በሀገራችን ከታዩ ምርጥ አጥቂዎችና የችሎታቸውን ያህል ካልተዘመረላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በሀገሪቱ ትልልቅ ክለቦች በዋንጫ የታጀበ የእግርኳስ ዘመን በስኬት አሳልፏል። ብሔራዊ ቡድናችን ካልተጠቀመባቸው አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የወቅቱ አሰልጣኝ እና የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ ዮሴፍ ተስፋዬ (ቫንባስተን) ማነው?
የቅድሞ ድንቅ ተጫዋች ኃይሌ ካሴ ኳስ ሜዳ እና አሸዋ ሜዳ በሚጫወቱበት ወቅት አንድ ወንድሙ የገዛለት የኤሲ ሚላን መለያ አድርጎ ረዥም፣ ቀጭን ታዳጊ ልጅ ሲጫወት ያየዋል። ፍጥነቱን፣ እርሱን ተከላካዮች ለመያዝ ሲቸገሩ፣ የኳስ አመታቱን፣ የጎል አጨራረሱን ሲመለከት ይሄ ልጅ ከሆላንዳዊው ታላቅ አጥቂ ቫንባስተን ጋር አጨዋወቱ ቢመሳሰልበት “ቫንባስተንን ያዙት’ እያለ ሲነግራቸው በዛው ቅፅል ስሙ ሆኖ የቀረው ዮሴፍ ተስፋዬ ትውልድ እና ዕድገቱ የኳሰኞች መፍለቂያ በሆነው መሳለሚያ ኳስ ሜዳ አካባቢ ነው። ኃይሌ ካሴ፣ ፉዓድ አብዱልቃድር፣ ብሩክ እስጢፋኖስ፣ ሰለሞን ቸርኬ እና ጌቱ ከበደን እየተመለከተ ያደገው ዮሴፍ እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የአዲስ አበባ እግርኳስ እንብርት በሆነችው ኳስሜዳ በመጫወት አድጓል።
ዮሴፍ የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እያለ 1982 እና 83 ባህር ኃይል ቢ ቡድን ተጫውቶ የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ለከፍተኛ ሰባት እና አካባቢው ተጫውቷል። በመቀጠል ተወልዶ ባደገበት አካባቢ ለሚገኘው ለህዝብ ማመላለሻ ለአንድ ዓመት ሲጫወት ቆይቶ በ1987 ጀምሮ ለሙገር ሁለት ዓመት አገልግሏል። በሙገርም ቆይታው የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ካነሳ በኃላ በተለይ አቅሙን አውጥቶ ወደተጫወትበት እና በብዙዎች የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ወደታወቀበት ኢትዮጵያ ቡና በ1989 ሊቀላቀል ችሏል። ለቡና በጉዳት ምክንያት ካልሆነ በቀር በፊት መስመሩ ላይ የአሰግድ ተስፋዬ አጣማሪ በመሆን በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል። ኢትዮጵያ ቡና የ1989 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ዋንጫን፣ የአሸናፊ አሸናፊን ዋንጫን እንዲሁም በ1990 የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሲያነሳ ከቡድን አጋሮቹ ጋር አብሮ በመሆን ታሪክ የሠራ ድንቅ አጥቂ ነው። በ1989 ላይ ተከተል ኡርጌቾ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ባጠናቀቀበት ዘመን ጉዳት እየፈተነው አልፎ አልፎ ከሜዳ እራቀ እንጂ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ የመጨረስ ዕድል ሰፊ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ከአጥቂነቱ በተጨማሪ ወደ ኃላ ተመልሶ ኳሶችን አደራጅቶ ወደፊት በመሄድ፣ ሰው ቀንሶ በማለፍ እና ለቡድኑ ጥንካሬ በመስጠት የሚታው ዮሴፍ ከሦሰት ዓመት የኢትዮጵያ ቡና ቆይታ በኃላ 1992 እና 93 ለሙገር እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለአንድ አንድ ዓመት ተጫውቶ በመቀጠል በ1994–95 ድረስ ሁለት ዓመት ለመድን ሲጫወት ቆይቶ ከ1996–98 ድረስ በሀዋሳ ከተማ የተሳካን ጊዜ አሳልፏል። ከአጥቂነት ባህሪው ወደ ኃላ በመመለስ ከሙሉጌታ ምህረት እና ከበኃይሉ ደመቀ ጋር በአማካይ ስፍራ ላይ የነበራቸው ድንቅ ጥምረት የክልል ቡድን በታሪክ መጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በ1996 እንዲያነሳ ማድረግ ችሏል። በተለይ በዚሁ ዓመት ኮከብ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ በአወዛጋቢ ሁኔታ የመሆን እድሉ መጨናገፉ ይታወሳል።
በሀዋሳ ከተማ አብሮት የተጫወተው በኃይሉ ደመቀ ስለ ዮሴፍ እንዲህ ይናገራል “ዮሴፍ ለኔ ኳስን በስሜት ከመጫወት ወጥቼ በአዕምሮዬ እንድጫወት የቀረፀኝ በትክክለኛ ሰዓት ያገኘሁት አስተማሪዬ ነው። አስገራሚ እይታ ያለው ተረጋግቶ በእውቀት የሚጫወት የኔ ምርጡ አማካይ ነው። ስለ መልካምነቱ ቃል የለኝም፤ እጅግ ሲበዛ ባለ ሙሉ ስብእና ባለቤት ነው። ጆሲ (ቫንባስተን) ይችላል” በማለት ተናግሯል።
በእግርኳስ ክህሎቱ እና በመልካም ስነ ምግባሩ የሚመሰከርለት ዮሴፍ ከሀዋሳ ጋር የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ካገኘ በኃላ ጫማውን እስከሰቀለበት 2001 ድረስ ለሦስት ዓመታት ያህል ለሐረር ቢራ ተጫውቷል። በሐረር ቢራ በነበረውም ቆይታ በ1999 የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ቡድኑ እንዲያነሳ የእርሱ ሚና ከፍተኛ ነበር። ብሔራዊ ቡድን ካልተጠቀሙባቸው አጥቂዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩለት ዮሴፍ ግብፅ ላይ 5-0 ተሸንፎ እዚህ 5-0 አሸንፎ በፍፁም ቅጣት ምት የወጣው የወጣት ቡድን ውስጥ አባል ነበር።
እግርኳስን ባቆመበት ዓመት በፍጥነት ወደ አሰልጣኝነቱ የገባው ዮሴፍ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን እያሰለጠነ ሲገኝ ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል። ይህ የዘጠናዎቹ ወርቃማ አጥቂ ዮሴፍ ተስፋዬ የዛሬው እንግዳችን ነው።
“የእግር ኳስ ህይወቴ ስኬት በቡና 1989 እና 90 በነበረው ቡድን ውስጥ የማልረሳው ጊዜ ነው። ቻምፒዮን የሆንበት፣ አል-አህሊን ከውድድር ያስወጣንበት ጨዋታ ለኔ ትልቁ ስኬቴ ነው። ሙገር ሆኜ ደግሞ 1987 ላይ ዋናው በር የከፈተለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሁለት ግብ አግብቼ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያነሳንበት ነው። ከሀዋሳ ከተማ ጋር የመጀመሪያው የክልል ቡድን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አሸናፊ እንዲሆን ያስቻልንበት በእግር ካስ ህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውቸው ስኬቶች ናቸው።
” የምቆጭበት ነገር ብዙም የለኝም። ከልጅነቴ ጀምሮ የምችለውን ያህል ያለኝ ሰጥቼ 17 ዓመታት ያህል ነው የተጫወትኩት፤ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። መቀጠልም መጫወት እችል ነበር። በእግርኳሱ ችክ ማለት አልፈልግም ብዬ ነው ያቆምኩት። ለተተኪዎችም ቦታውን መልቀቅ ያስፈልጋል።
“በ1989 የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ የመጨረስ ከፍተኛ እድል ነበረኝ። ተከተል ኡርጌቾ 12 ጎል አስቆጥሮ ቁጭ ብሎ ነበር። እኔ በቀሪ ጨዋታ ከንግድ ባንክ ጋር እየተጫወትን ሁለት ጎል አስቆጥሬ 11 ጎል ደርሼ ነበር። ሆኖም ተጨማሪ ጎል የማስቆጥርበት አጋጣሚ ቢኖረኝም ዐብይ ሀይማኖት ጉልበቴ ላይ ባደረሰብኝ ጉዳት መጫወት አቅቶኝ ተቀይሬ ወጣው እንጂ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ መሆን እችል ነበር።
“ወደ አሰልጣኝነቱ የገባሁት 2002 እግርኳስን እንዳቆምኩ ነው። ሳሪስ አካባቢ ነበር የምኖረው፤ ሰለሞን አባተ የሥዩም አባተ ወንድም ተጫውተው ያሳለፉትን ጥሩልኝ ብሎ መልዕክት ልኮብን አንደኛ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና ወሰድኩ። ከዛ በኋላ የተለያየ ስልጠናዎችን ስንወስድ ቆይቼ ሲ እና ‘ቢ አጠናቅቄ ከ2008 ጀምሮ በባለሀብቶች እና ተጫውተው ያሳላፉ ኳስ ሜዳ እና አካባቢው የተሰኘ አንድ ቡድን አቋቀምን በማሰልጠን ስልጠናን ጀመርኩ። በ2009 ላይ በዕድሉ ደረጄ ጠቋሚነት ከ20 ዓመት በታች የቡና ታዳጊ ቡድን ም/አሰልጣኝ ሆኜ ተቀጠርኩ። በመቀጠል ሦስት ጨዋታ እንደተጫወትን ዕድሉ ወደ ዋናው ቡድን ሲሄድ እኔ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆንኩ ፤ እስካሁንም እየሰራው ነው። 2010 ላይ ዙሩን አሸንፈን ዝዋይ ላይ በነበረው ውድድር ፍፃሜ መድረስ ችለናል። በዚህ መልካም ውጤትም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንድሆን እድሉን አመቻችቶልኛል።
“በአሰልጣኝነት ህይወቴ የወደፊት ዕቅዴ እንደመነሻ አሁን ወጣቶች ላይ ነው እየሰራው ያለሁት። እዚህ ላይ ለቡድኔ ጥሩ ጥሩ ልጆችን ማዘጋጀት እና ማቅረብ ነው የማስበው። ወደፊት ራሴን እያዘጋጀው በትልቅ ደረጃ ማሰልጠን እፈልጋለው።
“ስለያኔ እና አሁኑ የእግር ኳሱን ሁኔታ ያለው ነገር ለመግለፅ በፊት በጣም ብዙ ጥሩ ተጫዋቾች ነበሩ። ዕድሉን ሳያገኙ ሰፈር ውስጥ የቀሩ በጣም ብዙ ኳስ ተጫዋቾች ነበሩ። አንድ ቡድን ውስጥ ራሱ ዋና እና ተጠባባቂን ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ ማለት ነው። አሁን ላይ እንደዚህ ከሰፈር ከታች የሚመጣ ፉክክር የለም። አሁን እግርኳሱ በተወሰኑ ተጫዋቾች ቁጥጥር ስር ነው ያለው። ከአንዱ ክለብ አንዱ ክለብ እየተዘዋወሩ የሚቆዩበት እንጂ ፉክክር አለ ማለት ይከብደኛል። በፊት አስረኛ ያለው ቡድን አንደኛውን በጣም ነው የሚፈትነው። ወራጁ ቡድን ሊያሸንፍም ይችላል። ቢሸነፍም እራሱ በመከራ ነው። አሁን ዋና ተሰላፊውም፣ አሸናፊውም በቀላሉ ነው የሚታወቀው።
“ሁለት ወንድ ልጆች አሉኝ አንደኛው ገና ስምንት ዓመቱ ነው። ወደፊት እግርኳስ ተጫዋች ይሆናል ለማለት ከወዲሁ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ቢከብድም ፍላጎት አለው። የመጀመርያው ልጄ ቅዱስ ዮሴፍ ይባላል። አስራ ስምንት ዓመቱ ነው። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በአሁን ወቅት ለአፍሮፅዮን ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በተላካይ ቦታ እየተጫወተ ነው። ያው የአሰልጣኙ እምነት ነው እኔ አጥቂ ሆኜ እርሱ ተከላካይ መሆኑ። ወደፊት ወደ እኔ ቦታ መጥቶ ይጫወት ይሆናል።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ