የ5ኛ ዙር የማዕድ ማጋራት መርሐግብር ዛሬ ተከናውኗል

“እናንተ ውድ ኢትዮጵያዊያን ኑ መአዳችንን በጋራ እንካፈል” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ የሚገኘው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ዛሬም በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የጋራ ትብብር ለ5ኛ ጊዜ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ይህ የምገባ መርሐግብር ዛሬ ምሳ ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀጥሏል። ከዚህ ቀደም በአራት ዙሮች የምገባ መርሃግብሩን ያስቀጠሉት እነኚሁ የእግርኳስ ቤተሰቦች “እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገረዋለን” በሚል ሀሳብ ተሰባስበው በርካታ አቅመ ደካሞችን እያገዙ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ በአሜሪካ ቨርጂኒያ የሚገኙ የፍኖተ ህይወት በአታ ለማርያም ወቅዱስ ሚካኤል ኢ.ኦ.ተ. ቤ/ክ ማህበር አባላት፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ የቤላ ወጣቶች ስለፍቅር በአንድነት መረዳጃ ማህበር አባላት እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የጋራ ትብብር የተሰናዳው መርሃ ግብሩ በዛው እለት ከ1500 በላይ አቅመ ደካሞችን ምሳ መግቧል።

በመጀመሪያ ዙር 300፣ በሁለተኛ ዙር 750 እንዲሁም በሶስተኛ እና በአራተኛ ዙር 1500 ግለሰቦች በምገባው ላይ ተገኝተው መዓድ ተጋርተዋል። በዛሬው ፕሮግራምም ላይ ደግሞ 1500 ሰዎች በስታዲየም ተገኝተው ምገባ ተደርጎላቸዋል። ከምገባው መጠናቀቅ በኋላም በስፍራው ለተገኙ አቅመ ደካሞች የንፅህና መጠበቂያ እና የማስክ እደላ ተደርጓል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ