥብ ነበርኩ፤ ለጨዋታ ከከተማ ስንወጣ ከትምህርት ቤቴ ፍቃድ ሳልወስድ ወጥቼ አላውቅም። እስከዚህ ደረጃ ነበር ለትምህርት የነበረኝ ፍቅር። ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ ክለብ እየተጫወትኩ ክፍል ከክፍል ለሚደረጉት ጨዋታ ራሱ ካልተጫወትክ እያሉ ይጨቀጭቁኝ ነበር፤ እንደውም አንድ ቀን ቀጣይ ሳምንት ከባድ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አለብኝ አልጫወትም ብዬ ከክፍል አባርረውኛል።

” ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን የተጫወትኩትም ተማሪ እያለሁ ነበር። ከስዊድን ጋር ያደረግነው ጨዋታም በቀጥታ በቴሌቭዥን ተላልፎ ስለነበርና እኔም ግብ ያስቆጠርኩበት ጨዋታ ስለነበር በተለይም ትምህርት ቤት ዝናዬ ናኝቶ ነበር። ከስዊድን ጋር ያደረግነው ጨዋታ በጣም አሪፍ ነበር። ከጨዋታው በፊት ግን አንድ ያጋጠመኝ የማልረሳው አጋጣሚ አለ። ከጨዋታው ከሰዓታት በፊት የመጫወቻ ጫማዬ በሆነ ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆነ። የጫማ ቁጥሬም በጣም ትንሽ ነበር፤ ከዛ በፌደሬሽን እና ከተማው የሚበቃኝ ጫማ አጥተው ብዙ ተንከራተትን። ይሄ እየሆነ ያለው ከጨዋታው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ነበር። በመጨረሻው ግን የጉና ስራ አስከያጅ አቶ ኃይሉ በግላቸው ፈላልገው መጫወቻ ጫማ ይዘውልኝ መጡ። አዲሱን ጫማ አድርጌ ወደ ጨዋታው ገባሁ። ጨዋታው ፈታኝ ነበር፤ ስዊድኖች በሁሉም ረገድ ጠንካራ ነበሩ። ታክቲካሊ በተለይ መከላከል ላይ በጣም አስገራሚ ቡድን ነበሩ። እነ ፍሬዲ ሊዩምበርግ ፣ የርገን ፔተርሰን እና አንድርያስ ስቬንሰን የመሳሰሉ ተጫዋቾች የነበሩበት ቡድን ነበር። ቆይቶም ሩማንያ ባዘጋጀችው የአውሮፓ የታዳጊዎች ዋንጫ በጥሩ ደረጃ ነው የጨረሱት። ከኢትዮጵያ ጨዋታ በኃላም አሰልጣኙ ተጫዋቾቹ በትላልቅ የአውሮፓ ቡድኖች እየታደኑ እንደሆነ ገልፆ ነበር። ከኛ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በጣም አሪፍ ነበሩ። በመጀመርያው ጨዋታ ልክ እንደተጀመረ ነበር ጎል ያስቆጠርኩት። በሁለተኛው ጨዋታም ጎል አስቆጥሬያለው። በመጀመርያው ጨዋታዬ ያውም በሁለት ትላልቅ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ተከታታይ ጎሎች ማስቆጠር ለኔ ትልቅ ነገር ነበር።

“ከብሔራዊ ቡድን ተመልሼ ብዙም ሳልቆይ ለትምህርት ቤት ጨዋታዎች አድርጌያለው። የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ስለነበርኩም ብዙ ትኩረት ይሰጠኝ ነበር። እንደውም አንድ ቀን ስዊድንን ገጥመን ከተመለስኩ በኃላ ቡድናችን ለልምድ ልውውጥ ከደሴ አንድ ትምህርት ቤት ጨዋታ ነበረው፤ እኔ ግን ለመጫወት አላሰብኩም ነበር። ልብሴን ለብሼ ተቀያሪ ወንበር ላይ ነበርኩ። እስከ ዕረፍት ቡድኑ ሦስት ለባዶ እየተመራ ወጣ። ከዛ በኃላ በጉና ከኔ ጋር የሚጫወቱ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ነበሩ፤ ከነሱ ጋር ተቀይረን ገብተን 3-3 አለቀ። ግጥሚያው ከብሔራዊ ቡድን መልስ ስለነበር ጨዋታው ካለቀ በኃላ ከሜዳው መውጣት አልቻልኩም። ከደሴ የመጡ ተጫዋቾችም ከኛ ጋር የሚማሩ ተማሪዎችም ብዙ ሰዓት አሳልፈናል በሜዳ ውስጥ።

” አንድ ቀን ደግሞ ከኤርትራ ቡድኖች ጋር ለቅድመ ውድድር ጨዋታ አድርገን ነበር። በዛ ወቅት ደግሞ የኤርትራ ቡድኖች የትግራይ ክለቦችን አሳንሰው የሚያዩበት ጊዜ ነበር ፤ ለዝግጅት ሲመጡ ለኛ የነበራቸው ግምት እጅግ ዝቅተኛ ነበር። የነሱ እግር ኳስ ጥሩ ደረጃ ላይ የነበረበት ወቅት ነበር። እዚህ ሁለት ጨዋታ አድርገን አንድ አሸነፍን አንድ ጨዋታ ደግሞ አሸነፉን። ብዙም ሳይቆዬ ኤርትራ ሄደን እንድንጫወት ግብዣ አቀረቡልንና ሄድን። ቡድኑ “ምድላው ምግቢ” ይባላል። ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ደግሞ አልታህሪር ይባላል። እዛ ስንሄድ ግን በብዙ ነገር ተሻሽለን ሄድን እነሱም እንደዛ አልጠበቁንም ፍፁም ብልጫ ወስደን ነበር የተጫወትነው፤ በመጨረሻው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት አገቡብን እንጂ። እኔ በግልም እዚህ ኢትዮጵያ በነበሩት ጨዋታዎች በሁለቱም ግብ አገባሁባቸው፤ ኤርትራ ባደረግነው ጨዋታም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጌ እንደውም የግብ እድሎችም አባክኛለው። በዛን ሰዓት የኤርትራ እግር ኳስ ልዩ የሆነ የጋዜጣ ፣ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ሽፋን ይሰጠው ነበር። ጨዋታው ካለቀ በኃላም ለአሰልጣኛችን ዳንኤል ኤርትራዊ ነው ፤ ይህን የመሰለ ጥሩ ተጫዋች በኢትዮጵያ ያውም በትግራይ ሊኖር አይችልም አሉት። በኔ ብቻ ሳይሆን በክንደያ ታመነ፣ የማነ እና ቴዎድሮስ ነበር የተገረሙት። ቅድም እንዳልኩህ ለኛ እግርኳስ የነበራቸው ግምት በጣም ዝቅተኛ ነበር። ከዛ አብርሀም ተክለሀይማኖት የኛው ልጅ ነው ያውም ገና የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ነው አላቸው። እዛ ሄደን ያደረግነው እንቅስቃሴ ለእግር ኳሳችን የነበራቸውን የተዛብ አመለካከት ያስተካከልንበት ነበር። በግሌም በ1990 ከኤርትራ ክለቦች የዝውውር ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር፤ ሆኖም እኔ አልተቀበልኩትም። ”

*በቀጣይ ሳምንት በዘጠናዎቹ ክዋክብት ዓምዳችን የዳንኤል ፀሀዬ የእግር ኳስ ሂወት በሰፊው ይዘንላቹ እንደምንቀርብ ከወዲሁ ለመግለፅ እንወዳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ