ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር – ክፍል አራት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


በ1960ዎቹ የካቴናቺዮ አጨዋወት ሥልትን በዋነኝነት ያቀነቅን እና በተግባር ያውል የነበረው ቡድን ኢንተር ሊሆን ቢችልም ለተቀረው የአውሮፓ ክፍል “ሲስተሙ” ምን ያህል ተጽዕኖ አሳዳሪ ታክቲክ እንደሆነ ያሳየው የሚላን ከተማ ክፋይ የሆነውና ቀዩን ክፍል የሚወክለው ክለብ ኤሲ.ሚላን ነው፡፡ ምስጋና ለባለ ምጡቅ አዕምሮው አሰልጣኝ ሮኮ ይግባና ሚላኖች የካቴናቺዮ አጨዋወት ዘዴን በማስተዋወቁ ረገድ ፈር-ቀዳጅነቱን ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ ቅንብብ ባለ የፊቱ አቀማመጥ፣ በወፍራምና ቅርጸ-ቢስ ቁመናው እንዲሁም በአጫጭር እግሮቹ የተነሳ የሮኮን መላ አካላዊ ይዘት ያስተዋለ ሰው የሆነ አስቂኝ ምስል ይከሰትበታል፡፡ ይሁን እንጂ የአሰልጣኙ ገራገር መልክ ወይም ድንቡሽቡሽ ገጽታው ተጫዋቾቹ ላይ ፍጹም የበላይነት እንዲኖረው ከማድረግ አላገደውም፡፡ ሮኮ ከልምምድ ሜዳ ውጪም ቢሆን ተጫዋቾቹን በጥብቅ ክትትል ለመቆጣጠር ወደኋላ የማይል ነበር፡፡ የተጫዋቾቹ የግል አኗኗር ዘይቤ በእግርኳስ ህይወታቸው ላይ የተለየ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ይጥራል፡፡ በጣም ጥንቁቅ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ተጫዋቾቹ የእርሱ የትኩረት ኢላማ እንዳይሆኑ አስገራሚ ነገሮች አድርገዋል፡፡ ሮኮ በ1960ዎቹ አጋማሽ በቶሪኖ ሳለ የክለቡ አጥቂ ጂጂ ሜሮኒ የሴት ጓደኛውን እህቱ እንደሆነች በማስመሰል የሮኮን ውልፍት የማያስብል ቁጥጥር ለማለፍ ችሏል፡፡ ሮኮ ደስተኛ፣ ፍልቅልቅ፣ ግርማ ሞገሳም፣ ደስ የሚል ስሜት የሚነበብበት፣ በቶሎ የሚናደድና ቁጡ ባህርያት ተላብሷል፡፡ ከፍተኛ የመጠጥ ሱስ ያለበት በመሆኑ አዘወትሮ የሚጠጣበትን ሬስቶራንት እንደ ቢሮ እስከመጠቀም ደርሷል፡፡ ሰውየው በቀላሉ ተገማች ያልሆነ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በንዴት ስሜት ውስጥ ሆኖ በመልበሻ ክፍል ወለል ላይ ፊትለፊቱ ተቀምጦ ያገኘውን ሻንጣ በእግሩ ይነርተዋል፤ እርሱ ትርፍ መለያዎች የተጠቀጠቁበት ቦርሳ መስሎት ኖሯል፡፡ ነገርግን ቦርሳው የያዘው የልምምድ መስሪያ መሳሪያዎችን ነበር፡፡ በክፍሉ የሃዘን ድባብ ውጧቸው የነበሩ ተጫዋቾች ለመሳቅ ሮኮ የማይሰማቸው ርቀት ድረስ መሄዱን ማረጋገጥ ነበረባቸው፡፡ ኔሪዮ ሮኮ ይህን ያህል የሚፈራ አሰልጣኝ ነበር፡፡

በቶሪኖ ሮኮ አዘወትሮ የሚከውነው አንድ ልማድ ነበረው፡፡ ሁሌም የክለቡ የልምምድ ማዕከል አካባቢ ወዳለችው አንዲት መጠጥ ቤት ጎራ ይላል፤ ሁለት ጠርሙስ መጠጥ ይቀማምሳል፤ ከዚያም ጠርሙሶቹን ወደመልበሻ ክፍሉ አምጥቶ በልብስ መስቀያ ሳጥኑ አናት ላይ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ሮኮ የእግርኳስ ጨዋታ በየትኛው መንገድ መካሄድ እንዳለበት የያዘውን ሐሳብ የሚጋራው ብሬራ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ሆኖ እስከ እኩለ ለሊት፥ አንዳንዴም ከዚያ እስኪያልፍ ድረስ ወይን በላይ በላዩ እየተጎነጩ ከሚያሳልፈው ቆይታ በላይ የሚያስደስተው ጊዜ ያለ አይመስልም፡፡ ጂያኒ ብሬራ አንዴ በጻፈው ጽሁፍ ” አንድ የምሉዕነት ይዘት ያለው ጨዋታ 0-0 ይጠናቀቃል፡፡” ብሏል፡፡ ሮኮ ይህን ያህል ርቆ ባይሄድም በመሐለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ወደጎንዮሽ በሚደረጉ እርባና ቢስ ቅብብሎች ሳቢያ የሚመክኑ ኳሶች ቆሽቱን ያሳርሩታል፡፡ ይህ ከሚሆን ይልቅ ተጫዋቾቹ – አጥቂዎችም ቢሆኑ – ወደኋላ ተመልሰው ቢቀባበሉ ይመርጣል፡፡ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሮኮን በአግባቡ ተረድተውት አያውቁም፥ በእርግጥ የእርሱ ሐሳብም በቀላሉ ይሁንታን የሚያገኝ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፦ ብራዚላዊው አጥቂ ጆዜ አልታፊኒ (ተጫዋቹ በብራዚል ሳለ በመጀመሪያዎቹ የእግርኳስ ተጫዋችነት ዓመታቱ “ማዞላ” ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡) በሚላን የተሳካ የሚባል ቆይታ የነበረው ቢሆንም ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ለመልመድ ተቸግሯል፡፡ ጂሚ ግሪቭስም ህይወት በጣልያን የከበደችው እንዲሁ ከሮኮ የአጨዋወት ሥልት ጋር ለመጣጣም ባለመቻሉ ይመስላል፡፡ በ1961-62 የውድድር ዘመን ግሪቭስ በሴሪአው ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት ባደረጋቸው አስር ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠሩን ሰዎች ዘንግተውታል፡፡ ይህ ግን ለሮኮ በቂ አልነበረም፡፡ ” እነዚያ ሁለቱ ተጫዋቾች (ጆዜ አልታፊኒ እና ጂሚ ግሪቭስን ማለቱ ነው፡፡) በእግርኳስ ጥሩ ክፍያ ማግኘት ብቻ ሳይሆን መጎሻሸምም ያለ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡” በማለት ስለ “ቅንጦት” ተጫዋቾቹ ያለውን አስተያየት ይሰጣል፡፡

ኔሪዮ ሮኮ በአስራ ዘጠኝ ሃምሳዎቹ በትሬቪዞ የአጭር ጊዜ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ትሪየስቲና ተመለሰ፡፡ ከዚያም በ1953 ፓዶቫ የተባለውን ክለብ ተረክቦ ማሰልጠን ከጀመረ በኋላ የእርሱ አጨዋወት ሥልት ተቀባይነቱ ይበልጡን እየጨመረ ሄደ፡፡ በወቅቱ ፓዶቫዎች ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በ1956-57 እና 1959-60 የውድድር ዘመናት መካከል በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛ፣ ሰባተኛ፣ አምስተኛ እና ስድስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ቻሉ፡፡ ይህም በክለቡ ታሪክ የተሻለው ተከታታይ ጥሩ ውጤት ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ያን ጊዜ ለሮኮ ትልቅ ዕድል ከተፍ አለለት፡፡ በ1959 ከክለቡ ጋር ስኩዴቶውን ያሸነፈው አሰልጣኝ ቪያኒ በልብ ድካም ሳቢያ ሥራውን መቀጠል ባለመቻሉ ሮኮ ኤሲ-ሚላንን እንዲያሰልጥን ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ቪያኒ በሚላን የ<ስፖርቲንግ ዳይሬክተር>ነቱን ይዞ ሲሰራ የ”ጠራጊ ተከላካይ (Sweeper)” አስፈላጊነትን በአያሌው በመወትወት ለሮኮ እንዳሳመነው ይናገራል፡፡ በእርግጥ ሁለቱ አሰልጣኞች በዚህ የአጨዋወት ሥልት ዙሪያ በጥልቀትና በዝርዝር ውይይት አካሂደውበት ሊሆን ቢችልም ሮኮ ግን ያለምንም ጥርጥር ካቴናቺዮ-መሳይ የጨዋታ ዘዴን ቀደም ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ትሪየስቲናን ማሰልጠን እንደጀመረ መተግበሩ ሁሉም የሚያውቀው ነው።

ለነገሩ ሮኮ የሚጠቀመው የካቴናቺዮ አጨዋወት አይነት በአሉታዊ ገጽታ የሚታይ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፦ ሚላን በ1961-62 የውድድር ዘመን  ስኩዴቶን ሲያሸንፍ በሰላሳ አራት ጨዋታዎች ሰማንያ ሦስት ግቦች አስቆጥሮ ነበር፡፡ ይህ አሐዝ በጊዜው እጅግ በጣም ውጤታማ የነበረው ሮማ ካገባቸው ጎሎች በሃያ ሁለት ከፍ ያለ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በትሪዬስቴ ከተማ ተወልዶ የተጫዋችነት ዘመኑን በትሪየስቲና ቡድን ውስጥ  ሀ-ብሎ የጀመረው ሴዛሬ ማልዲኒ በጊዜው ቆራጥ ተከላካይ የነበረ ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ የጠራጊ-ተከላካይ (Sweeper) መገለጫ የመሆን ምናብ የመፍጠር አቅም አልነበረውም፡፡ ይልቁንም ለአስራ ሁለት ዓመታት የተጫወተበትን ቶሪኖ  በ1966 ሲለቅ በክለቡ ይፋዊ የታሪክ ማህደር ላይ ” የብቁ እግርኳስ ተጫዋቾች ተምሳሌት፣ ሙያው ላይ ብቻ የሚያተኩር ግለሰብ፣ እግርኳስ በዘይቤ እንዲቃኝ የሚሻ የጨዋታ ሒደት ተቆርቋሪ፣ ዘወትር የመከላከል ሚናውን ሳይዘናጋ የሚፋለም ብርቱ!” በሚል የሰፈረው ጽሁፍ ተጫዋቹን ይበልጥ የሚገልጸው ሆነ፡፡

ሮኮ በቡድኑ ውስጥ የሰፈነውን የፈጠራ ችግር እንደ ጂያኒ ሪቬራ ባሉ ተጫዋቾች ለማካካስ ጥሯል፡፡ ሪቻርድ ዊሊያምስ <ዘ-ፐርፌክት 10> ላይ እንዲያውም ይህን የኒሪዮ ሮኮ የፈጣሪ ተጫዋች ፍለጋ ከታዋቂው የአልበርት ካሙዝ የኅልውነት ፍልስፍና (Existensialism) መገለጫ ምሳሌ ጋር ያነጻጽረዋል፡፡ ምሳሌው አንድ ሰው በህይወቱ ምንም ለውጥ ለማያመጣ ነገር በከንቱ መባዘኑን እና ሰውየው ግን ተስፋ ሳይቆርጥ እንደማይሳካ እያወቀም በተደጋጋሚ ለለውጥ ሲታትር ያሳየናል-የሮኮ ጥረትም እንዲሁ ፍሬ-ቢስ ሲሆን እናያለን፡፡ ብሬራ የሪቬራን ነገር በተመለከተ የማይስማማበት አቋም ነበረው፥ ጉዳዩን ተጫዋቹ ከሮኮ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በማመን “ስታሊንግራድ” በማለት ይጠራዋል፡፡ የመከላከል እግርኳስ አቀንቃኝ (Defensivist Football) ብሎ ለመሰየም የአክራሪነት ባህርይ ያለው ብሬራ ሪቬራን “የቅንጦት ተጫዋች” ይለዋል፡፡ እንዲያውም “l’abatino” ወይም “መናኙ” በማለት ተጫዋቹ ሃሞተ-ቢስ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ በሮኮ ቡድን ውስጥ ሪቬራ ያለው ጠቀሜታ በሁለቱ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ላይ ሚላን ባሳካቸው ድሎች ሊታይ ችሏል፡፡ በ1963ቱ የፍጻሜ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ለአጥቂው አልታፊኒ ሁለት የግብ ዕድሎችን በማመቻቸት ሚላን ከመመራት ተነስቶ ዋንጫውን እንዲያሸንፍ አድርጓል፡፡ በ1969ኙ ፍጻሜም እንዲሁ ሚላን አያክስን 4-1 በረታበት ምሽት ሁለት የጎል ኳሶችን ማቀበሉ አይዘነጋም፡፡

የኔሪዮ ሮኮ የካቴናቺዮ አጨዋወት ሥልት ጥቂቶች እንዳሰቡት እጅጉን መከላከል ላይ ያመዘነ አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በቤላ ጉትማን ይሰለጥን ከነበረው የቤኔፊካ ቡድን ጋር የተለያየ የጨዋታ ዘይቤ አሳይቷል፡፡ በሁለቱም ቡድኖች የሚገኙ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ በሚኖራቸው ደካማ የቦታ አጠባበቅ ረገድ ተመሳስሎ ቢኖራቸውም ጉትማን ውበት ላለው እግርኳስ ቅድሚያ የሚሰጥ፥ ሮኮ ደግሞ ከምንም በላይ ለማሸነፍ መፈለጉ ይለያያቸዋል፡፡ ሚላን በ1969 የኢንተርኮንቲኔንታል ዋንጫ ከአስቸጋሪው የአርጀንቲና ቡድን ኢስቱዲያንቴስ ዴ-ላ- ፕላታ ጋር ከመፋለሙ ቀደም ብሎ ሮኮ ለቡድኑ ተጫዋቾች የመጨረሻ መልዕክት ማስተላለፍ ነበረበት፡፡ “ሜዳ ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ነገር ምቱ! ይህ የምትመቱት ነገር ኳስ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡” ንግርቱ ምናልባት አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፤ ነገርግን ይህ አይነቱ ባህርይ ለሮኮ ያልተለመደ አልነበረም ለማለት ያዳግታል።

በ1962-63ቱ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ሁለተኛው ዙር ኢፕስዊች ታውን በሚላን ሲሸነፍ የእንግሊዙ ክለብ አምበል አንዲ ኔልሰን የሮኮ ቡድን ብቃት ላይ ጥርጣሬ እንደነበረው ቅሬታውን ገልጿል፡፡ ” ጸጉርህን ይጎትታሉ፤ ይተፉብሃል፤ ጣቶችህን ይረግጣሉ፡፡” ሲልም አማሯል፡፡ በውድድሩ በርካታ ጎሎችን ሲያስቆጥር የሰነበተው የመስመር አማካዩ ፓውሎ ባሪሰን በፍጻሜው ሳይሰለፍ ቀረ፡፡ ይህን ለማካካስ ብሩኖ ሞራ ከቀኝ መስመር ተነስቶ በግራው መስመር ላይ እንዲጫወት ተደረገ፤ ጂኖ ፒቫቴሊ ደግሞ በሞራ ቦታ ተተክቶ የቤነፊካውን ጨራሽና ግዙፍ የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside-Forward) ማሪዮ ኮሉናን እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠር ከባድ ኃላፊነት ተጣለበት፡፡ ይህ እንግዲህ ምናልባት መጥፎ እድል ወይም ጊዜውን ያልጠበቀ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፤ አልታፊኒ ሚላንን አቻ የምታደርግ ግብ ካስቆጠረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ገደ-ቢሱ ኮሉና በፒቫቴሊ ተገጭቶ እያነከሰ ሜዳውን ለቆ ለመውጣት ሲገደድ ማንም አልተገረመም ነበር፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡