ከቀናት በፊት የዋና እና የረዳት አሰልጣኛቸውን ውል ያራዘሙት ብርቱካናማዎቹ የሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቻቸውን ውል አራዝመዋል።
በቅርቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበረውን የቀድሞው የሴት ቡድን አሰልጣኝ ፍሰሀ ጡመልሳንን በዋና አሰልጣኝነት ለአንድ አመት በመሾም እንዲሁም ረዳት አሰልጣኝ የነበረውን ዳዊት ተዋበን ውል በማራዘም ለቀጣዩ አመት እንቅስቃሴውን ከወዲሁ የጀመረው ድሬዳዋ ከተማ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች በማዞር ውሎችን ማራዘም ጀምሯል። ውላቸው በሰኔ ወር ከሚጠናቀቅ ከ15 በላይ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ ሁለቱ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ እና የተከላካይ አማካዩ ፍሬድ ሙሸንዲ ይገኙበታም። ይህንን ተከትሎ ክለቡ ሁለቱን ተጫዋቾች ለተጨማሪ አንድ አመት በክለቡ ለማቆየት ቅድመ ስምምነት በመፈፀም ፊርማቸውን እንዲያኖሩ አድርጓል፡፡ ፌድሬሽኑም የዝውውር መስኮቱን በይፋ ሲከፍት እንደሚያፀድቅላቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ጋናዊው የቀድሞው የስውዲኑ ክለብ ኤፍኬ ጉተንበርግ አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ የዛምቢያውን ቢውልድ ኮንን ከተቀላቀለ በኋላ ነበር በ2010 ጥር ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ መቶ ወልዋሎን የተቀላቀለው። ተጫዋቹም በክለቡ የአንድ አመት ከስድስት ወራት ቆይታን ካደረገ በኃላ በያዝነው አመት ወደ ድሬዳዋ ከተማ በማምራት በግሉ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን ለተጨማሪ አመት ቆይታን ለማድረግ ለክለቡ ፈርሟል፡፡ ሌላኛው ውሉን ለማራዘም ፊርማውን በማኖር የተስማማው ዲሞክራቲክ ኮንጎዊው የተከላካይ አማካይ ፍሬድ ሙሸንዲ ነው፡፡ ረዥሙ አማካይ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኃላ ሁለት አመታትን በድሬዳዋ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን ለተጨማሪ አመት በመቆየት በቀጣዩ አመት ዳግም በብርቱካናማዎቹ መለያ የምንመለከተው ይሆናል፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሶስት ወሳኝ ተጫዋቾችን በፊት መስመር እና በአማካይ ክፍሉ ላይ ለማስፈረም ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ድሬዳዋ በያዝነው የጥር ወር የዝውውር መስኮት አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ