“በእግርኳስ ሕይወቴ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ትልቅ ቦታ አለው” ተስፈኛው ከድር ዓሊ

በዛሬው የተስፋኞች ገፃችን ላይ ከሁለገብ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ከድር ዓሊ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል።

በጎንድር ከተማ ተወልዶ ያደገው ከድር ዓሊ በከተማው በኃይሉ ነጋሽ (ቲጋና) በሚሰጠው የ13 ዓመት በታች የእግርኳስ ፕሮጀክት ኳስን መጫወት የጀመረ ሲሆን በ2008 ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በማምራት ስኬታማ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል። በ2010 ታንዛኒያ ላይ ለፍፃሜ ቀርቦ የነበረው የ17 ዓመት በታች ቤሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካቶ ነበረው ከድር የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ እየተቀየረ በመግባት ሀገሩን ማገልገሉም ይታወሳል። በቀጣዩ የውድድር ዓመት ደግሞ ከ17 ዓመት በታች የሊግ ውድድር ላይ በግሉ መልካም ዓመት ያሳለፈው ከድር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በ2012ም ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን ተቀላቅሎ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት ነበር የዘንድሮ የውድድር ዓመት የተቋረጠው። ይህ ተስፈኛ አጥቂ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታን በማድረግ የዛሬው እንግዳችን ሆኗል።

“እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት በትምህርት ቤት ነው። ከቤተሰብ ፍቃድ ስለማላገኝ ከትምህርት ቤት ውጪ መጫወት አልችልም ነበር። ቲጋና ታዳጊዎችን መያዝ የጀመረበት ዓመት ላይ ተመርጬ ነበር። ነገር ግን በዕድሜ ትንሽ ስለነበርኩ ቤተሰቦቼ ሳይፈቅዱልኝ ቀርተው አቋረጥኩ። እናም ከሁለት ዓመት በኋላ እንደገና ወደ ቲጋና ቡድን ሄድኩ። ከዚያም ጎንደርን በመወከል ጅጅጋ ላይ በተካሄደው የኮካኮላ ሻምፒዮንሺፕ ተካፈልኩ። በመቀጠል አካዳሚ ተመረጥን ሙሉ የቲጋና ልጆች ነበርን ጎንደርን ወክለን የሄድነው። ስንመለስ ደግሞ ለአማራ ተመረጥን እና ቲጋና ራሱ ይያዘው ተብሎ ከውድድሩ መልስ ነው አካዳሚን 2008 ላይ የተቀላቀልኩት። ከቲጋና ጋር አንድ ዓመት ብቻ ነበር የሰራሁት። ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሄድን ጊዜ አንደ ቡድን ጥሩ የውድድር ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። አጭር የለምምድ ጊዜ ነበር የነበረው ቢሆንም ግን ጥሩ ጊዜ ነበረን። ከተመለስን በኋላ ኢትዮጵያ መድን ‘ሙሉ ቡድኑን እይዛለሁ’ ብሏል ሲባል ሰምተን ነበር ምክንያቱን ባላውቅም ሳይሳካ ቀርቷል።

 

“ከቤተሰብ ድጋፍ አይደረግልኝም ነበር ፤ እናቴ ነበር የተሻለ ነገር የነበራት። ከዛም ጎንደርን ስወክል እና ለአማራ ክልል ስመረጥ ጥሩ ነገር እንዳለኝ ሲረዱ ድጋፍ ያደርጉልኝ ጀመር። መጀመሪያም የፈቀዱልኝ ቲጋና ፍቃድ ጠይቆልኝ ነው። ወደ አካዳሚም ስሄድ ቅሬታ አልነበራቸውም ፤ ደስተኛ ነበሩ። አዲስ አበባ ላይ ቤተሰብም ስላለኝ ደስ ብሎኝ ነው የመጣሁት።

” የአካዳሚ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነው ፤ ሦስተኛ ዓመት ላይ ደርሻለሁ። በስልጠና ደረጃ በጣም ጥሩ ነው ፤ ደስተኛ ነኝ። ያው ሁሉም ቦታ ላይ ችግሮች አይጠፉም ፤ እንደ ሀገር ክለቦቻችን ላይም ጉድለት አለ። ወደ አካዳሚ ለሚመጡ ልጆች ማለት የምፈልገው አካዳሚ ሲመጡ በደንብ አጣርተው ቢመጡ ጥሩ ነው። በርካታ ታዳጊዎች ጠብቀውት ሚመጡት ነገር ከፍ ያለ ነው እና አጣርተው ቢመጡ የተሻለ ነው ።

“በእግርኳስ ለእኔ ትልቅ ቦታ ያለው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ (ቲጋና) ነው። በርካታ ነገሮችን አድርጎልኛል። ሁሌም ከጎኔ ነው ፤ ለሱ ትልቅ ቦታ አለኝ። ላመሰግነውም እፈልጋለሁ ፤ ቤተሰቦቼን ቀርቦ አስፈቅዶልኝ የምወደውን እግርኳስ እንድጫወት ስለደረግኝ። ቤተሰቦቸም በጣም ነው የሚደግፉኝ ፤ አጎቶቼም እህቴም በጣም ይደግፉኛል። ሁሉንም አመሠግናቸዋለው።

“ኢትዮጵያ ውስጥ የሳላዲን ሰዒድ አድናቂ ነኝ። ሳላዲን የተለየ ተጫዋች ነው። ለታዳጊዎች ተምሳሌት መሆን የሚችል አቅም ያለው እና በሀገርም ደረጃ ትልቅ ተጨዋች ነው። ከሀገር ውጪ ደግሞ የኔይማር ጁኒዬር አድናቂ ነኝ።

” ወደፊት ትልቅ ተጫዋች መሆን እፈልጋለሁ። ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ወጥቶ የመጫወት ዕቅድ ነው ያላኝ። ያን ለማሳካት ነው ጠንክሬ እየሰራሁ ያለሁት። እንዲሁም ብሔራዊ ቡድን መጫወት እፈልጋለሁ። ከዚህ በፊት ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሀገሬን ማገልገል ችያለሁ። አሁንም ከ20 በታች ዋናው ቡድን ላይም ከሀገሬ ጋር ጥሩ ነገር ማሳካት እፈልጋለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ