ሶከር ታክቲክ | የተቃራኒ ቡድን መስመርን ማቋረጥ

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡

ታክቲካዊ ትንተና፦ በታይ ሌቪንሶኽን

ትርጉም- ደስታ ታደሰ

አንድ ቡድን በየጨዋታዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የመውሰድ ሒደቱን እያሳደገ ሲሄድ የኳስ ቅብብልን ያለ ግልፅ ዓላማ መከወን የለበትም፡፡

በዘመናችን የ “tiki-taka” አጨዋወት ዝና መናኘት  ብዙዎች ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ማሳካት እና ከጨዋታዎች በሚወሰዱ ዳታዎች የተሻሉ አሃዛዊ መሻሻሎችን ማሳየት “የትልቅ ቡድን” መመዘኛ አድርገው እንዲያስቡ ገፋፍቷቸዋል፡፡ ይህ ግን በአብዛኛው ልክ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የኳስ ቅብብሎች በዓላማ ካልተደረጉ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ መልፋቱ ጥቅም የለውም ፡፡ የ”tiki-taka” ሥልት እንዲገን ያስቻለው ፔፕ ጓርዲዮላ እንኳ  “ቲኪ-ታካ” እርባና ቢስ የቅብብሎች ሒደትን ስለሚያበረታታ በቃሉ አውድ ላይ ቅሬታ እናዳለው በአደባባይ ሲናገር ተደምጧል፡፡

በዚህ የታክቲክ ትንተና በኳስ ቁጥጥር ሒደት የተሻለ እድገት ለማስገኘት የሚረዳውንና የተጋጣሚ ቡድን መስመርን እንዴት ማቋራጥ እንደምንችል የሚያሳየውን ታክቲካዊ አቀራረብ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡    

በሜዳ ላይ የሚገኙ ታክቲካዊ መስመሮች ምንድን ናቸው?

ጭራሹኑ እግርኳስ ለማይመለከቱ ሰዎች “መስመር” የሚለው ሃሳብ ረቂቅ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ መስመር በእግርኳስ ታክቲክ አልያም በሜዴ ላይ የሚኖረውን ትርጓሜ በቀላሉ ለማስቀመጥ ያህል- መስመሮች ተጫዋቾችን በአግድሞሽ የሚያገናኙ ሃሳባዊ ርቀቶች ናቸው ፡፡ከታች በቀረበው ምሳሌ ወጡ (Classic) 4-4-2 ፎርሜሽን በቀላሉ ሶስት መስመሮች በምን መልኩ እንደሚፈጥር እናያለን፡፡

ስለዚህም “መስመር ማቋረጥ” ማለት በሁለት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች መካከል በሚፈጠረው ክፍተት ኳስን ማሳለፍ ማለት ይሆናል፡፡ ከታች በቀረበው ምሳሌ እንደተመለከተው በሰማያዊ ቀለም በተቀለመው መስመር ተጫዋች ‹A› በተጋጣሚ ቡድን መስመር መሃል ለተጫዋች ‹B› ያቀብለዋል፡፡

የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጥግግት

በዚህ ትንተና ላይ ሁለት የጥግግት ዓይነቶች እናነሳለን፡፡ በተጫዋቾች መካከል በሜዳው ቁመት የሚኖር ጥግግትና በሜዳው ስፋት የሚኖር ጥግግት፡፡ በሜዳው ስፋት በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠር እንቅስቃሴያዊ ጥግግት (Horizontal Compactness) የሚባለው በተመሳሳይ መስመር ላይ ባሉ ተጫዋቾች መካከል ያለው ክፍተት ሲሆን በሜዳው ቁመት የሚኖረው ጥግግት ደግሞ በመስመሮች መካከል የሚፈጠረው ጥግግት ነው፡፡ ከታች በተመለከተው ምስል የአግድሞሽ ጥግግቱን (በጥቁር ነጠብጣቦች) እና የሜዳው ቁመት ጥግግትን ደግሞ(በነጭ ነጠብጣቦች) እናያለን፡፡

የተጋጣሚ ቡድን በሜዳው ስፋት በጣም የተጠጋጋ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ አደራደር ከያዘ ይህን መስመር በመሃል ለማቋረጥ አዳጋች ይሆናል፡፡ በሜዳ ቁመት የሚስተዋለው ጥግግት ደግሞ በመስመሮች መካከል ሊኖር የሚችል ክፍተት ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ ተጋጣሚ ቡድን በዚህኛው የጥግግት ዘርፍ (Vertical Compactness) ጥቅጥቅ ብሎ የሚጫወት ከሆነ በመስመሮች መካከል ክፍተት ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሌላኛው በሜዳ ቁመት በተጫዋቾች መካከል የሚኖር ጥግግት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ጉዳይ ተቃራኒ ቡድን በሜዳው ስፋት ላይ የሚሰራው  የግድግዳ  መስመሮች ብዛት ነው፡፡አንድ ቡድን በሜዳው ቁመት የሚይዘው የስፋት መስመሮች መጠን በጨመረ ቁጥር በሜዳው በተጫዋቾች መካከል የሚገኘው ጥግግትም ከፍ ይላል፡፡ ከታች ባለው ምስል በ<4-ዳይመንድ-2>  ፎርሜሽን በሜዳ ላይ የቁመትና የስፋት ጥግግትን እንመለከታለን፡፡

ከላይ በምስሉ በሚታየው ቅርፅ የተጫዋቾች አደራደሩ በሜዳው ቁመትና አግድሞሽ በጣም የተጠጋጋ ሆኖ ይታያል፡፡ በመሃለኛው የሜዳ ክፍልም ተጨማሪ ተጫዋቾች ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በመከላከል አደረጃጀት በሜዳው ቁመት ብዙ የስፋት መስመሮች አሉ ማለት የቡድኑ አጠቃላይ መዋቅራዊ ቅርፁ ላይ የወርድ ጥበት ያስከትላል፡፡ ይህ የጎንዮሽ ችግር ወደ በቀጣዩ ንዑስ-ርዕሰ ጉዳይ እንድናመራ ያስገድደናል፡፡

ጥግግትን መለጠጥ (Undoing Compactness)

በመስመሮች መካከል የመጫወት ሒደትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በተጫዋቾች እንቅስቃሴ ጥግግትን ለመለጠጥ መሞከር እንችላልን፡፡ ከታች በቀረበው ምሳሌ የሰማያዊ ቡድን ተጫዋቾች የሆኑት A እና B በመሃላቸው ያለውን ርቀት አጥብበው ይታያሉ፡፡ በቀይ ቀለም የተወከሉት ተጫዋቾች C እና Dም የአግድሞሽ ጥግግታቸውን ጠብቀዋል፤ ሆኖም በተጋጣሚ ተጫዋቾች መሐል ለመጫወት የሚያስችላቸውን ክፍተት ለመጠቀም አልሞከሩም፡፡ ይህም በመስመሮች መሃከል በስኬታማ መንገድ እንዲጫወቱ የነበራቸውን ዕድል የበለጠ አጥቦታል፡፡

የተጋጣሚ ተጫዋቾችን የአግድሞሽ ጥግግት  ዘርዘር ያለ ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ የጎንዮሽ ስፋትን (Width) መጠቀም ይቻላል፡፡ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች በአግድም የሚደረደሩበትን መስመር በመለጠጥ በተጫዋቾቹ መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፡፡ ከታች በቀረበው ምሳሌ የሰማያዊ ቡድን ተጫዋቾች የሆኑት A እና B በሜዳው ስፋት ርቀት ጨምረው ቆመዋል፤ ይህም የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች C እና D የአግድሞሽ ጥግግታቸውን እንዲቀንሱ ያስገድዳቸዋል፤ ስለዚህም ለሰማያዊዎቹ ተጫዋቾች በተጋጣሚያቸው (በቀዮቹ) መሀል ለመጫወት ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡

የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት የሚኖራቸውን ጥግግት ለማስፋት የምንጠቀመው ታክቲካዊ መላም አለ፡፡ ይኸውም ጥልቀት (Depth) ነው፡፡ በቀጣዩ ምሳሌ የሠማያዊ ቡድን ተጫዋቾች የሆኑት <A> እና<B> በመሃከላቸው ያለውን በሜዳው ቁመት ያለ ርቀት አጥብበው ይታያሉ፡፡ ይህም የተቃራኒ ቡድን (ቀዮቹ) በሜዳው ቁመት በደንብ ተጠጋግተው እንዲገኙና በመስመሮቻቸው መካከል ያለውን ክፍተት እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ ጥብቁን ተጫዋችን-በ-ተጫዋች በመያዝ የመከላከል ሥርዓትን (Man-Marking) በሚጠቀም ቡድን የሚተገበር የቁመት ጥግግትን ለመለጠጥና ለማስፋት ተጫዋቾች ወደ ተጋጣሚ ክልል በጥልቀት እንዲገቡ ማድረግ (Drpth) ወሳኝ አማራጭ ነው፡፡ ጥብቁን ክትትል ለማክሸፍ የተጫዋቾቹ ዘላቂ እንቅስቃሴ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በጨዋታ ወቅት ተጫዋቾች በጥልቀት እንዲጫወቱ ፈቃድ የመስጠቱ ጉዳይ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ቦታቸውን እንዲለቁ ስለሚያደርግ በሜዳው ቁመት የሚኖር ጥግግትን የማፍረስና ክፍተት የማስገኘት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ሲባል ጥልቀትን መጠቀም በጣም ውጤታማ ያደርጋል፡፡

 ቀጣዩ ምስል ሰማያዊው ቡድን የተጋጣሚው ቡድን ተጫዋቾች በሜዳው ቁመት ያላቸውን ጥግግት ለመቀነስ ጥልቀትን ሲጠቀም ያሳያል፡፡በምስሉ ተጫዋች <B> በጥልቀት ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል በመጠጋት የተቃራኒ ቡድን ተጫዋችን ከቦታው ያወጣዋል፡፡ይህም በመስመሮች መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ