የሴቶች ገፅ | “እልኸኛ ነኝ፤ ሽንፈትን አልወድም” ወይንሸት ፀጋዬ

በዛሬው የሴቶች አምዳችን በእግር ኳሱ ስኬታማ የሆነችሁን የመሀል ተከላካይ ወይንሸት ፀጋዬን (ኦሎምቤ) ይዘን ቀርበናል፡፡

ስሟ ወይንሸት ፀጋዬ ይባል እንጂ ብዙዎች የሚጠሯት ኦሎምቤ በሚለው ቅፅል ስሟ ነው። ይህ መጠሪያ ደግሞ ከካሜሩናዊው የቀድሞ የዊጋን አትሌቲክ ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ማርሴይ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሶሎሞን ኦሎምቤ የተወሰደ ነው፡፡ ለወይንሸትም በሚሊኒየሙ መባቻ ለደቡብ ክልል ምርጥ ቡድን ስትጫወት አብረዋት ይጫወቱ የነበሩ የሀዋሳ ልጆች አጨዋወቷ እሱን ይመስል ስለነበር ኦሎምቤ የሚል ተቀፅላ ስምን አወጡላት። እሷ ግን በዚህ ስም ከመጠራት ይልቅ ወይንሸት የሚለው ምርጫዋ ቢሆንም የእግርኳሱ ቤተሰብ ግን በደንብ የሚያውቃት በዚሁ ቅፅል ስሟ ነው፡፡

የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቿ ትውልድ እና ዕድገቷ በአርባምንጭ ከተማ ሲሆን በሰፈር ከወንዶች ጋር እንዲሁም በትምህርት ቤት ከኳስ ጋር ተጫውታለች፡፡ የእግርኳስ ህይወቷን በዚህ መልኩ ሀ ብላ የጀመረችው እንስቷ በትውልድ አካባቢዋ የሚገኙ ተመልካቾች አቅሟን ስለሚያውቁ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደምትችል በተደጋጋሚ ይነግሯት ነበር፡፡ እሷም አካባቢዋ ለዚህ የታደለ ነዉና ገና በለጋ ዕድሜዋ በፕሮጀክት በመታቀፍ አልፎም በትምህርት ቤት ውድድሮች ተሳታፊ በመሆን ራሷን ማጎልበት ጀመረች፡፡ በፕሮጀክት ከምታሳየው አስደናቂ ብቃት አንፃር የጋሞ ጎፋ ዞንን ወክላ በክልሉ የውስጥ ውድድር በተደጋጋሚ ተሳታፊ መሆን የጀመረች ሲሆን በዞኑ ስታሳይ በነበረው እንቅስቃሴ ለደቡብ ምርጥም የመጫወት ዕድልን አግኝታለች፡፡ “ለደቡብ ምርጥ ተመርጬ ስጫወት የአለቤ ሾው ቡድን አሰልጣኝ ባቢ 1997 ላይ አይቶ ወሰደኝ። ሆኖም በቡድኑ ብዙም አልቆየውም የቡድኑ መስራች አለቤ ህይወቱ በማለፉ እና ቡድኑም በመፍረሱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራሁ።” በማለት የክለብ ህይወት ጅማሮዋ ምን እንደሚመስል በመግለፅ ትጀምራለች፡፡

ክለብ ውስጥ ታቅፎ መጫወት ህልም ይመስላት የነበረችው ኦሎምቤ ምኞቷ ፍሬ ቢያፈራም አልጋ በአልጋ ሊሆንላት ግን አልቻለም። በኢትዮጵያ ቡና ከ1998 እስከ 99 ጅማሮ ድረስ መልካም የሚባል ቆይታ ቢኖራትም የክፍለ ሀገር ልጅ በመሆኗ ይከፈላት የነበረው ወርሀዊ ክፍያ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ለማቆም ተገደደች። የአዲስ አበባ ኑሮም እየከበዳት በመምጣቱ ወደ ትውልድ ስፍራዋ ትተመለሰች። ” በፊት አለቤ ሾው ስጫወት ቤት ተከራይቶ ነበር የሚያኖረን። እሱ ከሞተ በኃላ ትኩረትም የሚሰጥ ስለሌለ ዝም ብዬ ኢትዮጵያ ቡና ትንሽ ቆይታ ካደረኩ በኃላ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አስቤ ነበር። ብዙ ነገሮችን ምቹ ስላልነበሩ ወደ አርባምንጭ ተመለስኩ” ስትል በወቅቱ የገጠማትን ችግር ታስታውሳለች።

አሁንም ኳስ ለመጫወት ተስፋ ያልቆረጥችው የመሀል ተከላካዩዋ ወደ አርባምንጭ ከተመለሰች በኃላ አዕምሮዋን ወደ ሌላ አቅጣጫ በፍፁም አልቀየረችም። በድጋሜ በሰፈር መጫወት ከቀጠለች በኃላ 2000 ላይ በሀዋሳ የደቡብ ክልልን ወክላ በአንድ ሀገርአቀፍ ውድድር ላይ በመሳተፍ ላይ እያለች በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና ሴቶች አሰልጣኝ የነበረው ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) አሁንም በድጋሜ ቡናማዎቹን እንድትቀላቀል በተማፅኖ ሲጠይቃት እሷም ያለማንገራገር ጥሪውን ተቀብላ ዳግም ወደ ክለብ ህይወት ለመመለስ በቃች። “አሰልጣኝ ፓውሎስ ‘ሳንቲሙንም እናስተካክላለን የቤት ኪራይም እንከፍላለን’ ብሎኝ ድጋሜ ወደ ቡና ሄድኩኝ። አጋጣሚ እሱ አዲስ አበባ ምርጥን ይዞ እኔ ደግሞ ለደቡብ ስጫወት ነበር ያየኝ። የክፍለ ሀገር ልጅ ስለሆንኩኝ በወር 350 ብር እየተከፈለኝ በድጋሜ ወደምወደው እግር ኳስ ተመለስኩ።” ስትል ፈታኙን ጊዜ አልፋ ዳግም ወደ ሊግ ውድድር መመለሷን ታወሳለች፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ስም ከነበራቸው ቡድኖች መሀል በነበረው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ የተሳኩ ዓመታትን አሳልፋለች። ከጥሎ ማለፍ እስከ አዲስ አበባ ዲቪዚዮን ድረስ ተደጋጋሚ ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር አንስታለች። አልሸነፍ ባይ እንደሆነች የሚነገርላት ወይንሸት ልዩ ፍቅር ባላት ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ቆይታን ካደረገች በኃላ ክለቡ በመፍረሱ 2003 ላይ ወደ ደደቢት አምርታለች። ኢትዮጵያ ቡና በመፍረሱ በወቅቱ ቁጭት የነበረባት ተከላካዩዋ ምንም እንኳን ብትከፋም በደደቢት ቤት ቀስ በቀስ የነበራት ጥሩ ቆይታ የእግር ኳስ ህይወቷን ሙሉ አደርጎላታል። በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ በደንብ ለመተዋወቅ ባስቻላት የሰማያዊዎቹ ቤትም ለስምንት ዓመታት በምርጥ አቋሟ በመዝለቅ አራት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን አሳክታለች። “ስለ ደደቢት ቆይታዬ ቃላት የለኝም። በክለቡ የነበሩኝን ጊዜያት የማልረሳቸው ናቸው። በክለቡ የነበሩ አመራሮች ፣ ተጫዋቾች እና ኃላፊዎች ለኛ ትልቅ ክብር ሰጥተውናል ፤ ማንም በማያደርገው መልኩ ዝቅ ብለው። ከዐወል ጀምሮ እሱ ከወጣ በኃላም እነዋልታ እና ሚካኤል ለሴት ልጅ በጣም ክብር አላቸው። የእነሱ እንደዚህ መሆን ትልቅ ተጫዋች እንድንሆን እና ጠንክረን እንድንሰራ አድርጎናል። ክለብ መጫወት የጀመርኩት በኢትዮጵያ ቡና ቢሆንም ከኢትዮጵያ ቡና ቀጥሎ ግን በደንብ ከብዙሀኑ ጋር የተዋወኩት በደደቢት ነው።” ስትል በደደቢት የነበራትን አስደሳች ጊዜያት ታስታውሳለች።

ረዘም ያሉ ዓመታትን በደደቢት መለያ ከመሀል ተከላካይነቷ ባለፈ በአምበልነትም ያገለገለችው ወይንሸት ፀጋዬ የቡድን ጓደኞቿን የምታነቃባቸው በስሜት የታጀቡ አገላለፆቿ እና አልሸነፍ ባይነቷ መገለጫዎቿ ሆነው ዛሬም ድረስ አልተለይዋትም።
ስለዚህ ባህሪዋ ስትናገርም “ለእኔ ጠቅሞኛል። በጣም እልኸኛ ነኝ ፤ ሽንፈትን አልወድም። ከሰፈር ጀምሮ በጣም እልኸኛ ነኝ። ያ ባህሪዬ ደግሞ ከእኔ ጋር አድጎ አሁንም ድረስ አለቀቀኝም ፤ ሁሌም ማሸነፍን ስለመድኩኝ። እኔ በባህሪዬ ቁጡ ነኝ። ከኳስ ውጪ ደግሞ ብታዩኝ መሬት ነኝ (ሳቅ ….)። በጣም የተለያየው ሰው ነኝ። በሜዳ ላይ እኔ ቀልድ አላውቅም። ሁሌም ጥሩ የምሆነው ለሙያዬ ክብር እና ፍቅር ስላለኝ እና ሁሉም ተጫዋች እንደኔ እንዲሆን ስለምፈልግ ነው። ያ ነገር እነሱ ላይ እንዲንፀባረቅ ስለምፈልግ እናገራለሁ እቆጣለሁ። ይህን ባህሪዬን ስለሚያውቁ ዝም እንኳን ካልኩኝ እንኳን ያኮርፉኛል። ‘እንዴት ኦሎምቤ ዝም ትላለች ? ካልተናገረች ውጤት አይኖርም’ ይላሉ (ሳቅ..)። እነሱ ባይሉኝም እንኳን እኔ ራሱ አልችልም። አመራሮች ፣ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞችም ይህን ያውቃሉ። ሁሉም ደስ ብሏቸው ነው የሚቀበሉኝ ፤ የሚናደድም የለም። በራሴ ቁጡ ነኝ ፤ ግን አስተካክላለሁ ትንሽ ደንገጥ የሚሉም ስለማይጠፉ። አጠቃላይ ባህሪዬ ይሄ ነው። ከምንም በላይ ብዙ ዋንጫን አግኝቻለው ፤ ግን አሁንም አልጠግብም። አዳማ ገብቼም ይሄ ባህሪዬ አለ። ይሄን ደግሞ እኔ እወደዋለው። ሙያዬን አክብሬ ስለምሰራ እና ስለምወደው ሜዳ ላይ በውስጤ ምንም አልይዝም ፤ እጄን ሁሉ እያወራጨው እናገራለው።” ትላለች።

በ2008 ደደቢት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ የነበረው ፍሬው ኃይለገብርኤል የወይንሸት ጥንካራ አቋም እና ሰራተኝነቷ ሁሌም የሚገረምበት መሆኑን እንዲህ ሲል ይናገራል። “ስለሷ ከተጠየኩኝ ደስ ብሎኝ ነው የምመሰክረው። በመጀመሪያ እግርኳሱን በፕሮፌሽናል ቲንኪንግ የምትጫወት ሴት ናት። እጅግ በጣም ፕሮፌሽናል አስተሳሰብን ይዛ ነው የምትራመደው ፤ ለዚህም ነው ብዙ ዓመት የተጫወተችው። ከዚህ በኃላም በጣም የመጫወት አቅም አላት ብዬ አስባለሁ። ለመለያዋ ሟች ነች ፤ ሽንፈትን በጣም ከሚጠሉ ተጫዋቾች ግንባር ቀደም አድርጌ ወስዳታለሁ። ለዚህም ማሳያ እኔ ደደቢት እያለሁ አንድ ጨዋታ ከጊዮርጊስ ስናደርግ በስምንት ነጥብ እየመራን 2-1 ተሸነፍን። ያለመሸነፍ ጉዟችን ስለተገታ መልበሻ ቤቱ በሙሉ ሲያለቅስ የሷ ይለይ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ደስ የምትል ሴት ነች። ለስፖርቱ አስፈላጊ ናት ፤ ታታሪም ነች። ሌላው ለታክቲካል ተገዢ ሆና ነው የምትጫወተው። ሌሎች ሲቸገሩ እሷ ቶሎ ትቀበላለች። በፈለከው ፎርሜሽን እሷን ማጫወት ትችላለህ። በቁጥር አንሰህ ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት ተመራጭ ልታደርጋት እንደምትችል በዚህ አጋጣሚ መናገር እፈልጋለሁ። ቡድን ማነቃቃትም ትችላለች። በውስጧ ክፋት የለባትም። ወደፊት ራሱ ወደ አሰልጣኝነቱ እንደሷ ዓይነት ሰው ቢመጣ አስፈላጊ ነው።”

“ኳስን የምጫወተው ገንዘብ ስለሚያመጣ አይደለም ፤ ፍቅሩ ስላለኝ እና ስለምወደው ነው። ዛሬም ክፍያ ቢቆም ግድ አይሰጠኝም። እግርኳስ የኔ ስሜት ነው።” የምትለዋ ኦሎምቤ የደደቢትን መፍረስ ተከትሎ በ2011 የውድድር ዘመን ወደ አዳማ ከተማ አምራታ በመጀመሪያ ዓመቷ ልክ እንደ ደደቢት ሁሉ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለአምስተኛ ጊዜ ያነሳች ሲሆን ዘንድሮም ሊጉ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በዚሁ ክለብ ጠንካራ የመከላከል አቅሟን እያሳየች ነበር። ይህን ጊዜዋንም እንዲህ ትገልፀዋለች ” ‘እናንተ የዋንጫ ባለቤቶች ናችሁ። እዚህም ዋንጫ እንድትበሉ ነው ያመጣናችሁ’ ብለው አመራር ላይ ያሉ የአዳማ ሰዎች ቃል አስገቡን። እኛም በጥራት ደረጃ ጥሩ ስለነበርን ብዙዎቻችንም ከደደቢት ስለመጣን ሁሉም ቃል የገቡልንን ጥቅሟንም ለማግኘት በ2011 ጥሩ ጊዜ አሳለፍን። ሎዛ እስክትመጣም ድረስ ጥሩ ቡድን ነበር። ሎዛ ከመጣች በኃላ ደግሞ ይበልጥ ቻምፒዮን የመሆናችን ዕድላችን ሰፋ። በአዳማ ደደቢት ላይ የነበረኝን ስኬት ደግሜዋለው። አሁንም ግን በእግር ኳሱ ብዙ ክብሮችን ማየት እፈልጋለሁ ፤ አልጠግብም። ፕሪምየር ሊጉ ለኔ ሁሌ እንደ አዲስ ነው። ኳስን ስትጫወት ሁሌም ክብሮችን ለማግኘት ነው መሆን ያለበት። ይሄ ደግሞ ከእኔ ሁሌም አይጠፋም ፤ ሁሌም አዲስ ነገርን እፈልጋለሁ ፤ በዚህ ደግሞ ደስ ይለኛል።”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ጊዜ የነበራት እና በአፍሪካ ዋንጫም ሁለት ጊዜ የመካፈል ዕድሉን አግኝታ የሀገሯን መለያ የለበሰችው የኃላ ደጀኗ በ2002 በኢኳቶሪያል ጊኒው የአፍሪካ ዋንጫ ተካፋይ ከሆነች በኃላ መመረጥ አልቻለችም። በክለቧ ደደቢትም ሆነ በአሁኑ አዳማ ከተማ በወጥነት ብቃቷን ማሳየት የቻለችው ተጫዋቿ ለሀገሯ ዳግም የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት ኖሯት አለመጠራቷ ለራሷ ሁሌም ጥያቄ እንደሚሆንባት ትገራለች።

“መቆጨቴ ምንም ባያመጣም አለመመረጤ ግን ያናደኛል። ከማንም አላንስም ፤ ብጠራ ሀገሬን በጣም ነው ማገልገል የምፈልገው። አቅም እያለኝ ነው የማልመረጠው። ለምን እንደማልመረጥ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በጣም ከባድ ናቸው ፤ የሚመርጡት ሳይድ ይዘው ነው። ጋዜጠኞችም አሉበት ፤ እነሱም ይመርጣሉ። እዚህ ሀገር ላይ ስትጫወት ለመመረጥ ሰው ያስፈልግሀል። እስከዛሬ የምንመረጠው በሜዳ ላይ ስራ ነበር። በዚህ እኔ አምናለሁ። አሁን ላይ ግን የግድ ሰው ያስፈልግሀል። የግድ አሰልጣኝ ጋር መደወል አለብህ ፤ ከጋዜጠኛ ጋር ማውራት። በፊት እኛ ስንመረጥ እየለመኑን ነበር። አንድም ቀን እንኳን ተቀምጬ አላውቅም። በተመረጥኩ ሰዓት ሁሌም ተቀንሼ አላውቅም ፤ ቤስት ነኝ። በፊት መልካም የሆኑ አሰልጣኞችን አሁን ማንም የሚገመግማቸው የለም። ለአንተ ሚከራከርልህ ሰው የለም። ፌድሬሽኑም ክለብ ላይ ያሉትን አሰልጣኞች ነው የሚመርጠው ፤ ይሄ ደግሞ እኔን ጎድቶኛል። አሰልጣኞች እኔ ክለቤ ላይ ከነሱ ክለብ ጋር ጨዋታን ሳደርግ ይጠምዱኛል። ሜዳ ላይ ላለመሸነፍ ስጫወት ‘ተነጫናጭ ነች’ ይሉኛል። በዚህ ደግሞ ማንም ያውቀኛል። ለምሳሌ ለደደቢት ነፍሴን ነው የምሰጠው። ደደቢት ያለኝ ባህሪ ብሔራዊ ቡድን ላይ ሊኖረኝ አይችልም። ስንት ዓመት ሙሉ ብሔራዊ ቡድን ስጫወት መጥፎ ባህሪ የለኝም። ይሄን ደግሞ አሰልጣኞች ያኔም ያሉ አሁንም ያሉ ያውቃሉ። በአጠቃላይ የሴት አሰልጣኞች ናቸው ኳሱን እየገደሉ ያሉት። እኔ ብቻ አይደለሁም ብዙ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉ ያልተጠሩ። ለእኔ ብቻ አይደለም ለነሱም ወግኜ እናገራለሁ። መጠራት ባለብን ሰዓት ‘ዕድሜያቸው ገፍቷል’ ይላሉ። ዕድሜያችንን ሚያውቁት እነሱ ናቸው እንግዲህ እኛ አናውቅም። የምናውቀው ግን እኛ ነን እንደሚያጫውተን እና እንደሚያጫውተን። እግርኳስ የቢሮ ስራ አይደለም የሜዳ ላይ ስራ ነው። አንድም ቀን አቋሜ ወርዶ አያውቅም። ከሜዳ ውጪ ከማንም ጋር አላወራም ፤ ከማንም ጋር አልደዋወልም። በቃ ግዴታ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት መደዋወል አለብህ የአሰልጣኝ ስም አቀማጥለህ መጥራት አለብህ። ይሄ ይሄ ነገር ስላለ ኢትዮጵያ እኔን አጣችኝ እንጂ እኔ እትዮጵያን አላጣዋትም ፤ እግዚአብሔር ይመስገን እየኖርኩባት ነው። እኔ ብኖር ምንም ላላመጣ እችላለሁ። ግን ልምድ ሰጥቼ መውጣት እችላለው። ከክለባችን ሦስት ተጫዋቾች ተጠርቶ እኔ አልጠራም። እኔ ተሽዬ እያለሁ እኔ አልጠራም። አሰልጣኞች ጋር በጣም ፉክክር አለ። ለምሳሌ የባንክ አሰልጣኝ ወደ ብሔራዊ ቡድን ከመጣ የባንክ ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የሚመረጡት። እንዲሁም የጊዮርጊስ አሰልጣኝ ስትመረጥ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የሚመረጡት። ለኛ የሚከራከርልን ሰው የለም። ሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫዎች ሌላ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ እንችል ነበር። ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት ስታድየም ገብቼ አያለሁ ፤ እያለቀስኩ እና እየተቆጨው ነው የምወጣው። ለንግግር የለም ፣ ማውራት የለም ሁሉም አስመሳይ ነው። ተጫዋቹም አሰልጣኙም የእውነት የሚጫወት ሰው ሁሌም ተጎጂ ነው። የእውነት እጫወታለሁ የእውነት እስቃለሁ አስመስዬ ግን አልኖርም። ሜዳ ላይ ባህሪዬ እና እልኸኝነቴ ስለሚታይ በዛ በዛ ነገር ደግሞ ልጎዳ ችያለሁ።”

በእግርኳሱ ውጣ ውረዶችን አልፋ ዛሬ ላይ የደረሰችው ወይንሸት 2005 ላይ በደደቢት እያለች በመጨረሻው ሰዓት ዋንጫ ማጣታቸው እንደሚያስቆጫት የተናገረች ሲሆን “ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ለስኬቴ ትልቅ ድርሻ አላቸው። በምክር እና በእገዛ ብጠራቸው አያልቁም ግን ሁሉም ለረዱኝ እና ለደገፉኝ በእግዚአብሔር ስም ማመስገን እፈልጋለሁ” በማለት ሀሳቧን ቋጭታለች፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ