“የዘመናችን ከዋክብት ገፅ” ከባዬ ገዛኸኝ ጋር …

የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ እንግዳችን የወላይታ ዲቻው ባዬ ገዛኸኝ ነው።

በደቡብ ክልል ሚዛን ቴፒ ከተማ እንደተወለደ የሚናገረው ፈጣኑ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ እንደማንኛውም ታዳጊ ኳስን ከልጅነቱ ጀምሮ ሲጫወት ቆይቷል። ምንም እንኳን በቴፒ አካባቢ በርካታ የእግርኳስ ፕሮጀክት ቡድኖች ባይኖሩም በተለያዩ የሰፈር ውስጥ ውድድሮች እራሱን አጎልብቶ ትልቅ ደረጃ ደርሷል። በተለይ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚደረጉ የእግርኳስ ውድድሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረው ተጫዋቹ ቀስ በቀስ ወደ ታላቅነት የሚያደርገውን ጉዞ በዞን ደረጃ “ሀ” ብሎ ጀምሯል። ትምህርትም ለእርሱ እንዳልተፈጠረ በመረዳት ወዲያውኑ ትኩረቱን እግርኳስ እና እግርኳስ ላይ በማድረግ ህይወቱን ቀጥሏል።

በትውልድ አካባቢው ለሚገኝ የዞን ቡድን እግርኳስን መጫወት የጀመረው ባዬ በመቀጠል ለወራቤ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ግልጋሎት ሰጥቷል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ወደ ወላይታ ድቻ ዳግም ተመልሶ እየተጫወተ ይገኛል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚጠበቀውን ያህል ብዙም ግልጋሎት ያልሰጠው ተጫዋቹ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የአሰልጣኝነት ዘመን ጥሪ ቀርቦለት ሀገሩን አገልግሏል። እርግጥ ተጫዋቹ በሌሎች ጊዜያት ጥሪ ቢቀርብለትም በወጥነት የመጫወት እድል ግን ሳያገኝ ቆይቷል። ሶከር ኢትዮጵያም ከዚህ ፈጣን እና ቀልጣፋ አጥቂ ጋር በዘመናችን ከዋክብት ገፅ ቆይታ አድርጋለች።

በዚህ ወቅት ባዬ ጊዜውን በምንድን ነው የሚያሳልፈው?

ብዙ ጊዜ ከቤት አልወጣም። አስቸኳይ ጉዳይ ሲኖረኝ ብቻ ነው ከቤት የምወጣው። ቤት ውስጥም የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ ጊዜዬን አሳልፋለሁ። በዋናነት ልምምዶችን በቋሚነት አከናውናለሁ። ከዚህ ውጪ ግን ፊልሞችን እያየሁ ነው በቤቴ ጊዜዬን የማሳልፈው።

ባዬ እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

ከእግርኳስ ውጪ ሌላ ሙያ ነበረኝ። አውቶ ሜካኒክ ትምህርት ተምሬያለሁ። ምናልባት ከዚህ መነሻነት ሜካኒክ ወይም ሹፌር የምሆን ይመስለኛል።

ከማን ጋር ተጣምረህ ብትጫወት ደስ ይልሀል?

ከሳልሃዲን ሰዒድ ጋር ብጣመር ደስ ይለኛል። ሳላ ምርጥ አጥቂ ነው። ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው ነገሮች በጣም ልዩ ናቸው። በአጠቃላይ የተሟላ አጥቂ ስለሆነ ከእርሱ ጋር ብጣመር ደስ ይለኛል።

በእግርኳስ ውስጥ ካሉ ግለሰቦች ሚስጥረኛህ ማነው?

አዲሱ ተስፋዬ ምርጥ ጓደኛዬ ነው። በእግርኳስ ውስጥ ኳሉ ተጫዋቾችም ለእርሱ በጣም እቀርባለሁ።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል? ትዳር መስርተሃል?

እስካሁን ትዳር አልመሰረትኩም። ኮሮና ባይመጣ ኖሮ በዚህ ሰዓት ምናልባት ወደ ትዳሩ ዓለም ገብቼ ነበር። ፈጣሪ ይህንን በሽታ ያጥፋልንና በቀጣይ ትዳር እመሰርታለሁ ብዬ አስባለሁ።

ባዬ በእግርኳስ ያዘነበት ክስተት ይኖር ይሆን?

መከላከያ እያለሁ ጉዳት የደረሰብኝ ክስተት በጣም አሳዝኖኝ ነበር። በመከላከያ ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ዓመቱ ሊገባደድ ሲል ከፍተኛ የሆነ የጉልበት ጉዳት አዳማ ላይ ስንጫወት ደርሶብኛል። ይህ ክስተት በእግርኳስ በጣም ካዘንኩባቸው ጊዜያት ቀዳሚው ነው።

የተደሰትክበትስ አጋጣሚስ?

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደ ብሄራዊ ቡድን ሲጠራኝ በጣም ተደስቼ ነበር። በተለይ ባህር ዳር ላይ በሌሶቶ 1-0 እየተመራን ተቀይሬ ገብቼ 2-1 ያሸነፍንበት ጨዋታ በጣም የፈነደቅኹበት ጊዜ ነበር።


ምግብ ላይ እንዴት ነህ? የምትወደው እና የምትጠላው የምግብ አይነት ምንድን ነው?

ቁርጥ እና ዶሮ አንደኛ ምርጫዎቼ ናቸው። በተለይ ቁርጥ ሥጋ አዘወትራለሁ። በተቃራኒው ጥቁር ጎመን አይደለም መብላት ማየት አልፈልግም። ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ግን ጎመን አልወድም።

ሰዎች የማያውቁት የተለየ ባህሪ አለህ?

ምናልባት ሆደ ሰፊ እንደሆንኩ ብዙ ሰዎች ላያውቁ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ስከፋም ሆነ ስደሰት ስሜቴን በውስጤ የመያዝ ችሎታ አለኝ። በተለይ ስናደድ የተሰማኝን ስሜት ለሰዎች ማጋራት ስለማልፈልግ በውስጤ ቻል አድርጌ ጊዜውን አሳልፋለሁ።

ቅፅል ሥም አለህ እንዴ?

አዎ ድቻ ቤት ‘ባቢ’ ያሉኛል። ይህንን ቅፅል ሥም ያወጣልኝ ሙባረክ ሽኩር ነው። ስሙንም ከምን ተነስቶ እንዳወጣው አላቅም። ብቻ አንድ ቀን ዝም ብሎ ከዚህ በኋላ ባቢ ነው የምልህ አለኝ። ከዛ በኋላ ሁሉም ባቢ እያሉ ይጠሩኝ ጀመር።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚፈትንህ ተጫዋች ይሆር ይሆን?

ግርማ በቀለ ይፈትነኛል። የእርሱ አጨዋወት ትንሽ ኃይል የተቀላቀለበት ስለሆነ ይፈትናል።

ኳስ ከመጫወት ውጪ ምን ማድረግ ያስደስትሃል?

ይሄን ያህል እንኳን የተለየ የማከናውነው ነገር የለም። ግን አሁን ወደ ንግዱ ዓለም እየገባሁ ነው። በተለይ በዚህ የኮሮና ወቅት ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት እየሞከርኩ ነው። ከማስኮች ጋር የተገናኙ ሥራዎችንም አሁን ላይ እየሰራሁ ነው። ወደፊትም ከኳሱ ውጪ ወደ ንግዱ በደንብ በመግባት ተሳትፎ ለማድረግ አልማለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ