መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፫) | ቴስተኛው በቴስታ ሲወድቅ

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምንጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ቆይታም ባለፉት ሳምንታት አጫውተናችኋል። ዛሬ ደግሞ በወቅቱ እጅግ መነጋገሪያ የነበረው የተክሌ ኪዳኔ እና መንግሥቱ ወርቁን አጋጣሚ ይዘንላችሁ ቀርበናል።


ማስታወሻ ፡ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግስቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና “ፍትሀዊ የጠጅ ክፍፍል እና ሌሎች …” የተሰኙት ሁለት የገነነ መኩሪያ መፅሀፍት ለፅሁፋችን ዋነኛ ግብዓት መሆናቸውን እንገልፃለን።

ተክሌ ኪዳኔ ይባላል፤ የአስመራ ቴሌ ተጫዋች እና ከወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተሰላፊዎች መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ሦስተኛዉን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ በፍፃሜው ግብፅ ላይ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረውም ይኸው ተክሌ ኪዳኔ ነበር። ተክሌ በብሔራዊ ቡድን አጋሩ ከሆነው መንግሥቱ ወርቁ ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው። ያን ብቸኛውን አህጉራዊ ድል ባበሰረው እልህ አስጨራሹ የግብፁ ጨዋታ ላይ ሁለቱም ግብ ማስቆጠራቸው እና ተቃቅፈው ሲጨፍሩ ማምሸታቸው ብቻ ሳይሆን መንግሥቱ ዘና ለማለት ወደ አስመራ ባቀና ቁጥር በእንግድነት ቤቱ ተቀብሎ መኪናውንም ጭምር ሰጥቶት የሚያስትናግደው የብሔራዊ ቡድን ጓዱ የቴሌው ተክሌ መሆኑም ጭምር የባልንጀራነታቸው አንዱ ማስረጃ ነው። ነገር ግን በወቅቱ ከነበረው ከፍተኛ ፉክክር አንፃር እንኳንስ የተለያዩ ክለብ ተጫዋቾች ይቅሩና አንድ ክለብ እንኳን የሚጫወቱ ቢሆኑ እና ጓደኝነታቸው ምንም ያህል የዘለቀ ቢሆን በልምምድም ይሁን በጨዋታ ልክ እንደማይተዋወቁ ሁሉ አንዳቸው ለሌላኛቸው አይተኙም ነበር። ከጨዋታ በኋላ ይህ ስሜት ቶሎ የሚጠፋ ቢሆንም አንዳንድ ከበድ ያሉ አጋጣሚዎች ግን ከዚህም ያለፈ ቁርሾን ሲፈጥሩ ከተጫዋቾችም አልፎ ለደጋፊዎች መቃቃር እና ለግጭቶችም መንስኤ እስከመሆን ይደርሳሉ። በተክሌ እና በመንግስቱ መሀል የተፈጠረውም ለዚህ የቀረበ ነበር።

ጊዜው 1959 ነው፤ ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና የአስመራው ቴሌ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍፃሜው ተፋጠዋል። ይህን ጨዋታ አሸንፈው ሦስተኛውን ድል በማወጅ ትልቁን ወርቃማ ዋንጫ እስከወዲያኛው ለማስቀረት በያኔው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ስታድየም ተገናኝተዋል። ውጥረት በሞላበት በዚህ ታላቅ ፍልሚያ መሀል ግን የወቅቱ አነጋጋሪ ክስተት በመንግሥቱ እና ተክሌ መሀል ተፈጠረ። ለወትሮው የሁለቱ ቡድኖች አጥቂዎች በየፊናቸው በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ላይ ስለሚውሉ እርስ በእርስ የመገናኘታቸው ነገር እምብዛም ነበር። በዛን ጨዋታ ላይ ግን በእንቅስቃሴ መሀል የቴሌው አሰልጣኝ ተክሌን ወደ ኋላ እንዲሳብ አደረጉ። በዚሁ ጊዜ ከሸዋንግዛው ጋር ቦታ በመቀያየር ማጥቃት የለመደው መንግስቱ ተመሳሳይ ዘዴን ተጠቅሞ ኳስ ለመቀበል በተነቀሳቀሰበት ቅፅበት ከኳሷ ጋር ሳይገናኝ የተክሌ ቴስታ ቀደመው። ለኳስም ሆነ ለፀብ ቀድሞ ቴስታ መስደድ የሚቀናው መንግስቱ በራሱ ጥይት ተቀድሞ ሳያስበው በድንገት ባረፈበት ምት ተዘረረ ፤ በወደቀበትም ተክሌ ሲሳደብ ይሰማው ነበር። ታላቁ ስምንት ቁጥር የደረሰበት ጉዳት ከባድ እንደሆነ በሚጠቁም መልኩ እንደሌላው ጊዜ በቶሎ አልተነሳም ፤ አፉን በተለየ ሁኔታ መረረው። በጉልበቱ በርከክ ለማለት እየሞከረ ምን እንደመረረው ሲያስተውል አፉ በደም ተሞልቷል ፤ ሁለት ጥርሶቹም ወልቀዋል። ተክሌ ያደተሰበትን ባወቀ ጊዜም ” ወይኔ መንግሥቱ !” ነበር ያለው።

የቡድን አጋሮቹ እና ስታድየሙን የሞላው ደጋፊ የሆነውን ቢያውቅ ጨዋታው ወደለየለት ትርምስ እንደሚቀየር ያውቃል። ስለሆነም ማንም ሳያየው ጥርሶቹን ኪሱ ከቶ ጨዋታውን ለመጨረስ ወሰነ። ተክሌም ወትሮም መንግስቱ ሲነካ እንደንብ መንጋ የሚነሱት እና እሱንም ‘ካልደበደብነው’ ከሚሉት የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ገለል ያደረገውን የዳኛውን ቀይ ካርድ ተቀብሎ ከሜዳ በውጣት በፖሊስ ጥበቃ ውስጥ ቆየ። ክለቡ ጥርሱን የማሳከም አቅም እንደሌለው የሚያውቀው መንግስቱም ከባድ ህመም ቢሰማውም የሁልጊዜውም የእልህ ስሜቱ ከቁስሉ በላይ ሆኖ “ሌላውም ጥሬሴ ይሰበራታል እንጂ አልወጣም” ብሎ የመጀመሪያውን አጋማሽ ጨረሰ። ወደ መልበሻ ክፍል በማምራት ላይ ሳለም በተፈጠረው ነገር እጅግ የተናደደ እና ስሜቱን መቆጣጠር ያልቻለ አንድ ደጋፊ ወደ መንግስቱ በመቅረብ ” እንዴት ሲመታህ ዝም ትላለህ ? እንካ ተክሌን ግደለው ” በማለት ሽጉጥ ሰጠው። በህይወቱ ሽጉጥ በጣም የሚጠላው መንግስቱ የደጋፊው አቀራረብ ቢያስደነግጠውም ሁኔታውን ማረጋጋት እና ጨዋታውን ማሸነፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ስለነበር አስደንጋጩን ጥያቄ ሳይቀበል ወደ ውስጥ ዘለቀ። ጨዋታው ከተገባደደ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለድል ሆኖ ደጋፊውም አሸናፊነቱን በጭፈራ ሲያከብር ቢቆይም ተክሌ የማይተካው ውዱ ተጫዋቻቸው ላይ ያደረገውን ግን ፈፅሞ አልረሱም ነበር። “ተክሌን ካልገደልን አንሄድም ! ” በማለት በስታድየሙ መውጫ ላይ ይጠባበቁ ጀመር። የቴሌን ሰርቪስ አስቁመው እስከመፈተሽም ደረሱ ፤ ተክሌ ግን የውሀ ሽታ ሆኖባቸው ሳያገኙት ቀሩ። ይህን ቀድመው የገመቱት ፖሊሶች ተክሌን ፊቱን ሸፍነው በአምቡላንስ ወደ ኤርፖርት አስመልጠውት ነበር ፤ ማንም ሳይደርስበትም በነጋታው ወደ አስመራ በረረ።

ታድያ ያን በቴላቅ ድል የደመቀ እና በመልካም ትዝታ የተቃኘ የብሔራዊ ቡድን ወዳጅነት አስረስቶ ተክሌን መንግስቱ ላይ ያስጨከነው ምን ነበር ? ታላቁ የእግርኳስ ሰው አጋጣሚው እንዴት እንደተከሰተ ለገነነ ሊብሮ እንዲህ ሲል በቃለመጠይቁ አውግቶት ነበር። ” እኔ ኳስ ሲመጣ ሁኔታውን አይቼ ወደ ክንፍ እየሮጥኩ ነው። እዛ ያለው ልጅ ወደኔ ቦታ ሲመጣ ለካ ተክሌን በጣቱ ባለጌ ቦታ ይነካዋል። ተክሌ ደግሞ እዚያ ቦታ ሲነካ ያብዳል። እኔ የኛ ልጅ ያደረገውን አላወኩም። ያ ልጅ ተክሌን ነክቶት እዚያው መሆን ነበረበት። ያን ግን አላደረገውም። ኳስ ወደዚያ ጋር መጥቶ ስለነበር እኔ ኳስ ለማግኘት ፊት ለፊት ስሄድ ተክሌ እንደተናደደ ዘወር ሲል እኔን አገኘኝ። ” ወዲ ምናምን” ብሎ በቴስታ ጥርሴን ሰበረኝ። በወደኩበት ሁሉ ተናዶ የሚሳደበው በዛ የተነሳ ነበር። በኋላ ግን ተክሌ የኔ ጥርስ በመሰበሩ አዝኗል። በብሔራዊ ቡድን እንገናኛለን። ተረዳድተን የምንጫወተውም እኔና እርሱ ነን። ባለጌ ቦታ የነካሁት እኔ አለመሆኔን ሲሰማ የበለጠ በጣም አዘነ። ”

ከዚህ ጊዜ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመልስ ጨዋታ ቴሌን ለመግጠም ወደ አስመራ መሄድ ነበረበት። የተክሌ እና የመንግስቱ ፀብ በወቅቱ የፈጠረው ውጥረት ወደ ደጋፊውም ተጋብቶ ነገሩ ስለተባባሰ ስጋት የገባቸው የአስተናጋጁ ክለብ ባለስልጣናትም “ተክሌ እና መንግስቱን ለማስታረቅ ” በሚል ከጨዋታ በኋላ ትልቅ ግብዣ አዘጋጅተው ነበር። የከተማው ከንቲባ ሳይቀሩ ባለስልጣኖች እና የሚዲያ ሰዎች በተገኙበት ሁለቱ ተጫዋቾች ጉዳዩ ለየብቻ ተነግሯቸው እዛው እንዲገናኙ እና ይቅር እንዲባባሉ ዕቅድ ወጣ። ፕሮግራሙ ተጀምሮም እየተበላ እና እየተጠጣ አስታራቂ ሽማግሌዎች ሁለቱን ተጫዋቾች በምን መንገድ እንደሚያስታርቁ እየተወያዩ ተክሌ እና መንግስቱን በተናጠል እንዲያመጧቸው የተመደቡ ሰዎችን ይጠባበቁ ያዙ። ነገር ግን ተጫዋቾቹ በሆቴል እና በከተማው ቢፈለጉም ሊገኙ አልቻሉም።

“መንግሥቱ እምቢ አለ ፣ ተክሌ አሻፈረኝ አለ ፣ መንግሥቱ ካሳ ይሰጠኝ አለ ፣ ተክሌ እርቁን አልፈለገም” እያለም የተሰበሰበው ሰው ያውካካ ጀመር። ባለስልጣናት እና አስታራቂዎችም “እንዴት ቢንቁን ነው ? ” ብለው ተናደዱ። የደገሱት ሠርግ ያለሙሽሮቹ መና ሊቀር መቃረቡን በማሰባቸው እጅጉን ተቆጩ። ይህን ታላቅ ሀሳብ ይዘው ብዙ ሲወጥኑ ግን ከእነሱ ዕውቅና ውጪ ምን እየተካሄደ እንደነበር አላወቁም። የሆነው ይህ ነበር።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አስመራ ደርሶ ከአውሮፕላን ሲወርድ ከተዘጋጀለት ሰርቪስ አጠገብ አንድ የቤት መኪና ቆማ ነበር። መኪናዋ የተክሌ መሆኗን ያወቀው መንግስቱ ከዛ ክፉ አጋጣሚ በኋላ ስላላገኘው ድጋሜ ለፀብ ፈልጎት ይሁን አይሁን ግራ በመጋባት ዝም ብሎ ሊያልፍ ሲል ተክሌ ” መንግስቱ” ብሎ ጠራው። ይህን ያዩት የመንግስቱ የቡድን አጋሮች ራሳቸውን ለፀብ አዘጋጁ። መንግስቱም ራሱ ቢሆን በውስጡ ሳይቀደም ለመቅድም እያሰበ ነው ወደ ቴሌው አጥቂ የተጠጋው። ነገር ግን የተክሌ እጆች ለቡጢ ሳይሆን ለፍቅር ነበር የተዘረጉት። ሁለቱ አጥቂዎችም እግራቸው ደም በደም ሆኖ ከግብፅ መንጋጋ ዋንጫውን የነጠቁበት የአብሮነት ጊዜያቸውን እያሰቡ ተላቅሰው ከልብ ይቅር ተባባሉ። ተክሌም መንግስቱን ከቀሪዎቹ ተጫዋቾች ለይቶ ሻንጣውን ጭኖ ልክ እንደበፊቱ ሊያስተናግደው ወደ ሆቴል ወሰደው። ከእርስ በእርሱ ጨዋታ በኋላም ከክለቡ እውቅና ውጪ የተክሌ እንክብካቤ ቀጥሎ ነበር። ምንም እንኳን ሁለቱም እነርሱን ማስታረቅ በሚል ሀሳብ ትላልቅ ሰዎች በተገኙበት የተዘጋጀው ግብዣ ፕሮግራም ደርሷቸው የነበረ ቢሆንም በራሳቸው መንገድ እርቅ አውርደው ስለነበር ከጨዋታ በኋላ መንግስቱ ከሆቴል ማንም ሳያያው ወጥቶ ከተክሌ ጋር ተገናኘ። ሁለቱ ወጣቶች በአስመራ መዝናኛ ቤቶች እየዞሩ አንድነታቸውን እያወጁ ህዝቡን በፍቅራቸው ሲያስደምሙት እና ‘ለካ የስፖርተኞች ፀብ ሜዳ ላይ ብቻ ነው’ ሲያሰኙት አመሹ። በመጨረሻም ሞቅ ብሏቸው ተስብስቦ የሚጠብቃቸው ዕድምተኛ ወዳለበት አዳራሽ ተቃቅፈው ገቡ። ብዙ ጥርጣሬ ያስነሳው ከግብዣው የመቅረታቸው ሁኔታ ማንም ባልገመተው አኳኋን የፕሮግራሙን ዋና አላማ ያሳካ መሆኑን የተገነዘበው ተሰብሳቢ ሁሉ በአግራሞት እና በጭብጨባ ወጣቶቹን ተቀበላቸው። በዚህ ሁኔታም አስታራቂዎች እጃቸውን ያላስገቡበት ዕርቅ በሙዚቃ ታጅቦ እስከ ለሊቱ አጋማሽ ዘለቀ።

ይቀጥላል…

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ