“የዘመኑ ከዋክብት ገጽ” ከሐይደር ሸረፋ ጋር…

ባለፈው ዓመት መቐለ የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ሲሆን ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረውና ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የቆየው ሐይደር ሸረፋ የዛሬው የዘመኑ ከዋክብት እንግዳችን ነው።

ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ከታዩ ምርጥ አማካዮች አንዱ ነው። ትውልድ እና እድገቱ በመዲናችን አዲስ አበባ የሆነው እና የእግር ኳስ ሕይወቱን ቢኒ ትሬዲንግ በተባለ የታዳጊዎች ፕሮጀክት የጀመረው ይህ አማካይ በ2006 ወደ ደደቢት ሁለተኛው ቡድን ካደገ በኃላ ፈጣን እድገት በማሳየት በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል። እስከ 2008 አጋማሽ ድረስ በአሳዳጊ ቡድኑ ደደቢት ቆይታ የነበረው ሐይደር በተጠቀሰው ዓመት አጋማሽ ወደ ሌላኛው የፕሪምየር ሊግ ተወዳዳሪ ሀዲያ ሆሳዕና በውሰት አምርቶ በክለቡ የስድስት ወራት ቆይታ ካደረገ በኃላ በጅማ አባቡና የሁለት ዓመታት ቆይታ አድርጓል። ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ መቐለ 70 እንደርታ አምርቶ ክለቡ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ካስቻሉ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ይህ ተጫዋች በተሰረዘው የውድድር ዓመት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሳልፏል።

ከሀይደር ሸረፋ ያደረግነው አዝናኝ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ጊዜውን የሚያሳልፈው… 

በወረሽኙ ምክንያት አብዛኛው ጊዜዬን ቤቴ ነው የማሳልፈው። አስገዳኝ ሁኔታ ከሌለኝ ከቤት አልወጣምም።

እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን..

ነጋዴ ነበር የምሆነው። አከባቢዬ ወደ መርካቶ መሳለምያ አከባቢ ስለሆነ ወደ ንግዱ ዓለም እገባ ነበር።

ከኳስ ውጭ የሚያዝናናው

ጊዜዬን ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ነው የሚያዝናናኝ። አልፎ አልፎ ደግሞ ከጓደኞቼ ጋር ወጣ ብዬ ሻይ ቡና ማለት ያስደስተኛል።

ከማን ጋር ቢጣመር ይመርጣል

ከሽመልስ በቀለ ጋር ብጣመር ደስ ይለኛል። ከጎኑ ስትጫወት ምቹ ነው፤ ብዙ ነገር ያቅልልሀል።
በጠባብ ቦታ ውስጥ መጫወት ይችላል፤ ብዙ ኳሊቲዎች ያሉት ጥሩ ተጫዋች ነው።

በተቃራኒ ሲገጥመው የሚያስቸግረው ተጫዋች

ታፈሰ ሰለሞን በተቃራኒ ስገጥመው ያስቸግረኛል።
እይታው ጎበዝ ነው፤ ኳስ ከመቀበሉ በፊት ዙርያውን በደንብ ቃኝቶ ነው የሚጫወተው ፤ ተጫዋች እንደ ቀልድ ነው የሚያልፈው ፤ ከጎኑ ያሉትን ተጫዋቾች በደንብ ነው የሚያደራጀው። በነዚህ ምክንያቶች እነሱን በተቃራኒ መግጠም ከባድ ነው።

የማይረሳው ጎል

በ2009 ጅማ አባ ቡና እያለው ከወላይታ ድቻ ጋር ስንጫወት ያገባኃት ጎል አልረሳትም። ከሳጥን ውጭ አክርሬ ያስቆጠርቋት የመጨረሻ ደቂቃ ማራኪ ግብ ነበረች።

የማይረሳው ለግብ ያመቻቸው ኳስ

ብዙ ኳሶች ለግብ አመቻችቼ አቀብያለው። ከሁሉም አስበልጬ የምወዳት ግን ዘንድሮ ከድሬዳዋ ጋር ስንጫወት ለጌታነህ ከበደ አመቻችቼ ያቀበልኩት ኳስ ነው።

መጫወት የሚፈልገው ቦታ

መጫወት የምፈልገው ቦታ በተለምዶ ስምንት ቁጥር ተብሎ የሚታወቀው የአማካይ ቦታ ላይ ነው።

የልጅነት ጀግናው

ከውጭ አንድርያ ፒርሎን እያደነቅኩ ነው ያደግኩት። ከሀገር ውስጥ ግን በጣም ብዙ ናቸው።

በእግርኳስ የቅርብ ጓደኛው

በእግርኳስ የቅርብ ጋደኛዬ ሄኖክ ካሣሁን ነው።

ከጨዋታ በፊት የሚያደርገው የተለየ ልምድ

የተለየ ልምድ የለኝም። ከጨዋታ በፊት እፀልያለው፤ ሌላ ግዜም እፀልያለው።

ብዙ ገንዘብ ወጪ የሚያደርግበት ነገር

ብዙ ወጪ የማደርግበት ለታኬታ ጫማ እና ለተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) ነው ።

የማይረሳቸው ጊዜያት

በጥሩ የማስታውሰው ባለፈው ዓመት ከመቐለ ጋር ያነሳሁት ጣፋጭ ድል እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አይቮሪኮስትን ያሸነፈችበት ጨዋታ ነው። በመጥፎ የማስታውሰው ደግሞ ጅማ አባ ቡና ከፕሪምየር ሊጉ የወረደበት ቀን ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ